ድርድሩ የመግባባትና የልማት አቅጣጫን የሚይዝ ይሁን!

      ለአገርና ለወገን ከመሥራት ይልቅ በማይረባ ነገር  እርስ በእርስ መጠላለፍ፣ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አመለካከትና ልዩነትን አቻችሎ መንቀሳቀስ ያለመቻል፣ የራሳቸውን ችግር በማድበስበስ ህዝቡን ለማደናገር«መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ችግር እየፈጠረብን ነው» በማለት መግለጫ ለመስጠት አልቦዘኑም። ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሙጥኝ ያሉት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አካሔዳቸው ሊያስማማቸው ባለመቻሉ በየጊዜው እርስ በእርስ መበጣበጥ፣ አንዳቸው አንዳቸውን ለማዳመጥ ትዕግስት እያሳጣቸው መምጣቱና በቃላት እንጂ በተግባር የህዝብ ወገንተኛነታቸውን ማሳየት አለመቻላቸው በህዝቡ ዘንድ ታአማኒነትን እያሳጣቸው መጥቷል፡፡

       ይህ ሊደብቁት ያልቻሉት ገመናቸው በየጊዜው ሲያጋልጣቸውና የተጠናወጣቸው ኩርፊያ ብዙ አስቸጋሪና አሳፋሪ ድርጊቶችን እንዲያደርጉ እየገፋፋቸው የስብሰባ መድረክ እየረገጡ እንዲወጡ ሲያስገደዳቸው፤ አለያም የያዙት መስመር እንደማይሳካ ሲታወቃቸው ሰበብ ሲፈጥሩ ቆይተዋል፡፡

     የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ማየት የምንችለው በአገራችን የዕድገት ደረጃ ልክና በምናጣጥመው ሰላም  እንጂ በበለፀጉት አገሮች ልክ ከሆነ መነሻችንን ያለማወቃችን መድረሻችንን ለመገመት አዳጋች ያደርግብናል፡፡

      ከእኛ በብዙ ሁኔታ በተለይም በዴሞክራሲያዊ ስርዓት፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት የተሻለ ደረጃ ላይ የደረሱትና ለብዙ  ዘመናት በሰላም የኖሩት አገሮች ተሞክሮ የሚያሳየው ጥቂቶች እየጠፉ በመምጣታቸው ሳይሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ መብታቸውን ለማስከበር የተሻለ ሥርዓት መፍጠር በመቻላቸውእንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡

       እንደሚታወቀው ሕገ-መንግሥታችን  በዋናነት ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎችን የመለሰ ነው፡፡ አንደኛው ለዘመናት የግጭት ምክንያት የሆነውን ስልጣንና ሀብት በማዕከልና በጥቂት ኃይሎች መከማቸት የፈጠረውን ችግር  የማህበራዊ ፖለቲካው  የህልውና ጉዳይ በመሆኑና ስልጣንና ሀብት በፌዴራል እና በክልሎች መካከል ፍትሐዊ  ማድረጉ፤ሁለተኛው ደግሞ የህዝቦችን የማንነት ጥያቄ ለመመለስ  ራሳቸውን የማስተዳደር የራሳቸውን ማንነት፤ቋንቋ፤እምነትና ታሪክ ለማሳደግና ወደ ቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችል መሆኑ ነው፡፡

     ከዚህ አንፃር በእኛ አገር የተዘረጋውን የዴሞከራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ከምርጫና ውክልና አንፃር ስንመለከተው መስመሩ ጠርቶ እናገኘዋለን፡፡ ታዲያ ለምን ሁሌም ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በገዢው ፓርቲ ላይ ተመሳሳይ ይዘት ያለው አቤቱታ ያሰማሉ? ችግሩ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ ፓርቲዎች ሊኖራቸው ከሚገባው ሚና የሚመነጭ እንደሆነ አብዛኞቹ የፖለቲካ ምሁራን ይስማማሉ፡፡

      በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የፖለቲካ ድርጅቶች በመንግሥት ደረጃ እውቅና አግኝተው ዜጎችም በነፃነት  ፓርቲ በመመስረት በፖለቲካ ሂደቱ መሳተፍ የጀመሩት ከ1983 ወዲህ ነው፡፡ አራት ዓመት የፈጀ የሽግግር ወቅት ከተደረገ በኋላ ከ1987 እስከአሁን ድረስ ደግሞ አምስት አገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡እነዚህን አገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫዎችን ከዴሞክራሲና ከህብር ፓርቲ መርሆ ጋር አገናኝተን ብንመረምር የተቃዋሚ ፓርቲዎቻችንን አሉታዊ ሚና ለመረዳት እንችላለን፡፡ በተለያየ ጎራ ተሰልፈው የሚገኙት እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደተቋም ሳይሆን በግለሰቦችና በጥቂት መሪዎች የሚሽከረከሩ ከህዝብ ጋር ጠንካራ ትስስር ያልፈጠሩ በመሆናቸው ምክንያት ገዢውን ፓርቲ በሚፈታተን መልኩ መውጣት አለመቻላቸው ለዴሞክረሲያዊ ስርዓት ግንባታው አስቸጋሪ ሁኔታ ነው፡፡ አሠራራቸው ዴሞክረሲያዊ አለመሆኑና እንወክልሃለን የሚሉትን ህዝብ ጥቅም ወደ ጎን በመተው የራሳቸውን የግል ወይም የቡድን ተልዕኮ ለማሳካት መንቀሰቀሳቸው ከህዝቡ ጋር ያላቸውን ትስስር እንዲዳከም ያደረገው በመሆኑ በዚህም በኩል ሚናቸው ምንም እንዲሆን አድርጎታል፡፡

      አልፎ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰፍኖ የምናየው የፖለቲካ አስተሳሰብ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ማለት ገዢው ፓርቲ የያዘውን ፖሊሲ መቃወም ብቻ የሚመስላቸው ኃይሎች የመኖራቸው ሁኔታ ሲሆን፤ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሕዝብ ከተመረጡ ነገ የመንግሥት ሥልጣን ተረካቢ የመሆን ዕድል ያላቸው ከመሆናቸው አንፃር ገዢውን ፓርቲ ከመቃወምና ከማብጠልጠል አልፈው ዘርዘር ያለና የሕዝብን ጥቅም የሚያረጋግጥ አማራጭ ፖሊሲና የነጠረ ሕዝባዊ አመለካከት ለህዝቡ መሸጥ ይገባቸው ነበር፡፡ ከዚህ ዓይነት ጭፍን አስተሳሰብ ያልተላቀቁት የፖለቲካ ኃይሎች ስልጣን ቢይዙስ ምን ያህል የተረጋጋና ዘለቄታዊነት ያለው የፖለቲካ ሥርዓት ይኖረናል?የሚለውን ጥያቄም አብሮ ማሰቡ የግድ ይለናል፡፡

       ሌላው ችግር በተለያዩ ጎራ የሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች የሚያሳዩት አደገኛ አመለካከት ማለትም ገዢውን ፓርቲ ለማድከም ሲባልና በህዝቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ለመቀነስ የተከተሉት ስልት ምርጫ በተቃረበ ቁጥር አልፎ አልፎ ከሂደቱ ራሳቸውን ማግለልና ደጋፊዎቻቸው እንዳይሳተፉ ቅስቀሳ ማድረግ፤አለያም የምርጫውን ትክክለኛና ሕጋዊ አካሄድ ማጣጣል፤ ፓርላማ አንገባም በማለት የፖለቲካ ሂደቱን ለማዳከም መሞከራቸው ነው፡፡ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቋቋሙበት ዋና ምክንያት(ዓላማ) ደጋፊያቸውንና አባላቸውን በአንድ የፖለቲካ ዓላማ ስር በማደራጀት፤በማስተማርና በመምራት በምርጫ ጊዜ ወሳኝ ሆነው መውጣትና በሕዝብ ምርጫ የፖለቲካ ስልጣን መያዝ ነው፡፡ ሆኖም በየጊዜው ምርጫ በተቃረበ ቁጥር በአመዛኙ የምናየው ሂደቱን የመኮነንና በተለያዩ መንገዶች ለማሰናከል መጣር ነው፡፡

      ለዚሁ በተደጋጋሚ የሚቀርበው መልስ የፖለቲካ ምህዳሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ መጥበብና በክልሎች አካባቢ የተመቻቸ የፖለቲካ ሁኔታ አለመኖሩ ነው፡፡ ይህ ሰበብ እውነትም ብቸኛ ምክንያት ከሆነና የተወሰነ እውነትነት ካለው ገዥው ፓርቲ ዴሞክራሲ ሥርዓቱ ሁሉን አቀፍ እንዲሆንና ስር እንዲሰድ በክልሎች አካባቢ የሚታየውን  ችግር በጊዜ መፍትሔ በመስጠት የዴሞክራሲ ሂደቱ እንዲጎለብት የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡

       በዚህ ምክንያትም ነው ባለፈው ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ  በመንግሥት/ኢህአዴግና በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ውይይት እንደሚካሄድ የገለጹት፡፡

     የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመም በሕዝብ ተወካዮችና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን መክፈቻ ላይ  የመንግሥትን የዓመቱን የሥራ ክንውን በሚያመለክተው ንግግራቸው ይህንኑ ጉዳይ አንስተው እንደነበረ ይታወሳል። ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው የምርጫ ሕጉን ለማሻሻል መንግሥት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀው ነበር።

      ያ ቃል በተገባው መሠረት በኢህአዴግ ጋባዥነት ጥር 10 ቀን 2009 ዓ.ም በተካሄደ ቅድመ ድርድር ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቡዕ የካቲት 8ቀን 2009ዓ.ም የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ)ና 21 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ወደ ክርክርና ድርድር ለመግባት በሚያስችላቸው የደርድር አካሄድ ሥነ ስርዓት ማእቀፍ ላይ ውይይት አካሂደዋል። ፓርቲዎች ለዚህ ዓይነቱ ውይይት ያበቃቸውን ህገ መንግሥታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አክብረው ፣ መንግሥትና ገዢው ፓርቲ በአገር አቀፍ ደረጃ ያከናወኗቸውን ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች በመገንዘብ እነርሱም የልማት ሥራው ተሳታፊ በመሆን ለልማት ሥራው አጋዥ የሚሆኑበትን አቅጣጫ መያዝን ልብ ሊሉት ይገባል፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።