የፀረ-ሙስና ትግሉ የሚሳካው ተቀናጅቶ በመሥራት ነው!

ግንቦት 1993 በሚኒስትሮች ምክር ቤት እውቅና ተሰጥቶት ወደሥራ የገባው የፌደራል የሥነምግባርና  የፀረ ሙስና ኮሚሽን «በ2017 ሙስና እና ብልሹ አሠራር ለልማትና መልካም አስተዳደር እንቅፋት ከማይሆኑበት ደረጃ ላይ በማድረስ በዓለም ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ከሆኑ የጸረ ሙስና ተቋማት አንዱ ሆኖ መገኘት» የሚል  ራዕይ አንግቦ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

ኮሚሽኑ በመጠናቀቅ ላይ ባለው ዓመት መጀመሪያ አካባቢ በ250 የመንግሥት ተቋማት የሙስና መከላከል ስትራቴጂን ተግባራዊ ለማድረግ በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም አሳውቆ ነበር። ይሁን እንጂ ከሙስና ባህሪ ተለዋዋጭነት የተነሳ የቅንጅት ሥራው ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ሆኖበታል። ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶችን ጨምሮ የመንግሥት ተቋማት ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል የሚያስችላቸውን የሙስና መከላከል ስትራቴጂ እቅድ አዘጋጅተው ወደሥራ እንዲገቡ ቢደረግም፤  ቅንጅቱ ከወረቀት አልፎ በተግባር የሚጨበጥ ሥራ ሲሰራበት አልተስተዋልም።

ሙስናን ለመከላከል በሚዘጋጀው የስትራቴጂ እቅዱ ውስጥም በዋናነት ለሙስና መከሰት፣ መገለጫና ስጋት የሆኑ ዘርፎች ከነመገለጫቸው እንዲለዩ፤ እንዲሁም የስጋት ደረጃና የመከላከል ስልቶች እንዲካተቱ ቢደረጉም የሙስና መገለጫ ውስብስብና ተገማች ባለመሆኑ አንድ ቦታ ሲቋጥሩት ሌላ ቦታ እየተፈታ ነገሩን ሁሉ «ጠብ ሲል ስደፍን... ጠብ ሲል ስደፍን» ዓይነት አድርጎታል።

ኮሚሽኑ አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር የሥነ-ምግባርና የፀረሙስና ትምህርትና ሥልጠናን በማስፋፋት፣ በፀረ ሙስና ትግል የተደራጀ የሕዝብ ንቅናቄ በመፍጠር፣ የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት ሀብት በመመዝገብና በማሳወቅ፣ ሙስናና ብልሹ አሠራርን በመከላከል፣ የመንግሥትና የሕዝባዊ ድርጅቶች አሠራሮች ላይ ግልፅነትና ተጠያቂነትን እንዲሰፍን ግንዛቤ መፍጠር ይጠበቅበታል። ይሁን እንጂ በእስካሁኑ ሂደቱ ሙስናን የሚፀየፍ ትውልድ ከማፈራት አንፃር በተጨባጭ የሚመዘን ለውጥ ለማስመዝገብ አላስቻለውም። በአመለካከት ላይ የሚሰራው ግንዛቤ የማስረፅ ተግባር  በውጤት ላይ የተመሠረተ ባለመሆኑ የሚፈለገውን ያህል ለውጥ እንዳይመዘገብ አድርጎታል።

ሙስናን መከላከል የሚቻለው አመለካከት ላይ በሚሰራ እውቀት መሆኑን ልብ ማለት ይገባል። ምክንያቱም ያለፉት ተሞክሯችን የሚያሳዩት ይህንኑ ነውና «ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋልን» ዓይነት ከንቱ ተረት በልቦናው ይዞ ወደ ሥራው ዓለም መዝለቅና  ሥልጣን መቆናጠጥ የሚያስከፍለው ዋጋ ከባድ መሆኑን አይተናል። በመሆኑም ሙስናን የሚፀየፍ ትውልድ ለመፍጠርም በየደረጃው ያሉ የትምህርት ተቋማት ከመቼውም ጊዜ በላይ  ትኩረት ሰጥተው መስራት ይገባቸዋል።

መንግሥት የፀረ ሙስና ትግሉን ለማጠናከር የሚያግዙ ተቋማት እንዲጠናከሩ ብዙ ርቀት ተጉዟል። በተለይም በኮንስትራክሽን ዘርፍ ብልሹ አሠራርን ለመቅረፍ የሚያስችል «የኮንስትራክሽን ሴክተር ትራንስፓረንሲ ኢኒሼቲቭ»  ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱም ይታወቃል። ይህ ተቋም በተጨባጭ በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ የሙስና አዝማሚያዎችን ከመጠቆም አንፃር ይፋ ያደረገው ነገር ባይኖርም፤ በመንግሥት የሚከናወኑ ግንባታዎች ያሉባቸውን ችግሮች፤ በእቅዱ መሠረት ስለመከናወናቸውና ስለበጀት አጠቃቀማቸው በየጊዜው ሪፖርት እንዲያደርግ ኃላፊነት ተጥሎበታል። ይሁን እንጂ  ተቀናጅቶ ባለመሰራቱ የፀረ ሙስና ትግሉን በሚፈለገው ደረጃ እያገዘው ነው ለማለት አያስደፍርም።

የዋና ኦዲተር በየዓመቱ በሚያቀርበው ሪፖርት በተጨባጭ የተስተዋሉ የአሠራር ክፍተቶችንና የገንዘብ ጉድለቶችን ይፋ ማድረጉን አላስተጓጎለም። የሪፖርቱን ውጤት ተከትሎ አስቸኳይ እርምጃ ሲወሰድ አይስተዋልም። የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲም ቢሆን ለሙስና የሚያጋልጡ ግዥዎችን በመቆጣጠር  በሀገሪቱ ግልፅነትና የሙያ ሥነምግባርን የተላበሰ የመንግሥት ግዥ አፈፃፀምን ለማስፈን የተቋቋመ ነው።  ይሁን እንጂ አሁንም ግልፅነትን ያልተላበሱ ትላልቅ ግዥዎች እየተፈፀሙ የሀገር ሀብት እየባከነ ነው። በአጠቃላይ  በሁሉም  ዘርፍ የሚታዩ ለሙስና አጋላጭ የሆኑ አሠራሮችን ለመቀነስ የሚያስችል የጋራ አሠራር ባለመፈጠሩ ሙስና ሊገታ ቀርቶ ሲቀንስም ማየት አልተቻለም።

 መንግሥት በጥልቅ ተሃድሶ አሠራሩን ከፈተሸ ወዲህ  የፀረ ሙስና ትግሉን አጠናክሮ መቀጠሉ አይካድም።  በሙስና የተጠረጠሩ የሥራ ኃላፊዎችን ለሕግ እያቀረበ መሆኑም አሰየው የሚያስብል ነው። የሰሞኑ መነጋገሪያ የሆነው በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ባለሀብቶችና ደላሎች እስካሁን ባለው መረጃ ቁጥራቸው 51 ደርሷል። ተጠርጣሪዎች ለተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የፕሮጀክት ሥራ የወጣን ከ1ነጥብ15 ቢሊዮን ብር በላይ መንግሥትን ማሳጣታቸውም ይፋ ተደርጓል። ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነትን ተሸክመው የራሳቸውን ጥቅም ያስቀደሙ አመራሮች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው በራሱ የመንግሥትን ቁርጠኛ አቋም አመላካች ነው።

 የሕግ የበላይነትን ማስከበር፤ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን የማስጠበቅ ሂደት የህልውና ጉዳይ በመሆኑ የፀረ ሙስና ትግሉ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል፡፡ የሚስተዋሉ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቀነስ የፌዴራልና የክልል የፀረ-ሙስና ተቋማት ሕዝቡን የትግሉ አጋር በማድረግ ተቀናጅተው መስራትም  ይገባቸዋል።

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።