ከአገር በላይ ምን አለ?

«የአገር ህልውና ጥያቄ ውስጥ ሲወድቅ ጉዳዩ ከግለሰብና ከባለስልጣናት ክብር በላይ ነው፤ የአሁኑን ግምገማችንን ለየት የሚያደርገው ሁላችንም እንደምንገነዘበው ኢህአዴግ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ  መልካም ነገሮችን እየሰራ የመጣ ፓርቲ ሲሆን፤ በዚህም ሂደት ደግሞ በርካታ ግድፈቶችም ነበሩበት፡፡ ስራችንን እያከናወንን በመጣንባቸው ጊዜ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሃገራችን እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን በተመለከተ ቆም ብለን ውስጣችንን እንድንፈትሽ የሚያስገድዱ ስለሆኑ አጠቃላይ እንደ ፓርቲ ይዞታችን ምን ላይ ነው ያለው የሚለውን መመርመር የግድ አስፈልጓል፡፡ግምገማችንን ለየት የሚያደርገው በኢህአዴግ እህት ድርጅቶች መካከል መጠራጠርና  አለመተማመን  ስለነበር ይህንን ችግር ተለይቶ መፍታት ካልተቻለ ሃገርን መምራት አስቸጋሪ መሆኑን መተማመን ላይ መድረስ በመቻላችን በግልፅነት አከናውነናል፡፡ ...» የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች አመራሮች

ድንቅ አባባል ነው፡፡ መቼም ቢሆን ማንኛውም አካል ከአገር በላይ ሊሆን አይችልም፡፡ ሥልጣንም፣ አገር ማስተዳደርም፣ በሰላም ወጥቶ መግባትም፣ ቤተሰብ ማፍራትና ወልዶ መሳምም፣ ታሞ በክብር መሞትና መቀበርም የሚቻለው አገር ሲኖርና ሰላም ሲሰፍን ብቻ ነው፡፡

ሰላም በሌለበትና አገር በተረበሸበት ሁኔታ ደግ ደጉን ማከናወን ቀርቶ በወጉ መቀበር እንኳ አዳጋች ይሆናል፡፡ ጥቂት ከማይባሉ ወራቶች ጀምሮ በአገሪቱ እየተፈጸሙ ያሉ ያለመረጋጋት ድርጊቶች ለአገር የሚበጁ አልነበሩም፡፡ በተለይ በኦሮሚያ፣አማራ፣ኢትዮ ሶማሌ ክልል በተፈጠረው ቀውስ ዜጎችን ለሞትና መፈናቀል እንዲሁም በመንግስትና በሕብረተሰቡ ንብረት ላይ  ውድመቶች በማድረስ የአገርን ተስፋ የሚያደበዝዙና የሕዝብን ከድህነት የመውጣት ጽኑ ፍላጎት የሚያጨልሙ ሆነው ተስተውለዋል፡፡ እነዚህ ድርጊቶች በየትኛውም መለኪያ ተቀባይነት የሌላቸው የጥፋት መንገዶች በመሆናቸው ዳግም መከሰት የለባቸውም። ለዚህ ደግሞ መንግስትና ህዝብ ተቀናጅተው መስራት አለባቸው። ከሃገር ጥቅምና ህልውና በላይ የሚሆን የለምና።

በአሁኑ ወቅትም ገዥው ፓርቲ /መንግስት/  ለአገር የማይበጀውን ይህንን ስጋት ለማስወገድ ፣ የአገሪቱ ሰላም ወደ ከፋ ቀውስ ውስጥ እንዳይገባና ሕዝብ ለአደጋ እንዳይጋለጥ ትልቅ ኃላፊነት በመሸከሙ የበኩሉን ዕርምጃ ለመውሰድ ችግሮቹን ከነመነሻቸውና መፍትሄያቸው ለመለየት ረጅም ቀናቶች ተወያይቶ የደረሰበትን ድምዳሜ ለሕዝብ አሳውቋል፡፡ ይህን ያደረገው ሃገርንና ህዝብን ከጥፋት ለመታደግ መሆኑ ልብ ማለት ይገባል።

የሕዝቡ ቅሬታና ምሬት እየጨመረ ከፍላጎቱ ጋር የማይመጣጠን ቃል መግባት ብቻ ፋይዳ እንደሌለው፣ ከሕዝብ ፍላጎት ጋር የሚጣጣም ተግባራዊ ዕርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ፣ የሕዝብን ጥቅምና ፍላጎት ለማስከበር አስቀድሞ ራስን መፈተሽ አማራጭ የሌለው በመሆኑ ከአገር በታች ራሱን ዝቅ አድርጎ ውስጡን በመመርመር በሆደ ሰፊነት በራሳቸው ጥፋት ጉዳያቸው በክስ ሂደት ያለና የተፈረደባቸው አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ሌሎች ግለሰቦች  ለመልቀቅ ፣ በተለምዶ «ማእከላዊ» ተብሎ የሚታወቀው የተጠርጣሪዎች ማቆያና የምርመራ ስፍራ ወደ ቤተ መዘክርነት ለመቀየር እንዲሁም በቀጣይም ለሕዝብና ለአገር የሚበጅ ተግባር ለማከናወን ቃል ገብቷል፡፡ ይህ ለሃገር የሚበጅ በሳል ውሳኔ መሆኑን መገንዘብ ያሻል። ከሃገር በላይ የሆነ  ምንም የለምና።

ይህ የገዥው ፓርቲ/መንግስት እርምጃ ወቅታዊና ይበል የሚያሰኝ ሲሆን፤ ቀደም ሲል በተካሄደው የሁከት ተግባር የተካፈሉ  ዜጎች በሙሉ ከጥፋትና ከውድመት ድርጊቶች እንዲታቀቡ የሚያደርግ ነው፡፡ የመንግሥት ግንባር ቀደሙ ኃላፊነት  ሰላም ማስከበርና የዜጎቹን ደህንነት  መጠበቅ ሲሆን፤ የዜጎች ሃላፊነት ደግሞ ለጥያቄያቸው መልስ ሲያገኙ ከአፍራሽ ድርጊት መታቀብ ሊሆን ይገባል፡፡ምክንያቱም ሁሉም ዜጋ ለሃገሩ የሚበጅ ስራ መስራት እንጂ  ሃገርን የሚያጠፋ ስራ መስራት አይገባውም። ከሃገር በላይም አይደለም። ስለሆነም በሃገር ስም መነገድ ማቆም አለበት። ለዚህ ደግሞ ሁሉም የሃገሪቱ ዜጎች ለሰላም ዘብ መቆም አለባቸው።

በማኅበራዊ ሚዲያዎች የጥፋት መልእክት እያስተላለፉ ግጭትና ሁከትን ውጭ ሃገር ሆነው የሚመሩ  ወገኖችም በህዝብ  ስም የሚያራምዱት አገር የማፍረስ ተግባር መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡ እነርሱ በርቀት ሆነው የማይቆጣጠሩትን ኃይል እየቀሰቀሱና እያበረታቱ በሚያደርሱት ጥፋት አገርን ከማፍረስ ውጭ የሚያተርፉት አንዳች ነገር እንደሌለ ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ከሁሉም ጥቅም በላይ መሆኗንም መታወቅ አለበት።

ይህችን አዲሱ ትውልድ የሚረካባትን አገር እድገቷን በማስቀደም ፣ ልዩነቶችን በማቻቻል፣ ተከባብሮና በፍቅር ፀንቶ የሚኖር ኢትዮጵያዊነትን እንዲረከብ በሃላፊነት ስሜት መጓዝ ያስፈልጋል፡፡ በርግጥ አገሩን የሚወድድ ዜጋ  በተሻለ መሠረት ላይ እንድትገነባ ተግቶ የሚሰራ እንጂ  ለጥፋቷ ጥላቻን ሲዘራ፣ ዕልቂትን ሲቀምር የሚያድር ሊሆን አይገባም፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ከሃገርና ከህዝብ ሊያስቀድም የሚችለው የለምና።

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።