ክብር ለሰንደቅ ዓላማችን

 

የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአንድም ይሁን በሌላ ለሀገራቸው እና ለሰንደቅ ዓላማቸው ቀናኢ ናቸው፡፡ ለእዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ለነፃነታቸው ለሀገራቸው ሉዓላዊነት የከፈሉት መስዋዕትነት ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ባለፉት 26 ዓመታትም አንገታቸውን ያስደፋቸውን ድህነት በመግታት ኩራታቸውን ከፍ ለማድረግ እያደረጉት ያለው ርብርብም የቅርብ ጊዜ ማሳያ ነው፡፡ ስለሆነም የህዝቦች የኩራት ምንጭ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ማክበርና ማስከበር ከሁሉም ዜጎች ይጠበቃል።

ሰንደቅ ዓላማ የአገር እና የህዝብ ምልክት ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ምልክት በመሆኑ ከሰንደቅ ዓላማው ፊት በቆመ ቁጥር የሀገሩ ምስል የማይከሰትበት ሰው የለም፡፡ ከዓለም ታሪክ እንደምንረዳው ሀገራትና ዜጎች ከቅኝ ግዛት ተፅዕኖ ሲላቀቁ መጀመሪያ ከፍ አድርገው የሚያሳዩት ሰንደቅ ዓላማቸውን ነው ፡፡ ህዝቦችና አገራት በሰላም አደባባይም ሆነ በጦር ሜዳ ውሎ ለድል ሲበቁ ቅድሚያ የሚሰቅሉት ሰንደቅ ዓላማቸውን ነው፡፡ ይህን በማድረግም ፍቅርና ክብራቸውን እጅግ ከፍ ባለ መልኩ ለሰንደቅ ዓላማቸው ይገልፃሉ፡፡ ህዝቦች በአንድ ሰንደቅ ዓላማ ስር በመሰባሰብም ሉዓላዊነታቸውን ለዓለም ያሳያሉ፡፡

በኢ...ሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 3 ስር የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሃል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ በመሐሉ ብሔራዊ አርማ እንደሚኖረው ደንግጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጠው ብሔራዊ አርማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች እና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ መሆኑን ይገልፃል፡፡ ስለሆነም ሰንደቅ ዓላማችን በህገ መንግሥታችን እውቅ እና ጥበቃ ያለው ነው።

በሀገራችን ሰንደቅ ዓላማ መሃል ላይ የሚገኘው ብሄራዊ ዓርማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች እና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ መሆኑ እየታወቀ ብዝህነትን በሚፃረሩ ኃይሎች ዓርማ የሌለው ሰንደቅ ዓላማ ጥቅም ላይ ሲውል ይስተዋላል። ይህ ፀረ ህገ መንግሥት ተግባር በመሆኑ መታረም አለበት። ዓርማውን መቃወም ማለት የህዝቦችንና የሃይማኖት እኩልነትን መቃወም ነው። ስለሆነም ፀረ እኩልነት የሆነ ኃይልን በትዕግስት ብቻ ማለፍ ተገቢ አይሆንም። ህጋዊ እርምጃ መውሰድም ይገባል። ሰንደቅ ዓለማውም ህገ መንግሥቱም መከበር አለበት። ክብር ለሰንደቅ ዓላማችን።

በሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/2001 አንቀፅ 12 እና ተከታዮቹ መሰረት፤ የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ ከላይ እስከታች ባሉ የክልል የስልጣን አካላት ጽህፈት ቤት፣ በመከላከያ፣ ፖሊስና ጠረፍ ጥበቃ ተቋማት፣ በሪፐብሊኩ ኤምባሲዎች፣ በሀገሪቱ የንግድ መርከቦችና ጀልባዎች እንዲሁም በአምባሳደሮች መኖሪያ ቤት ሰንደቅ ዓላማ በየቀኑ ይሰቀላል፡፡ ተሰቅሎ የሚውለበለበው ሰንደቅ ዓላማ ያላረጀ፣ ያልተቀደደና ቀለማቱ ያልፈዘዙ መሆን አለበት፡፡ ሰንደቅ ዓላማው በየቀኑ ከጠዋቱ 1200ሰዓት ተሰቅሎ ከምሸቱ 1200ሰዓት መውረድ አለበት ይላል፡፡ ይህም ህግ ስለሆነ መተግበር አለበት።

የግልም ሆነ የመንግሥት ተቋማት ለሰንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር በመስጠት ጭምር ጠዋት ሰቅለው ማታ ማውረድ አለባቸው። ይህ የሰንደቅ ዓላማ ክብር አንዱ መገለጫ ነው። በተግባር ግን አልፎ አልፎ ጥቂት ተቋማት ለሰንደቅ ዓላማ ተገቢውን ክብር በማይሰጥ መልኩ ሲፈፅሙ ይስተዋላሉ። ተሰቅሎ ሳይወርድ ለቀናት የሚቆይበት፣ የተቀዳደደ ሰንደቅ ዓላማ ሲውለበለብ የምናይበት አጋጣሚ አለ። ይህ መስተካከል ያለበት ጉዳይ ነው። እርምጃ እንዲወስድ ኃላፊነት የተሰጠው አካልም ኃላፊነቱን መወጣት አለበት።

የሰንደቅ ዓላማ ክብር መገለጫ በሰዓቱ የመስቀልና ማውረዱ ብሎም በዚህ ወቅት እንደየተቋሙ ሁኔታ ተገቢውን ሥነ ሥርዓት ማከናወን ነው፡፡ ክብር ከራስ ስለሚጀምርም በዚህ መልኩ አክብሮም ሌሎች እንዲያከብሩት ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ ወጣቱም ሰንደቅ ዓላማ ለአገራችን ምንድን ነው፣ የሚለውን አውቆ ራሱን ሊመለከትበት ይገባል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ዜጋ ለሰንደቅ ዓላማ ክብር መትጋት አለበት። የውዴታ ግዴታም ነው። ሰንደቅ ዓላማ የሉዓላዊነት መገለጫም ነውና። ክብር ለሰንደቅ ዓላማችን።

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።