በ2030 ሴቶችን የማብቃት አጀንዳ ከወዲሁ ትኩረት ይሰጠው

የሴቶች በፖለቲካ ውሳኔ ሰጭነት የመሳተፍ መብት እ.አ.አ በ1948ቱ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ ዕውቅና አግኝቷል፡፡ የመግለጫው አንቀጽ 2 እና 21 ሴቶች በጾታቸው ምክንያት መድልኦ ሳይደረግባቸው የፖለቲካ መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙ ደንግጓል፡፡ እ.አ.አ. በ1966 የወጣው የፖለቲካና የሲቪል መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት በመግለጫው የተጠቀሰውን የሴቶች በመንግሥትና የፖለቲካ ሕይወት ያለምንም መድልኦ የመሳተፍ መብታቸውን አጠናክሮ ደንግጓል፡፡

የተባበሩት መንግስታት 17 ዘላቂ የልማት ግቦች መካከል  በአምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የፆታ እኩልነትን ማስፈን፣ሴቶችና ልጃገረዶችን ማብቃት አንዱ ነው።ድርጅቱ እ.አ.አ. በ2015 በአሜሪካ ኔውዮርክ ከተማ  ያወጣው እቅድ  እ.አ.አ. 2030 ድረስ በዓለም ላይ ሴቶች ከወንዶች እኩል መብት እንዲኖራቸው የጊዜ ገደብ አስቀምጧል። 

በአገራችን ካለው የሕዝብ ብዛት ሴቶች ግማሹን ቁጥር እንደሚይዙ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ ውስጥ የሚካሄድ ህዝብን የሚመለከት ማንኛውም እንቅስቃሴ እነዚህን የህብረተሰብ ግማሽ አካላት ግምት ውስጥ ያስገባ ሊሆን ይገባል፡፡ሴቶችን የማያሳትፍና እኩል ተጠቃሚ የማያደርግ ማናቸውም ዓይነት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ለውጤት እንደማይበቃ ሊታበል የማይችል ሀቅ ነው፡፡

በአገራችን የሴቶች ትግል ትልቁ ድል እንደሆነ በሚታመንበት የኢፌዴሪ ህገ-መንግሥት መሠረታዊ የሆኑት የሴቶች መብቶች መከበራቸው፣ የኢፌዴሪ የሴቶች ፖሊሲ መውጣቱ፣ በፌዴራልና በክልል መንግስታት የሴቶች ጉዳይ አደረጃጀት መፈጠሩ፣የቤተሰብ ህግ መጽደቁ፣ የወንጀለኛ ህግ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ በደሎችን ለመግታት በሚያስችል መልክ መሻሻሉ…ወዘተ የሴቶችን ጥያቄ ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖራቸው አይካድም፡፡በሌላም በኩል በትምህርት፣በጤናና በሌሎችም የልማት መስኮች የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ የተከናወኑት ሥራዎችና የተገኙት ውጤቶች አበረታች   ናቸው፡፡

በአገራችን የተደረጉ የፓርላማ ምርጫዎችን ለመቃኘት ብንሞክር በየምርጫ ዘመኑ ከፍተኛ የሚባል መሻሻሎችን እናያለን።ለአብነትም  በመጀመሪያው ምርጫ ከ547 የፓርላማ ወንበር  13 (2ነጥብ7በመቶ)  ከነበረበት እድገት እያሳየ መጥቶ አምስተኛው  ምርጫ ላይ ከ547 መቀመጫዎች ውስጥ 213 ወይም 38ነጥብ9በመቶ  መድረሱ ሴቶች በፖለቲካው መስክ ያላቸው  ተሳታፊነት እየጨመር መምጣቱን ያሳየናል። በዚህ ፍጥነት የሴቶች ተሳትፎ የሚቀጥል ከሆነ  የተባበሩት መንግስታት በ2030 የሴቶችን ከወንዶች እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚ ለማድረግ ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት የሚቻልበት እድል ሰፊ ይሆናል።

 የሴቶች ውክልና ከጨመረ የሴቶች ብቃት መጨመሩ አይቀርም፡፡ የሴቶች ብቃት ከጨመረ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው የጾታ መድልኦ አመለካከት በሒደት የሚቀረፍ ይሆናል። አገሪቱ የተነሳችበትን በጾታ መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ  ለማሳካትም ያስችላል፡፡በሁሉም ኅብረተሰብ እንደሚታየው ሴቶች ሕፃናትን የማሳደግና የመንከባከብ ድርሻቸው ሰፊ በመሆኑ የሴቶቹ የውሳኔ ሰጪነት መሳተፍ ሕፃናቱንም መጥቀሙ አይቀርም፡፡የሴት የፖለቲካ ተወካዮች ከሴቶች መብት በተጨማሪ የሕፃናትም መብቶች እንዲከበሩ በተሻለ እንዲሰሩ እድል ይፈጥርላቸዋል፡፡

በፓርላማ ያለው የሴቶች ተሳትፎ እድገት ቢያሳይም በሌሎች ከፍተኛ የፖለቲካ መዋቅሮች ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ግን አናሳ ነው። ከተለያዩ ጥናቶች ለመገንዘብ እንደሚቻለው ሴቶች ወደ ፖለቲካ አመራር ሰጪነት እንዳይመጡ የሚያደርጉ ምክንያቶች ብዙ ናቸው፡፡የመጀመሪያው ባህላዊና ኋላቀር አስተሳሰብ ነው፡፡ ሴቶችን ከአደባባይ ሥራ ይልቅ በጓዳ የሚገድብ ባህል ባለበት ሀገር ሴቶች ከልጆች አስተዳደግ ውጭ ያላቸውን ወይም የሚኖራቸውን ሚና የሚቀበል አሠራር መገንባት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ባህል በወንድ የበላይነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ይቅርና እኩልነታቸው የሚገዳደሩ አስተሳሰቦች ይበዙበታል፡፡

ሌላው ሴቶች ወደ አመራርነት እንዳይወጡ ተጽዕኖ ከሚፈጥሩባቸው ችግሮች መካከል ከራሳቸው የሚመነጭ አመለካከት ነው። ካለባቸው ተደራራቢ የቤት ውስጥ የስራ ጫና በመነሳት ኃላፊነትን ለመወጣትና ለመቀበል ድፍረት አለመኖር፣ ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች፣ በትምህርትና ስልጠና አለመብቃት፣ እንዲሁም የውጪው ተጽዕኖዎች ናቸው።  በሴቶች ብቃት አለማመን፣ በኃላፊነት ቦታም  ሲቀመጡ ስህተት መፈለግ በስፋት ስለሚስተዋሉ እነዚህን የተዛነፉ አመለካከቶች ፈጥኖ ማስተካከል ይገባል።

ሴቶችን በውሳኔ ሰጪነት ለማብቃት ሁሉም ተቋማት የተጠናከረ ሥራ ሊሰሩ ይገባል።በየተቋማቱ የተዋቀሩት የሥርዓተ ጾታ ክፍሎች በአፈፃጸም ደረጃ ውስንነት ማስተካከልና የሴቶችን አቅም በማጎልበት ለአመራር ሰጪነት በማብቃት በኩል የሚስተዋልባቸውን ክፍተቶች ከወዲሁ ሊያስተካክሉ ይገባል።

በየደረጃው የሴቶችን ፎረሞች የማቋቋምና የመደገፍ ጅምር ስራዎች የሚያበረታቱ ቢሆኑም የሚፈለገውን ያህል ባለመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል።ሴቶችን ማብቃት አመለካከትን የመስበር ጉዳይ እንጂ የመመሪያ፣ደንብና አዋጅ ጉዳይ አይደለም።የስርዓተ ጾታ የስራ ክፍሎችን ማቋቋም፣አደረጃጀት እና በጀት ላይ የሚነሱ ችግሮችን  መፍታት ከተቻለ የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል።

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።