የአብረን እንብላ ውል ሊቋረጥ ይገባል!

ባለፉት ጥቂት ወራቶች ዋነኛ የመነጋገሪያ ርዕስ ወይም አብይ ጉዳይ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ትምክህተኝነት፣ ጠባብነት፣ አድርባይነትና ብልሹ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች በአገሪቱ ስር በመሰደዳቸው ምሬቱ ያስከተለውን ችግር መፍትሄ ለመስጠት ጥልቅ ተሃድሶ መካሄዱ ነበር፡፡

መንግሥት በተደጋጋሚ ሙስና የስርዓቱና የመንግሥቱ አደጋ መሆኑን በይፋ በመግለፅ ችግሩን ለማስወገድ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ራሱን እንዲፈትሽ የመወያያ መድረኮችን በማመቻቸት የተደበቁና ለህብረተሰቡ ጠንቅ የሆኑ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ይፋ እንዲወጡ አድርጓል፡፡ ይህም ሆኖ የመልካም አስተዳደር ችግሮቹ ከመቀረፍ ይልቅ እየረቀቁና ስር እየሰደዱ መምጣታቸው በገሃድ እየታየ ነው። ከመልካም አስተዳደር ችግሮች አንዱና ዋናው የሙስናና የመልካም አስተዳደር ግድፈት መንሰራፋት ሲሆን፤ ሙስና በተንሰራፋበት ሁኔታ ልማትን፤ ብልሹ አሠራር በሰፈነበት ደግሞ መልካም አስተዳደርን ማስፈን አዳጋች ነው።

በተለያየ ጊዜ በሙስና ላይ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በሀገራችን ያለው የሙስና መጠን ከሌላው ጊዜ እየተሻሻለ እንዳልሆነና እንዲያውም እየጨመረ እንዳለ እየተገለፀ ነው፡፡ መንግሥት የችግሩን አደገኛነት በመገንዘብ ግልፅነት እንዲሰፍን የተለያዩ የአሠራር ስርዓቶችን ቢከተልም፤ የሂስና ግለሂስ መድረኮችን ቢያዘጋጅም ለመልካም አስተዳደር ችግሮቹ ግን ቁርጥ ያለ መፍትሄ ሊገኝ አልቻለም፡፡ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣን አንስቶ በየደረጃው ባሉ የሥራ እርከኖች በሙስናና በኪራይ ሰብሳቢነት የመዘፈቅ ሁኔታ ጎልቶ እየታየ ነው፡፡

በዚህ ሰሞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር ከሙስና ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር በዋሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎችና ግለሰቦች ዙሪያ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል። ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ደላሎች እና ነጋዴዎች ያሉበት 34 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም በመግለጫቸው ተናግረዋል።

ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉባቸው የመንግሥት ተቋማትም የፌዴራል እና የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፣ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ የገንዘብና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መሆናቸው ተገልጿል።ተጠርጣሪዎቹ በቢሊየን የሚቆጠር የመንግሥት ብርን በመመዝበር ለአገሪቱና ለህብረተሰቡ ጥቅም ይውል የነበረውን ሀብት ለግል ጥቅማቸው በማዋላቸው አገሪቱንና ህዝቡን በድለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ባለፈው ሳምንት በደቡብ ክልል ባሉ የፍትህ አካላት ላይ በተካሄደ ግምገማ በፍርድ አሰጣጥ ሂደት ፍርድ ያዛቡ ፣ ጉቦ የተቀበሉና ተገልጋዮችን ያጉላሉ ተለይተው ከሥራቸው እንደተወገዱ ተገልጿል፡፡

ባለፉት ዓመታትም በገቢዎችና ጉምሩክ መሥሪያ ቤት በሃላፊነት የተቀመጡ ግለሰቦች በአይነት ከዘረፉት የአገሪቱና የህዝብ ንብረት ሌላ በአገር ውስጥና በውጭ ጥሬ ገንዘብ በሻንጣና በማዳበሪያ በቤታቸው እስከ ማከማቸትና በጓሮአቸው እስከመቅበር ደርሰው በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በሙስና ሊዘረፍ የሚችለው በመቶ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ሀብት ለምናልመው ዕድገት ቢውል የአገሪቱን ልማት አፋጥኖ፣ ሥራ አጥነትን ለማስወገድ ለሚደረገው ርብርብ የበኩሉን አስተዋፅዎ ያደርጋል፡፡

በአገራችን ከፍርድ ቤቶች፣ ከፖሊስና ከመንግሥት አስተዳደር መሥሪያ ቤቶች ውጪ መልካም አስተዳደርን ማሰብ ወይም ስለ መልካም አስተዳደር ማውራት ጨርሶ አይቻልም፡፡ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ሙስና ተንሠራፍቷል ማለት ደግሞ ብልሹ አስተዳደር በመስፈኑ አገሪቱና ህዝቦቿ አደጋ ውስጥ ናቸው ማለት ነው፡፡

መንግስትም ሙስና በሀገሪቱ ላይ ያንዣበበ ከፍተኛ አደጋ መሆኑን ማመኑ በጐ ነገር ሆኖ ችግሩን ለማስወገድ መናገር ብቻ ሳይሆን ከንግግር በላይም ልክ እንደ ሰሞኑ ተጨባጭ እርምጃ በተከታታይ መውሰድን ይጠይቃል፡

ደላሎችና የግል ባለሃብቶች የመንግሥትን ስልጣን ከያዙት ጥቂት ሃላፊዎች ጋር በፈጠሩት የአብረን እንብላ ውል ብዙዎች ከተራ ሠራተኛነት ወደ ሚሊዬነርነት፤ ከአነስተኛ ተቀጣሪነት ወደ ታላቅ የፋብሪካ ባለቤትነት መቀየራቸው፤ በአጠቃላይ ካለድካምና እንግልት ወደ ከፍተኛ የሀብት ማማ መውጣታቸው በጉልህ እየታየ ነው፡፡

የእነዚህ ግለሰቦች ካለ ድካማቸው የሃብት ባለቤት መሆን ከሌብነት ንፁህ የሆኑ ዜጐችን ተስፋ የሚያስቆርጥ፣በአገሪቱ የወደፊት ዕድገቷና ህልውናዋ ላይ ደግሞ ከፍተኛ አደጋ የሚጋርጥ ሆኖ እየታየ ነው፡፡

«ይህንን አደጋ ለማስወገድ መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉት እርምጃዎች ጊዜያዊ ናቸው፤ ነገ ደግሞ ይተወዋል፤ ስለዚህም ሙስና ፈፅመው ከቦታቸው በተነሱት ቦታ የሚተኩት አዲስ በሊታዎች ይሆናሉ፤» የሚሉ ቢኖሩም እንኳ፤ በየትኛውም ስፍራ የሚመደቡ ሹመኞች ለሚፈፅሙት ጥፋት በጊዜውና በቦታው ተገቢውን ክትትል በማድረግ ወቅታዊ እርማት ማድረግ ተገቢ ነውና በአገርና በህዝብ ላይ ለሚያደርሱት በደል የመንግሥት ቸልተኛነት ሊኖር አይገባም፤ የአብረን እንብላ ውልም ሊቋረጥ ይገባል!

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።