ህዝብና መንግስት ይደማመጥ!

 

ህዝብና መንግስት መተማመንና መደማመጥ አለባቸው።ህዝብና መንግስት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ መሆን ካልቻሉ ልማቱም ዕድገቱም የታሰበው ደረጃ አይደርስም።መደማመጥ ካልተቻለ የመልካም አስተዳደር ችግሩ፣ኪራይ ሰብሳቢ ከመቀነስ ይልቅ ጡንቸኛ እየሆነ ይሄዳል።ይሄ ደግሞ ህዝብን ለአመፅና ለቅራኔ ያነሳሳል።ነገር ግን መንግስት የሰራውን፣ እየሰራ ያለውን፣ወደፊት የሚሰራውን በግልፅ ለህዝቡ ባሳወቀ ቁጥር ልማቱ እንኳን ሁሉንም ህብረተሰብ በሚፈልገው ደረጃ ተጠቃሚ ባያደርግም ነገን ተስፋ በማድረግ ለቀጣዩ የልማት ስራ ይተጋል።ብልሹ አሰራሮች ሲኖሩም በጊዜው ነቅሶ እያወጣ እንዲታረሙ ይገፋፋል።መንግስትም የሚመራውን ህዝብ የሚያከብር ነውና የቀረቡለትን ቅሬታዎች በወቅቱ ይፈታል።በአጥፊዎችም ላይ የማስተማሪያ ቅጣት ይጥላል።በዚህ ጊዜ ህዝብና መንግስት መተማመናቸው እየጎለበተ ይሄዳል።በአንድ ጉዳይ ላይ አንድ አይነት ቋንቋ መነጋገር ይችላሉ።

ለዚህ ደግሞ ሁሉም መንቀሳቀስ አለበት።መደራጀት አለበት፤መሰረታዊ ጥቅሞቹን ለማስከበር መታገል አለበት።የአካባቢው አስተዳደርም ይሁን በየደረጃው ያለ አመራር ሲያጠፋ መገሰጽ መቻል አለበት፤ኪራይ ሰብሳቢነት፣ሙስና እና ብልሹ አሠራር ውስጥ ሲገባ፣ጉቦ ሲቀበል እያየ ዝም ማለት የለበትም።በአጠቃላይ አመራሩ የተስተካከለ እንዲሆን ህዝቡ ሞጋች መሆን አለበት።

ይህን ለማስተካከል በተናጠል መሮጥ አያዋጣም።ህዝቡ በተደራጀ መንገድ መንቀሳቀስ አለበት። ህዝብ ሲደራጅ የአካባቢው አስተዳደር የሚያደርጋቸው መጥፎ ዝንባሌዎችን ፊት ለፊት መታገል ሲጀምር ያ አመራር የህዝቡን መሰረታዊ ጥቅሞች እያስከበረ መሄድ ይጀምራል።የህዝቡ ትግል ሲቀዛቀዝና የተደራጀ ተሳትፎው ሲቀንስ በየደረጃው ያለ አመራር ሃይ ባይ አመራርና የሚታገለው ህዝብ ስለማይኖር ለሙስና እና ብልሹ አሠራር የተጋለጠ ይሆናል። ስለዚህ በዋነኛነት የሚያስፈልገው የተቀናጀ የህዝብ እንቅስቃሴ ነው።ይሄ ሲሆን ነው መልካም አስተዳደር የሚሰፍነው። የፌዴራል ስርዓቱ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ወደኋላ እንዳይቀለበስ ለማድረግ የሚቻለው።ስለዚህ ህዝቡ ጠንካራ ትግል ማድረግ አለበት።ይሄ የሚሆነው ደግሞ በለዘብተኝነት ሳይሆን በጠንካራ ትግል መሞረድ ሲቻል ነው።

መንግስትም ለህዝቡ ሲናገር መደመጥ አለበት።የሚሰራው የልማት ስራ የህዝብ ነው። የአገር ነው። የመንግስት ሚና የመሪነት ብቻ ነው።በተሰራው ተጠቃሚው ህዝብ ነው። የሚያድገው አገር ነው። ስለዚህ መንግስት በሚያቅዳቸው፣በሚያነሳቸው ሀሳቦች፣ በሚጠይቃቸው ሀላፊነቶች በሌሎችም ቦታዎች ህዝብ አቤት አለሁ ልማቱ የእኔ ነው ሊል ይገባል። አቤት ብሎም አፀፋውን መመለስ አለበት።

ህዝብ የተፈጥሮ ሀብቱን መንከባከብ ፣እያንዳንዱ አርሶ አደር ባለችው ማሳ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ተጠቅሞ፣የሙያተኛ ምክርን አክለው በየዓመቱ ከሚያመርቱት በእጥፍ ለማምረት መንቀሳቀስ መቻል ያስፈልጋል። አምራች ዜጋ ከሆኑና ሁሉን የሚያመርት ከሆነ የተትረፈረፈ ምርት ይመጣል። ይሄ በተገኘ ቁጥር የገቢ ምንጩ ይጨምራል።ከዛ ባሻገር ሸማቹ ህብረተሰብ በተመጣጠነ ዋጋ ምርት መግዛት ይጀምራል።ምርቱ አነስተኛ በሆነ ቁጥር ራሱ ሸማቹም አይጠቀምም።ስለሆነም ምርቱን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን ከምርቱ ጋር የተሳሰሩ ግብዓቶችን መጠቀም መቻል አለበት።ቴክኖሎጂዎችን ማላመድና መጠቀም ያስፈልጋል።የእንስሳት ሀብቱን በዘመናዊ መንገድ ማልማት ይገባል።በዚህ መንገድ ሀብት ሲጨምር፥ህዝብ የጥቅሙ ተጋሪ እየሆነ ሲሄድ የበለጠ ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓቱ እየጎለበተ የሚሄድበትን ሁኔታ ይፈጥራል።

አሁን በአንዳንድ ቦታዎች የሚታየው ግጭት በየአካባቢ ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ የማልማት ሥራ ባለመሰራቱ፤ እንዲሁም ህብረተሰቡ አንድነቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ተከታታይ የሆኑ የአስተምህሮ ሥራዎች ባለመሰራቱ የተፈጠሩ ናቸው።ይሄ በሂደት እየተስተካከለ የሚሄዱ ይሆናሉ። ይሄንን እርግጠኛ ለመሆን የተጠናከረ ስራ መስራት ከመንግስት ይጠበቃል።የፌዴራል ስርዓቱን ጥቅሞች ማስረዳት ህብረተሰቡ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው የማድረግ ስራ መስራት ያስፈልጋል።ይሄ ሲሆን መንግስትና ህዝብ ይግባባሉ ፤ይረዳዳሉ። ለኢትዮጵያ ህዳሴም አሁን ካለው በላይ ይተጋሉ።

ይህን ውጤታማ ለማድረግ በመንግስት ደረጃ የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መጠናከር አለበት።ማንኛውም በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ የሚመጣን ችግር ለመመከት ዋናው ጉዳይ የህዝብና የመንግስት መደማመጥ መኖር ነው።ስለዚህ መንግስት ከህዝቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን ያዳምጥ። አዳምጦም ፈጣን ምላሽ ይስጥ።ይሄ ከሆነ ህዝብ የሚጎረብጠው ነገር እንኳን ቢያጋጥመው ከመናገርና ከመታገል ወደ ኋላ አይልም። ህዝብና መንግስት መደማመጥ ከቻሉ ተአምር ይፈጥራሉ።ስለዚህ የህዝብና የመንግስት መደማመጥ ያስፈልጋል።

 

 

 

 

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።