ጥልቅ ተሃድሶውን ተከትለው የተጀመሩ እርምጃዎች መጠናከር አለባቸው

 

በአገራችን ባለፉት 15 ዓመታት ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን ማስመዝገብ ተችሏል። ይህ ለውጥ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በየደረጃው ተጠቃሚ ያደረገ ነው። ይህን ፈጣን ዕድገት ለማስቀጠልና የዴሞክራሲ ሥርዓቱን ለማጎልበት እንዲቻል ሁሉም በየደረጃው ራሱን የሚያይበት መድረኮችን ተፈጥረው ሁሉም ራሱን የሚያይበት ዕድል ተፈጥሯል። ልማቱ ወደኋላ ሊጎትቱ የሚችሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍና በአገራችን የተጀመረውን የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለማጎልበት የሚያስችል ጥልቅ ተሃድሶ በየደረጃው ባሉት የተለያዩ አካላት ተካሂዷል።

ባለፈው ዓመት ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ፣ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮቹ፣ አባሎቹና ደጋፊዎቹ ጥልቅ ተሃድሶ አድርገዋል። ባለፉት 15 ዓመታት ፓርቲው እንደ መንግሥትና ድርጅት የተገበራቸው አሰራሮች፣ የተገኙ ውጤቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች በዝርዝርና በጥልቀት ታይተዋል። የአመራሮች ጥንካሬና ድክመት በስፋት ተፈትሸዋል። የመንግሥት ሠራተኛውም የጥልቅ ተሃድሶ መድረኮችን ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ባለው አደረጃጀት አካሂዶ ያለበትን ክፍተት ለይቷል። በተመሳሳይ ህብረተሰቡም የተሃድሶ መድረኮችን አካሂዷል። ይህ ለአገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት መጎልበት፣ ለመልካም አስተዳደር መስፈን የሚኖረው ሚና ጉልህ መሆኑ አይካድም።በየደረጃው በተካሄዱ የጥልቅ ተሃድሶ መድረኮች ለስልጣን ያለ የተዛባ አተያይ የወለደው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ዋና ችግር መሆኑ ተለይቷል።የትግሉ ማእከል ይኸው ችግር ለመፍታት መሆኑንም አቅጣጫ ተቀምጧል።

የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ የሚሸነፈው ልማታዊ የፖለቲካ-ኢኮኖሚ በመፍጠር እንደሆነ ይታመናል። የኪራይ ሰብሳቢነትን ለማስወገድ የሚደረገው ትግልም ዓመታትን የሚጠይቅ መሆኑን አይካድም። በአሁኑ ወቅት መወሰድ በጀመሩት እርምጃዎች በገጠር እና በከተሞች መሻሻሎች እየታዩ ነው። ይሁን እንጂ አሁንም ልማታዊ ፖለቲካ-ኢኮኖሚ በተለይ በከተሞች የበላይነት ያገኘበት ሁኔታ በሚፈለገው ደረጃ አልተፈጠረም። የተተኪው አመራር ፀረ የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ-ኢኮኖሚ ትግል ፈታኝ ያደርገዋል። ስለዚህ የኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካ -ኢኮኖሚ የበላይነት ባገኘበት ሁኔታ ኃላፊነቱን የሚወጣው አዲሱ አመራር ምን ያህል ከባድ ኃላፊነት የተሸከመ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

የጥልቅ ተሃድሶውን ተከትሎ ከአለፈው ዓመት ጀምሮ አመራሩን ለማስተካከል በተወሰዱት እርምጃዎች እና በጥልቅ ተሃድሶ ሕዝባዊ መድረኮች የተወሰኑ ችግሮች መፈታት ጀምረዋል።በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ከማንነት እንዲሁም ከወሰን ማካለል ጋር ተያይዘው የግጭት መንስኤ የነበሩት መፍትሄ እያገኙ ነው። አሁንም ግን ከፍተኛ የህዝብን እርካታ ማረጋገጥ በሚቻልበት ደረጃ ላይ አልተደረሰም፡፡ ስለዚህ የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄው በላቀ ህዝባዊ ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች ለመፍታት አመራሩ የተተነተነ ምላሽ የመስጠት ብቃቱም አብሮ ማደግ ይገባዋል። ሙስናን፣ አድሏዊ አሰራርን፣ ያልተገባ ጥቅም ፈላጊነትን፣ የጥቅም ሰንሰለትን በየጊዜው እየበጣጠሱ መጓዝን ይጠበቃል፡፡ በድርጅቱም ሆነ በመንግሥት የሥራ ኃላፊነቶች ውስጥ ያሉ ተግዳሮቶችን በአግባቡ ተንትኖ በመረዳት ችግሩን ዘላቂነት ባለው መንገድ ለመፍታት ጥረት ማድረግ ይገባል።

መንግሥት የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉን እያካሄደ ነው፡፡ ስለዚህ፤ መንግሥት ራሱን ከችግር አጽድቶ የህዝቡን እንባ ለማበስ ቁርጠኛ ቢሆንም፤ በተጨባጭ የሚያደርገው እንቅስቃሴ አርኪ መሆን አልቻለም፡፡ የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል መጀመር ያስደነገጣቸው ቡድኖች እና የሥርዓቱ ባላንጣዎች የህዝቡን አጀንዳ ነጥቀው የጥያቄውን ውል እያጠፉት ይገኛሉ። የህዝቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ከሰላማዊ የተቃውሞ ሂደት ወጥቶ የፀጥታ ሥጋት እንዲሆን እንቅልፍ አጥተው እየተረባረቡ ናቸው፡፡

መንግሥት መስተካከል የሚገባውን ነገር ለማስተካከል ጥረት እያደረገ ከህዝብ ጋር መምከር ሲጀምር፤ የተለያዩ ኃይሎች አጀንዳውን ሰርቀው በየአቅጣጫው እየጎተቱ፤ ችግሩን ከፌዴራል ሥርዓቱ ጋር በማያያዝ እና ብሔረሰባዊ ቅርጽ በማላበስ የፌዴራል አወቃቀሩን ማውገዝ ይዘዋል፡፡ ይህ ደግሞ ተገቢነት የሌለው በመሆኑ የተጀመሩት ጥረቶች የህዝቡን ጥቅም ከማስከበር አንፃር መቃኘት ስላለባቸው ህዝባዊ ውይይቶች ተጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል።

በሌላ በኩል፤ በህዝብ ብሶት ግሎ የተጀመረው የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል እንደ ደራሽ ጎርፍ ጠራርጎ ሊወስዳቸው መሆኑን የተረዱት ኪራይ ሰብሳቢዎች ፤ በየጊዜው የሚከሰተው ሁከት ከመጣባቸው አደጋ የማምለጥ ዕድል እንደሚሰጣቸው በማሰብ ጉዳዩን በማቀጣጠል ተሳታፊ እየሆኑ ይታያሉ፡፡ ይህን አካሄድ መንግሥት በሚገባ ተረድቶታል። በመሆኑም ከእያንዳንዱ ችግሮች በስተጀርባ ሆነው ችግሮቹን የሚያባብሱና የሚያቀጣጥሉ ወገኖችን አደብ እንዲገዙ ሊያደርጋቸው ይገባል።

ከጥልቅ ተሃድሶ እርምጃዎች በዘለለ የመንግሥት መዋቅራዊ አሰራርም ሊጠና ይገባዋል። የመንግሥት መዋቅርን ተጠቅሞ ያለአግባብ በስልጣኑ የሚጠቀም ፈጻሚ ተበራክቷል። የችግሮቹ ምክንያት ሲቃኝ የተጠያቂነት ስርዓት አለመጠናከሩን ያሳያል። መንግሥት በጥልቅ ተሃድሶ ግምገማው ባገኛቸው የመልካም አስተዳደር ጥሰቶችና ስልጣንን ካለ አግባብ በመጠቀም ላይ በነበሩ አመራሮችና ፈፃሚዎች ላይ እርምጃ መውሰዱ እሰየው የሚያስብል መሆኑ አይካድም። ግን ሰዎችን በማሰር ብቻ የሚቋጭ መሆን የለበትም። ሰዎችን የሚያስራቸውና ከስልጣናቸው የሚያስወግዳቸው ቋሚ የአሰራር ሥርዓት ሲኖር ነው። በመሆኑም አስፈጻሚው አካል ተጠያቂ መሆኑን የሚያጠናክር ተቋማዊ አሰራር ማጠናከር ያስፈልጋል። በመሆኑም መንግሥት በአጥፊዎች ላይ መውሰድ የጀመረውን እርምጃ ተቋማዊና ቀጣይነት ባለው መልኩ ማከናወን ይኖርበታል።

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።