ለባንኮች ተደራሽነት በእጃችን ያሉ ሁለት አማራጮች!

 

በኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት ከተጀመረ ከመቶ ዓመት በላይ ቢያስቆጥርም ከአገሪቷ የባንክ ታሪክ አንፃር ተነስተን ስንመለከተው ግን የባንክ አብዮት ተካሄደ የምንለው ከደርግ ሥርዓት ውድቀት በኋላ ያለውን ነው። ይህ ዝም ብሎ የሚባል ሳይሆን የዘርፉን ታሪክ መለስ ብሎ ለሚመለከት በቀላሉ የሚረዳው ሀቅ ነው። ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ብቻ የባንኩ ዘርፍ አስደማሚ በሆነ ፍጥነት እያደገ መጥቷል። ይህንን የዕድገት ጉዞ ከጎረቤት አገራትም ይሁን ከተቀሩት አፍሪካውያን አገራት ጋር ስናነፃፅር ብዙም የሚያስመካ እንዳይደለ እንረዳለን። ዕድገቱ ተደራሽነትን በሚፈለገው ልክ አላረጋገጠምና።

ያም ሆኖ ታዲያ የኢትዮጵያ የባንክና የአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት የቁጠባ ሂሳብ ቁጥር 43 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ደርሷል፤ አንድ ሺህ 748 የባንክ ቅርንጫፎች ተከፍተዋል፤ የክፍያ መፈፀሚያ ነቁጦች ቁጥር 492፤ የኢ ቲ ኤም ማሽኖች ቁጥር ደግሞ ሁለት ሺህ 743 ደርሷል። የወኪል ባንክ ቁጥርም ዕድገት አሳይቶ 10 ሺህ 481 ሆኗል። በዚህ መልክ የተስፋፋው የባንክ አገልግሎት የቁጠባ መጠኑን ወደ 568 ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር አድርሶታል። የብድር መጠኑም 560 ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ደርሷል።

የአገሪቷ የባንክ አገልግሎት ከነችግሩም ቢሆን የተጠቀሰውን ያህል ዕድገት አስመዝግቧል። ይህ ዕድገት በአንድ ጀምበር የመጣ አይደለም። ይልቁንም በጥብቅ የማይክሮ ፋይናንስ ፖሊሲና አፈፃፀም እንጂ። ስለሆነም የመንግሥት ቁርጠኛ አፈፃፀምና አገር በቀል ፖሊሲ ዘርፉን እዚህ አድርሶታል። በተጓዳኝም ዕያደገ ያለው ኢኮኖሚና የህዝብ ቁጥር እጅግ የተቀላጠፈና ዘመናዊ ብሎም ተደራሽ የባንክ አገልግሎት የሚፈልግበት ደረጃ ላይ ደርሷል።

መንግሥትም ይህ ዕድገት እንዳለ ይጠቅስና ተደራሽነቱ ገና ዝቅተኛ ነው የሚል ግምግማ አለው። ተደራሽነትን ይበልጥ ለማስፋፋትም የተቀመረ ስትራቴጂን ይዞ ብቅ ብሏል። ይህ ስትራቴጂ የባንክ አገልግሎትን በብዛትና በጥራት ለማድረስ ሁነኛ መፍትሄ እንደሆነ ተገልጿል።

አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ሁለት መከራከሪያዎችን ይዘው ብቅ ብለዋል። በአነድ ወገን ያሉቱ አሁን ያለንበት ዘመን ቴክኖሎጂን በብዛትና በጥራት የሚፈልግ መሆኑን በመጥቀስ ቅርንጫፎችን ከማስፋፋት ይልቅ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶችን ማስፋፋት ይበጃል ይላሉ። ይህንን ሀሳብ የሚያነሱ ምሁራን መከራከሪያ ነጥባቸው አሁን በአገሪቱ ያለው አብዛኛው ህዝብ ወጣት እንደመሆኑ ለቴክኖሎጂ ቅርብ ነው፤ ቴክኖሎጂው ደግሞ በብዛትና በጥራት እየተስፋፋ መጥቷል፤ ስለሆነም የግድ ወደ ባንኮች ቅርንጫፍ መሄድ ስለማይገባ ሁሉም በየቤቱ አገልግሎቱን የሚያገኝበትን ዕድል መፍጠር ይቻላል የሚል ነው።

ዛሬ እስከ 50 ሚሊዮን የሚደርስ የሞባይል ተጠቃሚ አለ። ኢትዮ ቴሌኮም ደግሞ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የተጠቃሚውን ቁጥር 100 ሚሊዮን አደርሳለሁ ብሎ ታትሮ እየሠራ ነው። ስለሆነም ይህንን ያህል ህዝብ በቀላሉ ማግኘት የሚቻለው በሞባይል ባንኪንግ ነው ይላሉ። በቅርንጫፍ ለመድረስ መሞከር አክሳሪ ባይሆንም በሚፈለገው ልክ ግን አትራፊ እንደማያደርግ ይገልፃሉ። የሞባይል፣ የኢንተርኔትና የወኪል የባንክ አገልግሎቶች በመስጠት ብቻ 70 እና 80 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቷን ህዝብ ለባንክ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ይቻላልም ሲሉ ይከራከራሉ።

በሌላ ወገን ደግሞ ከቴክኖሎጂው ይልቅ ቅርንጫፎችን ማስፋፋት አዋጭ ነው ብለው የሚከራከሩ አልታጡም። የእነዚህ ምሁራን እይታ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የአገሪቷ ህዝብ የሚኖረው በገጠር እንደመሆኑና ጥቂት የማይባለው ጎልማሳም ለቴክኖሎጂ ባዳ በመሆኑ አዋጭው መንገድ ቅርንጫፍን ማስፋፋት ነው የሚል ነው። ይህ ማለት ግን ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋት አያዋጣም ማለት እንዳልሆነ በመግለፅም ዋናው ትኩረት መሆን ያለበት ግን ቅርንጫፎች ላይ ነው ባይ ናቸው።

ዛሬም ድረስ በሰለጠኑት አገራት ሳይቀር የባንክ ቅርንጫፎችን መክፈት እንዳለ መሆኑን በመግለፅም በኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ፊትን ወደ ቴክኖሎጂ ማዞር አዋጭም ተመራጭም አይደለም የሚል ሙያዊ አተያይ አላቸው።

የሁለቱም ወገኖች ምሁራዊ ዕይታ መንግሥት ይዞት ከመጣው ስትራቴጂ አንፃር የሚነቀፍም ሆነ የሚጣል አይደለም። ሁለቱም ያስፈልጋሉ፤ ሁለቱም ጊዜው የሚጠይቀው አማራጮች ናቸው። በዚህም ምክንያት ጭምር መንግሥት ስትራቴጂውን በዚህ አግባብ ቃኝቶ ማውጣቱ በእርግጥም ተገቢ ነው። ስለሆነም ባንኮች እንደሚገቡበት አካባቢ ተጨባጭ ሁኔታ እያዩና እየመዘኑ አዋጭ የሚሉትን አማራጭ ተግባራዊ ማድረግ ይገባቸዋል። ቴክኖሎጂው በደረሰበት መንደር የቴክኖሎጂ አማራጮችን፤ ባልደረሰበት ደግሞ ቅርንጫፎችን እያስፋፉ መሄዱ እንደ አገር ተጠቃሚ ያደርጋልና።

መንግሥትም ያሉበትን እንደ መብራትና ስልክ ያሉ የመሰረተ ልማት ሥራዎቹን በጊዜና በፍጥነት ማዳረስ አለበት። ከዚህ ጎን ለጎንም በየአምስት ዓመቱ እያንዳንዱ የንግድ ባንክ ሊደርስ የሚገባበትን ደረጃ እንደየወቅቱ እየከለሰና እያስገደደም ጭምር ዘርፉን በዋና ባለቤትነት እየተቆጣጠረ መቀጠል አለበት እንላለን።

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።