ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ያቀራረበውን ዕለት ስናከብር

 

ነገ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በአፋር ክልል በሰመራ ከተማ ለ12 ኛ ጊዜ በድምቀት ይከበራል፡፡ ዕለቱ አገሪቱ ለዘመናት ብዝሃነትን መቀበል ተስኗት ዜጎች ተፈጥሮ ካፈራው እንዲሁም በጉልበታቸው ካበረከቱት አስተዋጽኦ በእኩልነት እንዳይጠቀሙ ጋሬጣ የሆነው ስርዓት ተወግዶ ለፌዴራላዊ መንግሥት አወቃቀር እና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ምስረታ እውቅና ያጎናጸፈው ህገ መንግሥት የፀደቀበት በመሆኑ ልዩ ክብር ይሰጠዋል፡፡

ቀኑ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራሳቸውን ቋንቋ፣ ባህል እና ማንነት የማጎልበት እንዲሁም እራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ስልጣናቸው ሕገ መንግሥታዊ እውቅና ያገኘበት ስለሆነ ዜጎች በናፍቆት ይጠብቁታል፡፡ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ጥቅም ያማከለ እድገት እንዲመዘገብ መሰረት የተጣለበት እንዲሁም በሰላም ወጥቶ በሰላም የመግባት ዋስትና የተረጋገጠበት ዕለት በመሆኑም ዜጎች የእኛ ቀን ይሉታል፡፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል መከበር ከጀመረበት ዓመት ወዲህ ማዶ ለማዶ ተራርቀው የነበሩ የአንድ አገር ልጆች ተቀራርበው አክራሞታቸውን ያወጋሉ፡፡ በወደፊት ተስፋቸውና ራዕያቸው ላይ ይመክራሉ፤ ይዘክራሉ፡፡ ይህ በርካታ በጎ እሴቶችን አንግቦ መከበር የጀመረው በዓል አስራ ሁለት ዓመታት ቢያስቆጥርም፣ ትሩፋቶቹም አንድ ሁለት ተብለው ሊጠቀሱ ቢችሉም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉት ሁኔታዎች ዕለቱን ስናከብር ሰከን ብለን ልንመዝናቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉ የሚያመላክት ነው፡፡

ከሰሞኑም በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲሁም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚታየው ሁኔታ በየዓመቱ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓልን ከመዘከር ባለፈ ሊሰሩ የሚገባቸው የነበሩ የቤት ሥራዎች እንደነበሩ አሁንም እንዳሉ ይጠቁማል፡፡ በተለይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቀደም ሲል የአገሪቱ ብዝሃነት መገለጫ አብይ ማሳያዎች ተደርገው ይወሰዱ ነበር፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ከተለያየ ስፍራ የመጡ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በየዕለቱ አብረው መብላታቸው፣ መጠጣታቸው ባህሎቻቸውን መለዋወጣቸው በዚያ ዘወትር ኅዳር 29 ነው እስከማለት አስደርሶ ነበር፡፡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችም ቢሆኑ ዜጎች ማንነትን መሰረት ያደረገ ጠብ ሳያስነሱ ተከባብረው የሚለያዩባቸው መድረኮች ነበሩ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችም ሆነ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብሔርን መሰረት ያደረጉ የጥላቻ አመለካከቶች መታየታቸው፣ የማጥቃት ዝንባሌዎች መከሰታቸው በተቋማቱ ደረጃም ሆነ እንደ አገር ሲገነባ የከረመው የመከባበርና የመቻቻል በጎ እሴት ምን ነካው? የሚያስብለው ነው፡፡

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አካባቢ እያቆጠቆጠ ለመጣው ችግር ምክንያቱ የወጣቶች ስብዕና የሚገነባባቸው መሰረቶች አካባቢ ያለው የተዛባ አመለካከት አንድ ምክንያት ሊሆን ስለሚችል በቅጡ ሊፈተሽ ይገባል፡፡ ለእክሎቹም መፍትሄ መሻት ብልህነት ነው፡፡ ለዚህም በቅድሚያ የሚጠቀሰው ቤተሰብ ነው፡፡ የሰው ልጅ በብሔሩ፣ በሃይማኖቱ በሌሎቹም ልዩነቱ የተነሳ ምንም ዓይነት ተጽእኖ ሊደርስበት እንደማይገባና ሁሉም እኩል መሆኑን የመጀመሪያውን አስተምህሮ በማስረጽ ረገድ ጉልህ ሚና ያበረክታል፡፡ ስለዚህ መልካሙን የመቻቻል እሴት ለማጎልበት ድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡

ወጣቶች ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት በሚያልፉባቸው የተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች የሚሸምቷቸው መረጃዎች የሚያከማቿቸው ዕውቀቶች በዛሬ ማንነታቸው ላይ ጉልህ አሻራ ያሳርፋሉ፡፡ አሁን በየቦታው የሚታየው የተዛባ አመለካከት በትልቁ የሚጠነሰሰው እዚያ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ዛፍ ተጣሞ ከአደገ በኋላ ለማቃናት የሚደረገው ጥረት አዳጋች መሆኑ ግልጽ ነውና ከታችኛው ጀምሮ በየደረጃው በሚገኘው ትምህርት ቤት የመከባበር፣ የመቻቻል እና የአብሮነት እሴት የሚያጎለብቱ ሃሳቦች በስርዓተ ትምህርቱ ሊካተቱ ግድ ይላል፡፡

መገናኛ ብዙሃን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ዓመት እየጠበቁ የመርሃ ግብር ማድመቂያ ከማድረግ የዘለለ ዓላማ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ብዝሃነትን መለያዋ ባደረገችው አገር የጋራ እሴቶችን ለማጎልበት የሚረዱ የታቀዱ ሥራዎችን በየወቅቱ በመስራት በጎዎቹን እሴቶች የማስረጽ ሚናቸውን የመወጣት አገራዊ ግዴታ አለባቸው፡፡ ዳጎስ ያለ የማስታወቂያ ገቢ ያስገኛሉ ተብለው ከሚታሰቡ የወጣቶችን ስስ ስሜት ከሚያማልሉ ፕሮግራሞች የአየር ሰዓት ከፍለው ዜጎችን ለሚያንጹም ይዘቶች ተገቢውን ሽፋን መስጠት አገራዊም ሞራላዊም ግዴታቸው መሆኑን መገንዘብ አለባቸው፡፡ ተግባራዊነቱም ትኩረት ተችሮት ዛሬ ነገ ሳይባል ለዜጎች ዓይንና ጆሮ የሚመጥንና የሚስብ በጎ አመለካከት የሚቀረጽበት ይዘት ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በየዓመቱ መከበሩ በቦታ ርቀት በመገናኛ እጥረት ተራርቀው የኖሩ ሕዝቦችን በማቀራረብ የጋራ አገራቸውን እንዲገነቡ የመቻቻል እሴታቸውን እንዲያጎለብቱ የማገዝ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡ ወደፊትም ይህ ይቀጥላል፡፡ የዘንድሮው በዓሉ መከበር ከጀመረበት ወቅት አንስቶ ሁሉንም ክልል እና የከተማ አስተዳደር በማዳረስ የመጀመሪያ ምዕራፍ ማጠናቀቂያ ተደርጎ የሚወሰድ በመሆኑ ዕለቱን ስንዘክር ቀሪ የቤት ሥራዎቻችንን በጥልቀት በመፈተሽ ለዘላቂ መፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ መሆን አለበት፡፡ በተለይ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያቀራረበውን ዕለት ስናከብር ዜጎች በየትኛውም ስፍራ በማንነታቸው ኮርተው ተከባብረው የሚኖሩበትን እሴት ጠብቀው እንዲኖሩ መልዕክት በማስተላለፍ ይሁን፡፡

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።