በሕገ መንግሥታችን የደመቀ ሕብረ፣ ብሔራዊነታችን ለህዳሴያችን

 

ኅዳር 29 ቀን 2010 .ም አስራ ሁለተኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የአፋር ብሔራዊ ክልል መንግሥት ርዕሰ መዲና በሆነችው ሠመራ ከተማ «በሕገ መንግሥታችን የደመቀ ሕብረ፣ ብሔራዊነታችን ለህዳሴያችን» በሚል መሪ መልዕክት ይከበራል። ይህ መሪ መልዕክት ሦስት ቁልፍ ጉዳዮችን ያካተተ ነው - ሕግ መንግሥት፣ ሕብረ፣ ብሔራዊነትና ህዳሴ። የዘንድሮውን መሪ መልዕክት ለማጣጣም እነዚህን እርስ በእርስ የተሳሰሩ ጉዳዮች በቅጡ መመልከት ይገባል።

ኅዳር 29 ቀን1987 .ም የፀደቀው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የአገሪቱ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነ ሕግ ነው። ኢትዮጵያ በመጪው ዘመን እደርስበታለሁ ብላ ላቀደችው ብልፅግና ያስቀመጠችው መሪ አቅጣጫም ተደርጎ ይወሰዳል። ለእዚህም ነው በሕገ መንግሥቱ መግቢያ «የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መጪው የጋራ ዕድላችን መመስረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል፤ ጥቅማችንን፣ መብታችንና ነፃነታችንን በጋራ እና በተደጋጋፊነት ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባቱን አስፈላጊነት በማመን፤ በትግላችንና በከፈልነው መስዋዕትነት የተገኘውን ዴሞክራሲና ሠላም ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ፤ይህ ሕገ መንግሥት ከዚህ በላይ ለገለፅናቸው ዓላማዎችና ዕምነቶች ማሰሪያ እንዲሆነን እንዲወክሉን መርጠን በላክናቸው ተወካዮቻቸን አማካይነት አፅድቀነዋል» ሲሉ ቃል የገቡት።

ይህ በሕዝቦች ጥልቅ ውይይት የዳበረ እና የፀደቀ ሕገ መንግሥት የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን የዘመናት የሠላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ጥያቄዎች መልሷል። ወደፊትም ለተያዘው አቅጣጫ ገዢ የሕግ ማዕቀፍ ሆኖ ይቀጥላል። በመሆኑም ሕገ መንግሥቱ በሁሉም ዜጎች ልብ የሰረፀ የቃል ኪዳን ሰነድ እንዲሆን ግንዛቤ የመፍጠሩ ሥራ ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫ መሆን አለበት። በተለይም አገር ተረካቢ የሚባለው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል በውስጡ የተካተቱት አንቀጾች ምን አንደምታ እንዳላቸው በተገቢው መንገድ በመገንዘብ ለተያዘው የለውጥ ጉዞ መሰረት የሆነውን ሰነድ የማስከበር ሚናውን እንዲወጣ ኃላፊነት የተጣለባቸው አካላት የቤት ሥራቸውን መሥራት አለባቸው።

ሕብረ ብሔራዊነት የኢትዮጵያ መገለጫ ነው። ይህም በተለያዩ ሃይማኖቶች፣ ብሔሮች እና አመለካከቶች ይንፀባረቃል። ይሁንና የቀድሞዋ ኢትዮጵያ ይህን ሕብረ፣ ብሔራዊ የሆነ ስብጥር ለዘመናት በአግባቡ ማስተናገድ አቅቷት ኖራለች። በዚህ የተነሳ መብታቸው ያልተከበረላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ከግዳጅ አንድነት ይልቅ በጦርነት የሚገኝ ነፃነትን መርጠው ወደ ትግል ተሰማርተው ነበር። በ1983 .ም በሁሉም የአገሪቱ ውድ ልጆች የህይወት መስዋዕትነት ከተገኘው ድል በኋላ የፀደቀው ሕግ መንግሥት የአመለካከትና የሃይማኖት ነፃነትን ከማስከበሩም በላይ ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብቱን እንደተጎናፀፈ ደንግጓል። ለሁሉም የአገሪቱ የሕብረተሰብ ክፍሎች ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ዋስትናና ዕውቅና በመስጠት ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲመሰረት መሰረት ጥሏል።

የአገሪቱ ብዝሃነት ለዘመናት ከተነፈገው ዕውቅና ተላቆ በፅኑ መሰረት እንዲቆም ሕገ መንግሥቱ ቁልፍ ሚና አበርክቷል። ይህም መላው ሕብረተሰብ በሕገ መንግሥቱ ጥላ ስር በመሆን ሕብረ፣ ብሔራዊነቱ ያመጣው ልዩነት ሳያግደው ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች ተከብረው የኢትዮጵያን ህዳሴ ለማረጋገጥ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት እንዲታትር መሰረት ጥሎለታል። በእዚህም በአለፉት 26 ዓመታት በአገሪቱ ተጠቃሽ ዕድገት እንዲመዘገብ አቢይ ምክንያት ሆኗል፤ የህዳሴው ጉዞ ተጀምሯል።

በአገሪቱ በአለፉት ዓመታት በሠላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ተጨባጭ ለውጦች ቢገኙም እንዲሁ በቀላሉ የመጡ አልነበረም። በአገር ውስጥ ከሚፈጠሩት ችግሮች ባሻገር የውጭ ጥቃቶችና ተፅዕኖዎች ለውጡን ተገዳድረውታል። ይሁንና በተያዘው ትክክለኛ መስመርና በመላው ሕዝብ የላቀ ትብብር እየተመከቱ አሁን ለተገኘው ለውጥ ለመድረስ ተችሏል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሕብረ፣ ብሔራዊ አንድነታችን ባስገኘልን ትሩፋቶች ላይ የተቃጡ እክሎች መታየት ጀምረዋል።

የአንድነታችንና የህዳሴያችን ጉልበት የሆነው ሕብረ፣ ብሔራዊነታችንን እንደ ዋዛ ለመሸርሸር የሚደረጉት የጥፋት ኃይሎች ከንቱ ሙከራ በአብዛኛው ሠላም ወዳድ ሕዝብና ለውጡን በማጣጣም ላይ በሚገኘው ሕብረተሰብ በፅኑ እየተወገዘ መሰረት እንዳይኖረው ቢደረግም፤ አሁንም ከዚህም ከዚያም የሚታዩትን ግጭቶች ለማስቀረት የሕዝቦች የተባበረ ክንድ ያስፈልጋል። በተለይ አገር ተረካቢ ወጣቶች በልዩነት ውስጥ ያለውን የአንድነት አቅም ተገንዝበው የለውጥ መሣሪያ ሊያደርጉት ይገባል።

«በሕገ መንግሥታችን የደመቀ ሕብረ፣ ብሔራዊነታችን ለህዳሴያችን» ሲባል ልዩነት ውበት መሆኑን ከመቀበል በላይ የጋራ ዕሴትን በማጠናከር በአንድነት ሠርቶ ወደ ህዳሴው ለተጀመረው ጉዞ ሕገ መንግሥቱ የጣለውን ፅኑ መሰረት በመገንዘብ ነው። ስለዚህም ለብዝሃነታችን ዕውቅና በመስጠት ለህዳሴው ጉዞ መሰረት የጣለውን ሕገ መንግሥት እናክብረው፣ እናስከብረው።

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።