ይዋል ይደር የማይባል ተግባር!

 

የኢትዮጵያ ህዝብ ሕይወት ከተፈጥሮና ሰው ሰራሽ  ሀብቶች  ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ለዚህም ነው ማህበረሰባችን በከተማም ሆነ በገጠር ከቤት እንስሳት  ጋር በእጅጉ የተገናኘ ህይወት የመምራት ልምድ   ያለው ፡፡  ይህ ተግባር መጠኑ ይብዛም ይነስም ፤ በደጋ፣ በቆላ ወይም በወይና ደጋ በሚኖረው ሕዝብ ዘንድ በግልጽ ይንጸባረቃል፡፡  እንዳውም በአብዛኛው የገጠሩ ሀገራችን  ከብት አርቢ እንስሳቱን  የልጆቹ ያህል ነው የሚመለከታቸው፡፡ በዚህ  የተነሳም  ልጆቹና ከብቶቹ ሲቆጠሩበት እንኳ አይወድም ፡፡

ከእነዚህ እንደ አይኑ ብሌን ከሚጠብቃቸው ከብቶቹ የሚለየውም  ድርቅ ፣ የእንስሳት በሽታ እና ችግር ብቻ ናቸው ፡፡ በተለይ እንደ አሁኑ ለእንስሳቱ የህክምና አገልግሎት በስፋት ባልነበረባቸው በእነዚያ አስከፊ ወቅቶች ከብቶቹ ክፉኛ በበሽታ ሲጠቁም ሃዘኑ የበረታ ነበር፡፡ ጉዳቱ ባለችው ሀብት  ላይ ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ ትስስሩ ላይ ጭምር እንዲሆን የሚያደርገውም ይኴ ነበር፡፡

በእርግጥ ይህ አስተሳሳብ  እየተቀየረ ከመጣ  ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በሀገሪቱ ለእንስሳት ሀብት እየተሰጠ ያለውን ትኩረት ተከትሎ የክትባት አገልግሎቱ እንዲሁም በማዳቀል ስራ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለማውጣት የተደረጉ ሰፊ ተግባሮችን ተከትሎ የዜጎች የእንስሳት ሀብት ተጠቃሚነት እያደገ መጥቷል፡፡ አንድ ከብት ለጥቂት ወራት ብቻ በማድለብ ተጠቃሚ እየሆኑ ያሉ ዜጎች ቁጥር በርካታ ሆኗል፡፡

ይህ በእንስሳት ሀብት ልማት ላይ እየመጣ ያለ ለውጥ ግን በግብይት በኩል ሊደገፍ ባለመቻሉ  ሳቢያ በተለይ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች እንዲሁም ሀገሪቱ የእንስሳት ሀብቱ ዋነኛ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ አልተቻለም፡፡ ውጤቱም የሚፈለገውን ያህል አልሆነም፡፡ እነዚህ ችግሮች ሀገራችን በእንስሳት ሀብት ብዛት  ከዓለም በ10ኛ ደረጃ ላይ ፤  ከአፍሪካም ቀደሚዋ የመሆኗን ያህል ተጠቃሚ እንዳትሆን አድርገዋታል ፡፡          

በተለይ ከዘመናዊና ህጋዊ ዓለም አቀፍ ግብይት አለመጠናከር ጋር በተያያዘ ከሀገራችን ይልቅ ከዚህ ሀብት በእጅጉ ተጠቃሚ እየሆኑ ያሉት ኮንትሮባንዲስቶች ናቸው፡፡ ከየአካባቢው የቁም እንስሳቱን  ወደ ተለያዩ ሀገሮች የሚወስዱ ህገወጥ ነጋዴዎች፣ ደላሎችና ሌሎች  በልማቱ ላይ  ምንም ሚና የሌላቸው በህገወጥ ሰንሰለት የተቃፉ የተለያዩ  አካላት  ናቸው ፡፡ 

እነዚህ ህገወጦች የሀገሪቱን የቁም እንስሳት እየነዱ ድንበር በማሻገር በርካሽ ዋጋ ለገበያ የሚያቀርቡ ናቸው፡፡  በመሆኑም  በተለያዩ የሕግ ሥርዓቶች  የሚገዙት  የኢትዮጵያ ሕጋዊ ነጋዴዎች ተወዳድረው ለመሸጥም  ተቸግረዋል፡፡ ሀገራችንም ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሬ እየተነጠቀች ነው ፡፡

በቁም እንስሳት የወጪ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻዎች እንዳመለከቱትም  ዘርፉን ህገወጥ ንግድ ፣ የኳረንቲን አገልግሎትና የፋይናንስ አቅርቦት አለመኖር፣ የመኖ እጥረትና የመሳሰሉት  ችግሮች  ፈተና ሆነውበታል፡፡

  በሀገወጥ መንገድ ከሀገር እንዲወጡ የሚደረጉ የቁም እንስሳት በውጭ ሀገር ለገበያ የሚቀርቡበት ዋጋ ዝቅተኛ  መሆን ፣ የሀገራችን ነጋዴዎች ቀረጥ እየከፈሉ ወደ ውጪ ከሚልኩበት ዋጋ ጋር የሚወዳደር አለመሆኑ እንዲሁም  ከበሽታ ጋር በተያያዘ ወደ ውጭ ከተላኩ በኋዋላ የሚመለሱ እንስሳት ጉዳይም  ዘርፉ በጽኑ የታመመ መሆኑን የሚያመለክቱ ከመሆናቸውም በላይ የአፋጣኝ ህክምናን አስፈላጊነት ያስገነዝባሉ፡፡

የእንስሳት ግብይት ችግርን በመፍታት ሀብቱን በሚገባ ለመጠቀም እንዲያስችል ባለፈው ዓመት የወጣው አዋጅ ወደ ስራ አለመግባቱም ሌላው የዘርፉን ችግር ከመቀነስ ይልቅ እንዲወሳሰብ  ያደረገ ነው፡፡ እነዚህ ችግሮች  ነጋዴዎቹ እና ሀገሪቱ በገዛ ህብታቸው የበይ ተመልካች እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል፡፡

በተለይ ከህክምና እና ኳረንቲን ጋር ተያይዞ የሚነሳው ችግር ዘመናትን ያስቆጠረ ነዉ፡፡ በተለይ  በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ለሚላኩ እንስሳት አስፈላጊው  የኳረንቲን አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው  በውጭ ሀገሮች እንደመሆኑ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት በእጅጉ  መጉዳቱም ተለይቷል፡፡ አሁንም  እየጎዳንም  ይገኛል ፡፡   ለዘመናት ተንሰራፍቶ የቆየውን ይህን ችግር ለመፍታት ከዓመታት በፊት እንደሚገነቡ ይጠበቁ የነበሩት ኳረንቲኖች ጉዳይ ዛሬም አድሮ ጥሬ አይነት  መሆኑ  ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት  ገና ብዙ መጓዝን ይጠይቃል ማለት ነው፡፡

በአጠቃላይ በሀገራችን የእንስሳት ህክምና አገልግሎት እየተስፋፋ መሆኑ አንድ እርምጃ ነው፡፡ ይሁንና  በእንስሳት ሀብታችንን  በሚገባ መጠቀም ይቻላል ተብሎ በሚታመንበትና  በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ብዙ በተሰራበት በዚህ ዘመን  የላቀ ውጤት አለማስመዝገብ ሊፈተሽ ይገባል፡፡ ይህን እምቅ  ሀብት ይዘን ተጠቃሚ የማያደርግን የትኛውንም የግብይት ደንቃራ ማስወገድም   ይዋል ይደር የማይባል አብይ ተግባር መሆን ይኖርበታል፡፡

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።