ድህነትን ለማሸነፍ የምንተገብራቸው መርሃ ግብሮች ጥብቅ ቁጥጥር ያሻቸዋል

በ2004 ዓ.ም የተጀመረውና 4 ሺህ በሚሆኑ በገጠር እና አነስተኛ ከተሞች የሚገኙ ቤተሰቦች ላይ የተሠራው ጥናት ባለብዙ መገለጫ ድህነት በኢትዮጵያ መቀነሱን የካቲት ወር 2009 ዓ.ም ይፋ አድርጓል፡፡ ጥናቱ በ2006 እና 2008 ዓ.ም ተጨማሪ የከተማ ቤተሰቦችን በማካተት በአጠቃላይ ከ5 ሺህ በላይ ቤተሰቦች ላይ በመመርኮዝ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ላይ ነበር የተካሄደው፡፡ በማዕከላዊ ስታስትቲክስ ኤጀንሲና በዓለም ባንክ የተሠራው ይህ ጥናት ትኩረቱን ያደረገው በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በግብርና ጉዳዮች ላይ ነበር፡፡ 

የጥናቱ አካል በሆኑት ቤተሰቦች ላይ የሚታየው የኑሮ ሁኔታ እንዲሁም የምርታማነት ለውጦች ሊመጡ የቻሉት ምን አይነት የልማት ፖሊሲዎች ተተግብረው መሆኑንና ሌሎች ጉዳዮችን ለማጥናት ያስችላል፡፡

የኢትዮጵያ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መረጃ ከሚሰበስብባቸው ዘርፎች መካከል ትምህርት፣ ጤና፣ የጊዜና የገንዘብ አጠቃቀም፣ የሥራ ሁኔታ፣ የምግብ ዋስትና እንዲሁም ግብርና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በከተሞች የሚኖሩ የድሃ ድሃና ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ዜጎችን የኑሮና የገቢ ደረጃ በማሻሻል ወደ ዘላቂ የኑሮ ዋስትና ማሸጋገር ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

በቀጣዮቹ አስር ዓመታት በሀገሪቱ 972 ከተሞች የሚኖሩ 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚገመቱ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የሚጠበቀው የከተሞች የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር ፕሮጀክት ትግበራው ሙሉ በሙሉ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ ይህ በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ በቀጣዮቹ አስር ዓመታት የሚተገበረው የማህበራዊ ዋስትና ፖሊሲ አካል የሆነው መርሀ ግብር ወደ ትግበራ የገባው 190 ሺ ሰዎችን በማሳተፍ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ በመጋቢት ወር በሃዋሳ ከተማ፣ በሚያዝያ ወር ደግሞ በጅግጅጋ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ እና በሌሎች ሦስት ከተሞች፣ በግንቦት ወር አጋማሽ በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ሙሉ መተግበር ጀምሯል፡፡ በአሶሳና ጋምቤላ በሰኔ ወር  የተጀመረ ሲሆን፣ በሎጊያ ከተማም ሰሞኑን እንደሚጀመር ይጠበቃል፡፡

የምግብ ዋስትና ፕሮጀክቱ እየተካሄደ የሚገኘው ከዓለም ባንክ በተገኘ 350 ሚሊዮን ዶላር እና ከኢትዮጵያ መንግሥት በተመደበ 150 ሚሊዮን ዶላር በድምሩ በ450 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ነው፡፡ በመጀመሪያው አምስት ዓመት የፕሮጀክቱ ትግበራ፤ በአሥራ አንዱ ከተሞች ከ600 ሺ የሚልቁ ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ይጠበቃል፡፡

በፕሮጀክቱ የመጀመሪያው መርሃ ግብር የታቀፈ አንድ ቤተሰብ ለሦስት ዓመት ድጋፍ ከተደረገለት በኋላ ቦታውን ለሌላ ቤተሰብ የሚለቅበት እና አዳዲስ ድጋፍ የሚሹ ዜጎች የሚካተቱበት አሰራርን ዘርግቷል፡፡ ይህ ማለት የመጀመሪያዎቹ ተጠቃሚ ቤተሰቦች የራሳቸው የገቢ ምንጭ መነሻ ካፒታል ይዘዋል ተብሎ ስለሚገመት ነው፡፡ የመርሃ ግብሩ ዋና ዓላማም በድህነት ውስጥ እየኖሩ የሚገኙ ዜጎች ከድጋፍ በዘለለ ዘለቄታዊ የገቢና የኑሮ ዋስትና እንዲኖራቸው ማስቻል ነው፡፡

በፕሮጀክቱ የሚካተት ቤተሰብ የሚመዘንባቸው መስፈርቶች አስቀምጧል፡፡ በምግብ ዋስትና ፕሮጀክቱ ድጋፍ የሚያገኙ ቤተሰቦችን ለመለየት፤ ቤተሰቡ ያለው አንጡራ ሀብት፣ የገቢ መጠኑና የኑሮ ሁኔታው እንደመለኪያ በመውሰድ የኑሮ ደረጃ ምዘና ያደርጋል፡፡ 

የምግብ ዋስትና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ቤተሰቦች ትክክለኛ ልየታ ማካሄድ ትልቁ ፈተና መሆኑ አይካድም፡፡ ቢሆንም በተቻለ መጠን ጥንቃቄ አድርጎ በተዘረጋው አሰራር መሰረት ለመሥራት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

መርሃ ግብሩ በሦስት የተለያዩ መንገዶች ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ ተቀምጧል፡፡ በመርሃ ግብሩ ከታቀፉት መካከል መሥራት የሚችሉ በከተማ የአካባቢ ልማት ሥራ ላይ ተሰማርተው ድጋፉ ይደረግላቸዋል፡፡ ጧሪ የሌላቸው አረጋውያን፣ ወላጅ ወይም ደጋፊ የሌላቸው ህፃናት፣ በአካል ጉዳት ምክንያት መሥራት የማይችሉ ነዋሪዎች በየወሩ ቀጥታ የገንዘብ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡

 የምልመላና የመረጣ ሂደቱ የተቀመጠውን መስፈርት የሚያሟሉትን በመለየት ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደተደረገበት ይታመናል፡፡ ሆኖም ሙሉ በሙሉ የተጣራ ሥራ ተሠርቷል ተብሎ መቀበል አይቻልም፡፡ ድህነትን ለማሸነፍ የሚተገበሩ መርሃ ግብሮች ጥብቅ ቁጥጥር ያሻቸዋልና በቀጣይነት በሚደረገው የመለየት ሥራ  ሊያጋጥም የሚችልን አግባብ ያልሆነ ጥቅም ፍለጋና አድሎን ለመቀነስ የተለያዩ ዘዴዎችን በመዘርጋት ሊተገበር ይገባል እንላለን፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።