እኛ ነን!

 

ኢትዮጵያ በታሪኳ ብዙ ውጣ ውረዶችን ወጥታለች፤ ወርዳለች። ወድቃለች፤ ተነስታለች። አዝናለች ተደስታለች። የእርስ በእርስ ጦርነት ያደረሰባት ድቀትም ቢሆን ዛሬም ድረስ በታሪኳ ገዝፎ ይታያል። ከነገስታቱ ዘመን ጀምሮ አንዱ ሌላውን ጥሎ ለማለፍ የተደረጉ ግጭቶች አገሪቷን ወደፊት ሳይሆን ወደኋላ ሲጎትታት ኖሯል። ይሄ እንደ አገር የምናዝንበት ታሪካችን ነው። ዛሬም ድረስ በቀደመው ታሪክ መግባባት ተስኖን በውስጥም በውጭም ሆነን ጎራ ላይተን የምንወቃቀሰው ማንም ሳይሆን እኛ ነን።

አንዱ የግዛት መስፋፋት የሚለውን ግጭት ሌላው ወረራ እያለ፤ አንዱ ማስገበር የሚለውን የግጭት መንስኤ ሌላው ዝርፊያ እያለ እየሰየመ እነሆ በዚህ ዘመን ላይ ሆነን እንኳን የዚያ ዘመን ታሪካችን ሳያግባባን እንዳለን አለን። ይሄ የማንም ታሪክ አይደለም የእኛ እንጂ። ከነገስታቱ ዘመን በፊትም ይሁን በኋላ በመጡ መንግስታት አንድ አገር፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ፣ አንድ በሚሉ ብዙ የአንድ ቅኝቶች አንድ የሆንን መስሎን አንድ ሳንሆን በተዛባ ግንኙነት የኖርነው አሁንም እኛ ነን።

ይሄ አገዛዝ ይብቃ ብለን ለ17 አመታት መራር ትግል አድርገን መራር መስዋዕትነት በከፈሉ የአገራችን የቁርጥ ቀን ልጆች ላብና ደም ህገ መንግስት የፃፍን ታሪክም ያጻፍን እኛ ነን። የግፍ አገዛዙን መሸከም ታክቶን መሳሪያ አንግበን በተለይም ለብዙሐነታችን እንቅፋት የነበረውን ስርዓት ታግለን ያስወገድን፤ የትግሉ ውጤትን እያጣጣምን ያለን፤ ተወስዶብን የነበረውን ነጻነት ያስመለስን፤ ተነጥቀን የነበረውን ማንነታችንንም ህገ መንግስታችን ላይ በሰማዕታት ደም ያጻፍን ማንም ሳይሆን እኛው ነን።

የሚላስ የሚቀመስ አጥተን በረሃብ አለንጋ የተገረፍን፤ ምፅዋዕት ፍለጋ አደባባይ የወጣን፤ ዓለም ስለ ረሀባችን የዘመረልንና የለመነልን እኛ እንጂ ማንም አይደለም። በተፈጥሮ ሀብት ብዛትና አይነት እንደ እኛ የታደለ፤ ሰፊ የሚታረስ መሬት፣ ከዓመት ዓመት የሚፈሱ እልፍ ወንዞች ያላቸው፣ ሰው ሰራሽም ሆኑ የተፈጥሮ ድንቅ መስህቦች ያሉባት አገር ባለቤት የሆንን፣ በሚሊዮን የሚቆጠር የትኩስ ጉልበት ባለቤት የሆኑ ወጣቶች ያሉን፣ በአግባቡ ብንጠቀምባት ትልቅ አንድነት የሚፈጥር ልዩነት ያለን ህዝብና አገር እኛ ነን።

በአሀዳዊ ስርዓት እየተመራች ማንነታቸውን ወደጎን እንዲሉ ይገደዱ የነበሩ ህዝቦች የነበሩባት አገር፣ በክልላቸው ውስጥ በራሳቸው ቋንቋ መስራትም ሆነ መማር፣ በክልላቸው ሀብት መጠቀምና ማዘዝ እርም የሆነባቸው ህዝቦች የነበሩባት አገር የነበረችን እኛ እንጂ ማን ሊሆን ይችላል። ማንም።

በከፈልነው መራር መስዋዕትነት ዛሬ ኢትዮጵያ ሲባል 76 በላይ የሆኑት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አዕምሯችን ውስጥ እንዲመጡ አድርገን አገራችንን እየገነባን ያለን እኛ ነን። በልዩነት ላይ የተመሰረተ አንድነት የሰፈነባት አገር እየገነባን እንደ ታሪኳ ሁሉ የገዘፈ የኢኮኖሚ እድገት እየተመዘገበባት ያለች አዲስ ኢትዮጵያ እየፈጠርን ያለነውም እኛ ነን። እኛ ብዙ ነን። እኛ ትናንትም ነበርን፤ ዛሬም እለን፤ ነገም እንኖራለን።

የትናንቱ ታሪካችንን እንደ ጥሩ መስፈንጠሪያ ቆጥረን ዛሬ በዓለም ዙሪያ የምንደመጥና የምንመረጥ አገር ሆነናል። በዓለም ላይ ነዳጅ ሳይኖራቸው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ አገራት ተርታ በቀዳሚነት የሚገኘው የአገራችን ስም ነው። ትናንት የለመንን እኛ፤ ዛሬ ባለ ሁለት አኃዝ ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት የሚዘገብባት አገር ባለቤት የሆነውም እኛ ነን።

የትናንቱ የልማት ቁጭታችን የዛሬውን ልማት ወልዷል። የዛሬው ልማታችን ደግሞ የነገዋን ኢትዮጵያን የማይፈጥርበት ምንም ምክንያት የለም። ምክንያቱም ከማንም ሳይሆን ከራሳችን የተማርነው ይሄንኑ ነውና። እርስ በርስ በተባላንበት ዘመን ተርበናል፤ እርስ በእርስ ተከባብረን በሰራንበት ዘመን ድርቅ እንኳን መትቶት ረሀብን ድል መትተናል። ይሄ የማንም ሳይሆን የራሳችን ታሪክ ነው። እኛ እንደዚህ ነን።

እየተመዘገበ ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ የጨረሰለት ያበቃላት እንዳልሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው። ስለሆነም አሁንም እኛ ይሄን ተግዳሮት አንድ ሁለት ብለን እንፈታዋለን፤ በተባበረ ክንድም እንረታዋለን። ከምንም በላይ ግን አገራችን እየገባችበት ያለው የሰላም ማጣት ጉዳይ ወደነበርንበት አረንቋ እንዳይመልሰን ያሰጋናል። ስጋቱ ግን ትጋት ካልታከለበት ዋጋ የለውም። ስለሆነም አብረን በወደቅንበት ዘመን አብረን ታግለን አሸንፈን ወደ ድል እንደመጣን ሁሉ፤ አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶች የእኛው ጉዳዮች ናቸውና አብረን የመፍትሄው አካል መሆን አለብን።

መንግስት ብቻውን የፈጠረው ችግር የለም፤ ብቻውን የሚፈታው ችግርም አይኖርም። ስለሆነም የፊታችን ህዳር 29 የቀን የሚከበረው የብሄሮች ብሄረሰቦች ቀን በዓልን ለዚህ አይነቱ ዓላማ ማዋል ይገባል። በዚህች አገር ላይ የነበርን እኛ፤ ያለነውም እኛ የምንኖረውም እኛ ነን ካልን፤ ለስኬቱም ለውድቀቱም አብረን እንወቃቀስ፤ አብረን እንስራ፤ አብረንም አገራችንን ወደፊት እናስኪድ። በልዩነታችን ሳይሆን በአንድነታችን ላይ እናተኩር፤ ከመንደር ፖለቲካ እንውጣ። ከግል ተጠቃሚነት ተላቅቀን ሁላችንም እኔ እኔን ትተን እኛ እኛ እንበል። ምክንያቱም እኔነት ይህችን አገር ወደ ግጭት እንጂ ወደ አንድነት ሲያመጣት አልተመለከትንም፤ ወደፊትም አንመለከትምም።

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።