የምክር ቤቱ አባላት ለስኬታማነት ቆርጠው መነሳት ይገባቸዋል!

 

ኢትዮጵያ በማያቋርጥ የዕድገት ግስጋሴ ላይ ትገኛለች። ይህ ግስጋሴዋ እውን ይሆን ዘንድ ደግሞ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነች ቢሆንም የሚቀሯትና ማሳካት የሚገባት ሥራዎች በርካታ ናቸው፤ እነዚህን እውን ለማድረግም ሁሉም የድርሻውን ማበርከት ይኖርበታል። ከዚህ አንጻርም ባለፉት ዓመታት የተከናወኑትን ስኬታማ ሥራዎችና መልካም ተሞክሮዎች የሚሰፉበት እንዲሁም አገሪቱን አጋጥመዋት የነበሩትን ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ዳግመኛ እንዳይከሰቱ በሚከላከሉ ሁኔታ ላይ በማተኮር የህዝቦች የላቀ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት ግልጽና ሰፊ ወይይት በማድረግ ለተግባራዊነቱ በትኩረት መስራት ከኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚጠበቅ ይሆናል።

2010 .ም የመጀመሪያው ሚሊኒየም 10 ዓመታት የተገባደዱበት፤ አዲስ ተስፋ የተሰነቀበት፤ በአገሪቱ ለዘመናት ተንሰራፍቶ የነበረው ድህነት ቀስ በቀስ እየተቀረፈ የመጣበትና ተከታታይና ፈጣን ዕድገት እየተመዘገበ ያለበት ዓመት በመሆኑ በዚህ ዓመት ይህ መልካም ተሞክሮ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ በኩል ምክር ቤቱ ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት።

ከፍተኛውን የህዝብ አደራ የተሸከመው ይህ ምክር ቤት የተጀመረውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሀድሶ በማስቀጠል እንዲሁም በአማካይ የተመዘገበውን የሁለት አሀዝ ዕድገት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር በኩል የሚኖረው ሚና የጎላ ከመሆኑ አንጻርም በሚያወጣቸው ህጎችና ደምቦች እንዲሁም በሚያጸድቃቸው የተለያዩ አዋጆች ላይ ትኩረት በማድረግ የተጠናከረ የውይይት ባህልን ማዳበር ይኖርበታል።

አምስተኛው የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን መጀመርን ምክንያት በማድረግ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ፡- « አገሪቱ ከነበረችበት ገናና የስልጣኔ ማማ እየወረደችና እያሽቆለቆለች ቆይታ በሁለተኛው ሚሊኒየም መገባደጃ አካባቢ በውድ ልጆቿ መራር መስዋዕትነት ወደ አዲስ የህዳሴ ጉዞ ከገባች ሩብ ምዕተ ዓመትን አስቆጥራለች። ይህንን የተሀድሶ ጉዞዋንም ማስቀጠል የሚቻለው በተለይም ምክር ቤቱ ጠንካራ ሲሆን ነው፡፡ » ብለዋል።

«አገሪቱ በህዳሴ ጉዞዋ በአማካይ 10 ነጥብ 5 በመቶ ዕድገትን እያስመዘገበች መምጣቷ በዓለም ፈጣን ዕድገት ካስመዘገቡ አገራት ተርታ የሚያሰልፋት ከመሆኑም በላይ ትልቅ ድል በመሆኑ ይህንን ሁኔታ አስቀጥለን መሄድ ከቻልን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ እንደምንሰለፍ እርግጠኛ መሆን ይቻላል» በማለትም አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ይህ እንዲሆንም በህዝብ ትልቅ አደራ የተሰጠው ምክር ቤት የሚያወጣቸው የትኛውም ፖሊሲዎች የአገሪቱን ዕድገት ማዕከል ያደረጉና የህዝቡን ፍላጎት መሰረት የተከተሉ መሆን እንዳለባቸው ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ይህ በተግባር ከዋለ በርግጥም የዕድገት ግስጋሴው ምሉዕና የማይቆም ይሆናል።

ክቡር ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው በተለይም በውጭ ንግድ ላይ ያለውን ክፍተት አርሶ አደሩና ባለሀብቱ በጋራ ሊያከናውኑ የሚገባቸውን ድርሻ ከተወጡ አሁን ካለው የምርት ጭማሪ በበለጠ ማግኘት እንደሚቻልና በዘርፉ እንቅፋት የሆነውን የጥራት መጓደል እንዲሁም ማነቆ የሆነውን የአቅርቦት ችግር በማሻሻል ሥራ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አስገንዝበዋል።

እነዚህን ማነቆዎች በመፍታትም የህዳሴውን ጉዞ ማስቀጠል እንደሚገባና በ2009 .ም የተገኘውን 220 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወደ 4 መቶ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማድረስ አበክሮ መስራት እንደሚያስፈልግና ከፍተኛ ዋጋን በሚያስገኙ ሌሎች የሰብል ምርቶች ላይም ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል። በመሆኑም ይህንን ለማድረግ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የሚቆጣጠሯቸውን መስሪያ ቤቶች ከኋላ ቀር አሰራር ወደ ዘመናዊ አሰራር እንዲሸጋገሩ በማድረግ፣ ጉድለቶች ሲኖሩም በፍጥነት በማረም የማስተካከል ሥራ መስራት ይኖርባቸዋል።

በፌዴራል ሥርዓታችን ውስጥ ትልቅ ሚናን የሚጫወቱት ሁለቱ ምክር ቤቶቻችን የዓመቱን የሥራ መርሐ ግብራቸውን ዛሬ አንድ ብለው ጀምረዋልና ዘንድሮም እንደወትሮው ቀጣይ የሥራ ትኩረታቸው ለአገሪቱ ዕድገት የሚበጅ፣ ህዳሴዋን የሚያረጋግጥና ወደ ከፍታ ደረጃ የሚያደርሱ ህጎችን ማውጣትና አስፈጻሚ አካላትን መቆጣጠር በማድረግ ለሀገራዊ ህዳሴያችን መረጋገጥ አበክረው የሚሰሩበት ሊሆን ይገባል፡፡

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።