የወርቅ ንግዱ ጋሬጣ የሆነው ኮንትሮባንድ ከልብ ይዘመትበት!

በቅርቡ የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የ2008 በጀት ዓመት አፈፃፀም ይፋ ተደርጓል። በዚህ መሰረትም ጠቅላላ የወጪ ንግዱ እና የአገልግሎት ዘርፉ ለጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ በ2007 በጀት ዓመት ከነበረበት የዘጠኝ ነጥብ አራት በመቶ ምጣኔ በአንድ ነጥብ አራት በመቶ በመቀነስ፤ በ2008 በጀት ዓመት ወደ ስምንት በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ ለአፈፃፀሙ መቀነስ ዋና ምክንያት የቡና፣ የሰሊጥ፣ የወርቅ እና ሌሎች የወጪ ንግድ ሸቀጦች ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ መቀነስ እንደሆነ ተገልጿል። 

የእኛም ነጥብ ያለው እዚህ ላይ ነው፤ የወርቅ የወጪ ንግድ መቀነስ ላይ። ቀደም ባሉት ዓመታት ከቡና ቀጥሎ ወርቅ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ ኖሯል። አሁን ላይ ግን ይህ እውነታ እየተቀየረ መጥቷል። በተጠናቀቀው የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ  ዘመን ከወርቅ የተገኘው ከፍተኛው ገቢ  በ2004 ዓ.ም የነበረ ሲሆን፤ 12 ቶን ወርቅ ለዓለም ገበያ ተልኮ 602 ሚሊዮን 425 ሺ ዶላር ገቢ ነው ማግኘት የተቻለው። ይህ መጠን የሚናቅ ባይሆንም ከዚህ በላይ ማግኘት ይቻል እንደነበረ ግን የሌሎች አገራት ገቢ ይነግረናል። አፍሪካዊቷ አገር ጋና እአአ በ2016 ከወርቅ ንግድ ሦስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች።

 በእርግጥ ጋና ያላትን ያህል ወርቅ ኢትዮጵያ አላት ተብሎ መከራከር ውሃ የማያነሳ ጉንጭም የሚያለፋ አመክንዮ ነው። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ያላትን የወርቅ ሀብት ያህል እንኳን መጠቀም እንዳልቻለች መረጃዎች ያሳያሉ። በ2009 በጀት ዓመት በእቅድ ደረጃ ከወርቅ ይገኛል ተብሎ የነበረው 675 ሚሊዮን 991 ሺህ ዶላር ቢሆንም የተገኘው ግን  290 ሚሊዮን 677 ሺህ ዶላር ብቻ  ነው። ይህንን አፈፃፀም ስንመለከት የወርቅ ንግዱ በትክክለኛው መንገድ እየተጓዘ ነው ማለት አይቻልም። ለምን?

ለወርቅ ገቢ ማሽቆልቆል ዋናው ምክንያት የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት ነው ተብሏል። ኮንትሮባንድ አንዱ የአገሪቷ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በሆነው ወርቅ ላይ ከዘመተ የኢኮኖሚው መጨረሻ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ስለሆነም መንግሥት የወርቅ ንግዱ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ያሽቆለቆለበት አብይ ምክንያት ኮንትሮባንድ መሆኑን ተገንዝቦ መፈተሽ ያለበትን ጓዳ ሁሉ ይፈትሽ።

የንግድ ሚኒስትሩ ዶክተር በቀለ ቡላዶ ከአንድ ወር በፊት የተቋማቸውን የ11 ወራት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት የኮንትሮባንድ ንግድ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እየገዘገዘ እንደሆነ መናገራቸውና ይሄው ጉዳይም በሰፊው መዘገቡ አይዘነጋም። ሚኒስትሩ በወቅቱ፤ ‹‹በኮንትሮባንድ ጉዳይ እርር ድብን ብሎ መድረክ ላይ የሚናገር አመራር ራሱ በር ከፋች ነው፡፡ አልያም አይቶ አላፊ ነው?›› ሲሉም በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ችግር መኖሩን አስታውቀዋል። አያይዘውም፤ ‹‹የአመራሩ ድራማ መቆም አለበት፡፡ ሆነን መገኘት መቻል አለብን›› ሲሉም ተደምጠዋል።

 እውነታውም ይሄው ነው። ይሄንን የሚኒስትሩን የምሬት ቃል እየቀነሰ ከመጣው የወርቅ ገቢ አንፃር ካየነው ለገቢው ማሽቆልቆል በአመዛኙ ዋናው ምክንያት ኮንትሮባንድ ነው ከማለት የዘለለ ድምዳሜ የለም። የዓለም ገበያ መዋዠቅ ሌላ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የዓለም ገበያ መዋዠቅን ለመቋቋም ወደ ውጭ የሚላከውን የወርቅ መጠን በመጨመር መከላከል ይቻላል። እውነታው ግን የሚላከው የወርቅ መጠንም እየቀነሰ መምጣቱ ነው። ስለሆነም የችግሩ ቁልፍ ነገር ያለው ኮንትሮባንድ ላይ ነውና መንግሥት ከላይ እስከ ታች ያለውን መዋቅሩን ከአንገት ሳይሆን ከአንጀት ይፈትሽ።

አገር እየተጎዳ ግለሰብ የሚበለጽግበት ምክንያት አይኖርም፤ ሊኖርም አይገባም። ስለሆነም በወርቃችን ላይ የመጣው ቀበኛ እጅ ሊቆረጥ ይገባል። ብሄራዊ ባንክም መፈተሽ ያለበትን አሠራር መፈተሽ አለበት። ከዓለም ገበያ የተሻለ ዋጋ እያቀረበ አቅራቢዎችን ለማበረታታት የሚያደርገው ጥረት በጥቁር ገበያው እየተፈተነ ስለሆነ ወቅቱንና ገበያውን ያማከለ ዋጋ በመስጠት፤ እንዲሁም ከህግ አካላት ጋር አብሮ በመሥራት በወርቅ ላይ የተጋረጠውን ጋሬጣ ሊያስወግድ የግድ ይለዋል።

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።