ዘመን የማይሽረው የተጋድሎ ታሪክ!

የኢትዮጵያ ህዝቦች በነፃነትና ልዑላዊነት ቀናኢነታቸው ወደር የሚገኝላቸው አይደሉም፡፡ አንድነትን፣ ሀገርን፣ ሰንደቅንና ነፃነትን ላለማስደፈር ለዘመናት በጀግንነት ሲወድቁ የኖሩትም በዚሁ ጠንካራ ማንነታቸው ነው፡፡ ሀገራችንን ከበርካታ ዓመታት በፊት አንስቶ የወረሩ የውጭ ኃይሎችን አይቀጡ ቅጣት እየቀጡ፤ ለአሁኑ ትውልድ ያስረከቡትን አያት ቅድመ አያቶቻችንን ለዘመናት ስንዘክር የመኖራችን ሚስጥርም ይሄውና ይሄው ብቻ ነው፡፡

አዲሲቷ ኢትዮጵያም ብትሆን ጥላትም ሆነ ጀግናና አርበኛ ትውልድን ያጣች አይደለችም፡፡ በተለይ ባለፉት 25 ዓመታት የሀገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በእኩል ተጠቃሚነትና ተሳትፎ እየገነቧት ያለችው ሀገራችን ዘላቂ ሠላሟን ያረጋገጠችው ታሪክ በተረከበው የመከላከያና የፀጥታ ኃይሉ ትጋት መሆኑ ሊዘነጋ አይችልም፡፡ የጀግኖቹ ወላጅ  የሆነው ህዝቡም ሠላሙን በማስጠበቅ በኩል ያለው ድርሻ ወደር የለውም።

ኢትዮጵያ በተለይ በአሁኑ ወቅት ከየትኛውም ህዝብና መንግሥት ጋር ተስማምቶ የመኖር፣ ሰጥቶ የመቀበል የውጭ ፖሊሲ ያላት ሀገር ነች፡፡ ያም ሆኖ ሀገራችን በጀመረችው ፈጣን ለውጥና የህዳሴ ጉዞ ምክንያት ዕንቅልፍ የሚያጡ ጠላቶች በዙሪያዋ ተፈጥረውባታል። ከዚህ አንጻር እንደ ኤርትራ መንግሥትና አልሻባብን የመሳሰሉ ፀረ ሠላምና የጥፋት ኃይሎችን ተደገጋሚ አካሄድ አብነት አድርጎ መጥቀስ ይቻላል፡፡

በሰላሙ መንገዳችን በአብሮ እንልማ መርሀችንም እንደ አለመታደል ሆኖ ጠላት ብናፈራም፤ የጠላት ቅስምንና አከርካሪን መስበር የሚያውቀበት መከላከያ ሰራዊት ስላለን ደግሞ ከእድልም በላይ እድለኞች ሆነናል።

የጠላቶቻችን እኩይ ተግባርና የጥፋት መንገድ በጀግናው የመከላከያ ኃይላችንና በምልዐተ ህዝቡ ብርቱ ጥረት ከአንዴም ሁለት ሦስት ጊዜ እንዲመክን ሆኗል፡፡ ከ15 ዓመታት በፊት በተሳሳተ ስሌት ሀገራችንን የወረረው ሻእቢያ ዳግም ይፋዊ ጦርነት በማይለኩስበት ደረጃ ተኮላሽቶ ተቀምጧል፡፡ አልሻባብም ጎረቤት ሶማልያን ስርዓት አልባ በማድረግ ጅሃድ አውጆ ሀገራችንን ለማጥቃት ቢዝትም ምኞቱን እዛው ከበቀለበት ምድር ፈቅ ሳይል ማምከን ተችሏል፡፡ የሶማልያ ህዝብም እፎይታን አግኝቶ በአዲስ የምርጫ ስርዓት መሪውን እስከመምረጥ ያደረሰው በመከላከያ ኃይላችን ግንባር ቀደም አስተዋጽኦ ነው፡፡ ይሄ ለጀግና ህዝብና ሰራዊት ትልቅ ኩራት ነው።

ትናንት  በኢትዮጵያ ሳማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ለ5ኛ ጊዜ በተከበረው የመከላከያ ቀን ላይ እንደተገለፀውም፤ ዘመን የማይሽረው የኢትዮጵያዊያን ጀግንነትና አርበኝነት አሁንም በመከላከያ ኃይላችን እየጎለበተ መጥቷል፡፡ ለዚህም ነው የዕለቱ መሪ ቃል “በህዝባዊ መሠረት ላይ የተገነባው ጀግንነታችን እየታደሰ ይኖራል” የሚል ጠንካራ ሀሳብን ያነገበው፡፡

በስነስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመም ጀግናው የመካላከያ ኃይላችን የህዝብና መንግሥት አደራን ተቀብሎ እየፈፀመ ላለው ተግባር አመስግነዋል፡፡ ይህን ዘመን የማይሽረው ጀግንነት ተጠቅሞና፣ ህዝባዊነቱን ጠብቆ ለወደፊቱም ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎችን እየመከተ የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ለማስቀጠል እንዲተጋም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣን፣ የመከላከያ ባለከፍተኛ ማዕረግ አዛዦች፣ የጅግጅጋ ከተማ ህዝብና የደቡብ ምስራቅ ዕዝ አባላት በተገኙበት በዚህ ደማቅ ስነስርዓት ላይ የተከናወነ አንድ ታሪካዊ ተግባርም ነበር፡፡ ይኸውም የኢትዮጵያዊያን የጀግንነትና አርበኝነት ውርስ እንደ ወራጅ ወንዝ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚፈስ መሆኑን ያስመሰከረ ገድል ነው፡፡

ይህ በወርቃማ የታሪክ መዝገብ ተከትቦ ወደ ሌላ ትውልድ የሚሸጋገረው ጀግንነትም፤ የደቡብ ምስራቅ ዕዝ የ13ኛው ክፍለ ጦር 4ኛ ሬጅመንት አዛዦችና አባላት በሶማልያ በሃልሜን አውደ ውጊያ ውሎ የፈጸሙት ጀግንነት ነው።

አልሻባብ ለዓመታት የደረሰበትን ተከታታይ ጥቃት ተከትሎ ባለ በሌለ ኃይሉና በውጭ ሀገሮች ድጋፍ ጭምር ታግዞ ሰኔ 2 ቀን 2008 ዓ.ም በጀግኖቹ ኢትዮጵያዊያን ምሽግ ላይ ይዘምታል፡፡ ጨለማን ተገን አድርጎ፤ በከባድ መሳሪያ ታግዞ በመከላከያ ኃይላችን ካምፕ ላይ የከፈተውን ውጊያ በጀግንነት በመመከት በመልሶ ማጥቃት ታሪክ የማይረሳውን የአርበኝነት ተግባር የፈፀመችው ይህች 4ኛ ሬጅመንት ነበረች፡፡ የሬጅመንቱ አባላትም ላስመዘገቡት ከፍተኛ ድልና  ጀግንነት 2 ደረጃ የሚዳሊያ ሽልማት ከፕሬዚዳንቱ እጅ ተቀብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ፊት ኩራትና ክብርንም ተቀዳጅተዋል፡፡

በአውደ ውጊያው የተሰው የሬጅመንቱ አዛዥ ኮሎኔል ጌጡ ዳምጤና ሌሎች ሰማዕታትም በክብር ተወስተዋል፡፡ መቼም ለማይነጥፈው ኢትዮጵያዊ ጀግንነት ዳግም ምስክር ሆነዋል፡፡ በዚህ አርዓያነት ኢትዮጵያዊያን ሁላችን ለሀገራችንና ለህዝቦቿ ሰላምና ብልፅግና አርበኞች መሆን ይኖርብናል፡፡ ታሪክ ሰሪዎችም ልንሆን ይገባል፡፡   

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።