በስኬት የደመቀው ጉዞ በስኬት ይዘልቃል !

 

ለደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ምስረታ ጥንስስ የሆነው የታሪክ አጋጣሚ የተፈጠረው ከ27 ዓመታት በፊት ነበር። የታሪክ መዛግብት እንደሚያመላክቱት ለመጀመሪያ ጊዜ ደቡብን ሊወክል የሚችል አብዮታዊና ዴሞክራሲያዊ አደረጃጀት ያለው የስምጥ ሸለቆ ታጋዮች መሸጋገሪያ ማህበር ታህሳስ 1983 .ም በትግራይ ክልል ከሽሬ እንዳስላሴ ከተማ በስተደቡብ ምዕራብ አስር ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ማዕበራ በምትባል ስፍራ ተመስርቷል። ከ25 ዓመት በፊት በወርሃ መስከረም የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ግንባር (ደኢህዴን) የተመሰረተ ሲሆን፤ የግንባሩ አባል ድርጅቶች የሚመሩበትና የሚያራምዱት ዓላማ አንድ እስከሆነ ድረስ መከፋፈል እንደማይጠቅም ታምኖበት ስያሜውን በ1996 .ም ወደ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ቀይሯል።

እነሆ ያለፉትን ዓመታት በስኬት ያሳለፈው ቀጣዩንም ጉዞ ከመላው የክልሉ ህዝብና ከሌሎች አጋሮች ጋር በመሆን ብሩህ ለማድረግ እየተጋ ያለው ደኢህዴን «በስኬት የታጀበው ጉዟችን፣ ወደ ህዳሴው ማማ በሚል መሪ መልዕክት የምስረታውን 25ኛ ዓመት ሰሞኑን እያከበረ ይገኛል። ድርጅቱ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ተጠቃሽ ማህበራዊና ፖለቲካ ድሎች እንዲመዘገቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። የክልሉ ህዝቦች የልማት፣ የዴሞክራሲና የሰላም ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ ስኬትን ማጣጣሙን በተጨባጭ ማስረጃዎች አስደግፎ መናገር ይቻላል።

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል 56 ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚገኙበት ነው። የክልሉ መሪ ድርጅት ደኢህዴን እነዚህም የተለያዩ ግን የሚያቀራርባቸው የጋራ እሴት ያላቸውን ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አቀናጅቶ በመምራት ረገድ ተጠቃሽ ውጤት አስመዝግቧል። የክልሉ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ተቋዳሽ ይሆኑ ዘንድ በተሠራው ሥራ እራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ አስችሏል። በአገር አቀፍ ደረጃም ተገቢውን ውክልና እንዲያገኙ በማድረግ ህብረተሰቡ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን አስተዋጽኦ አበርክቷል። ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እንዲጎለብት የበኩሉን ሚና ተጫውቷል።

ድርጅቱ የተመዘገበውን ፖለቲካዊ ስኬት ዘላቂነት ለማረጋገጥ ቀሪ ተግባራት እንዳሉ ሳይዘነጋ አቅሙን ማጠናከር፣ የአባላቱን እንዲሁም የደጋፊውን ብዛት ማሳደግና ጥራታቸውን ማረጋገጥ አለበት። የህዝቡ ተሳትፎ በይበልጥ የሚረጋገጥበትን ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅበታል። በክልሉ ብልጭ ድርግም እያለ የሚታየውን የጠባብነት አመለካከት እንዲሁም ተግባራት ከሥራቸው ለመንቀልም የማያሰልስ ጥረት ማድረግ አቢይ ሥራ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። በተለይ ከእነዚህ ዝንባሌዎች ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ግጭቶች ምንጫቸውን በመፈተሽ ድጋሚ እንዳይከሰቱ ማድረግ የስኬቱ ቀጣይ እጣ ፈንታ ላይ ጉልህ ሚና ስለሚኖረው ጉዳዩ ለነገ ይደር የማይባል መሆኑ ሊወሰድ ይገባል። የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት እና ተግባር የድርጅቱ ቀጣይ ስኬት ላይ ጥላውን እንዳያጠላም ብርቱ ትግል ይደረግ።

ደኢህዴን በክልሉ ለተመዘገበውና እየተመዘገበ ለሚገኘው ማህበራዊ ለውጥ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። በክልሉ የትምህርትና የጤና ተደራሽነት እንዲያድግ እና በቋንቋ የመማር መብት እንዲከበር ጉልህ ሚና ተጯውቷል። በእዚህም በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንዲሁም በሁሉም ቀበሌ ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መገንባት ተችሏል። በክልሉ ከሚነገሩ ቋንቋዎች 29 የሚሆኑት በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለመማሪያነት ውለዋል። አምስት ቋንቋዎች ደግሞ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ እየተሰጡ ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅት 716 ጤና ጣቢያዎችና ስልሳ አምስት ሆስፒታሎች አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን፤ ለውጦቹም ለስኬቱ አቢይ ማስረጃ ናቸው።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በማህበራዊ አገልግሎት ዘንድ የሚጠበቀውን ጥራት የማስጠበቅ ጉዳይ በተደራሽነት ከተገኘው ስኬት እኩል እንዲሆን ጠንክሮ የመሥራት ኃላፊነት በድርጅቱ ላይ ተጥሏል። መላውን ባለድርሻ አካላት በማስተባበር «ጥራት የህልውና ጉዳይ ነው» በሚል መንፈስ ወደ ህዳሴው የሚደረገው ጉዞ በስኬት እንዲዘልቅ መትጋት ይገባል።

በክልሉ በግብርና ዘርፍ የተገኘው ለውጥ ሌላው የስኬት አብነት ነው። በ1985 .15 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ የነበረው ምርታማነት ወደ 160 ሚሊዮን ኩንታል አድጓል። በሌላም በኩል የወጣቶችንና የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ፣ ቱሪዝምን የገቢ ምንጭ በማድረግ እና በሌሎችም መስኮች በክልሉ ዘርፈ ብዙ ለውጥ መጥቷል።

የተጠቀሱት ስኬቶች የተመዘገቡት በመሪ ድርጅቱ ደኢህዴን ያላሰለሰ ትግል ነው። በቀጣይም መላውን ሰላም ወዳድ ህዝብ ከጎኑ በማድረግ፣ በአመለካከትና በተግባር ግንባር ቀደም የሆኑ አባላቱንና መላውን ህዝብ በማስተባበር ግስጋሴውን ማጠናከር ለዘላቂነቱ መሥራቱን አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅበታል።

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።