ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ተጨማሪ እርምጃ

ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርአት አመለካከትን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ማራመድ ለሚፈልጉ ሁሉ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በዚህም ባለፉት 26 አመታት የተለያየ አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውን ሲያራምዱ ቆይተዋል፡፡ ይህም በሀገሪቱ በታሪክ ታይቶ የማያውቅ እንዲሁም ለዴሞክራሲያዊ ሥርአት ግንባታም  የራሱን በጎ ሚና የተጫወተ ነው፡፡

በሀገሪቱ በተካሄዱ አምስት ምርጫዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ያደረጉት ፉክክር ከዚህ አንጻር ይጠቀሳል፡፡ በተለይ ደግሞ ምርጫ 97 ተቃዋሚዎች የአዲስ አበባን አስተዳደር ምርጫ ማሸነፋቸው፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበሮች  መያዛቸው የሥርዓቱ መጎልበት ማሳያ መሆኑን ለማንም ግልፅ ነው። ነገር ግን  ፓርቲዎቹ ያገኙትን ወንበር በመጠቀም ረገድ ውስንነት ስለነበረባቸውና በተፈለገው ርቀት መሄድ አልቻለም፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ ተቃዋሚ  የፖለቲካ ፓርቲዎች ጽንፍ እየወጡ ከሀገሪቱ ህገ መንግሥት ያፈነገጡ ተግባሮች እየፈጸሙ ከመገኘታቸው ጋር በተያያዘ ይህን ለማስተካከል በሚል ህጉ በሚፈቅደው መሰረት በተለያዩ ወቅቶች ህግ የማስከበር እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ በፓርቲዎቹ አመራሮችና አባላት  መካከል በሚፈጠር መከፋፈልም የፖለቲካ ሙቀቱ ለመቀዛቀዙ ምክንያት ነው።ይህ የፓርቲዎች መከፋፈል አሁንም ድረስ ቀጥሏል ፡፡

በመንግሥት በኩል ሲወሰዱ የቆዩ እርምጃዎች የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ከመስመር ወጥተው በመገኘታቸው የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ሲባል የተወሰዱ እና ትክክለኛም እርምጃዎች ናቸው፡፡ ይህ አይነቱ እርምጃ በቀጣይም ሊወሰድ ይችላል፡፡ መወሰድም አለበት። ማንም ሰው ከህግ በላይ የለምና።

ይሁንና ፓርቲዎቹ  እየታረሙና እየተጠናከሩ መምጣት ሲገባቸው ተዳክመዋል፡፡ ባለፉት ሁለት  ምርጫዎች የነቃ ተሳትፎ አለማድረጋቸውም ለዚህ አንድ ማሳይ ይሆናል፡፡

ፓርቲዎቹ በበኩላቸው የፖለቲካ ምህዳሩ በመጥበቡ እንደልብ መንቀሳቀስ አልቻልንም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ መንግሥት ካለፈው አመት አንስቶ የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ ለማስፋት የሚያስችሉ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። ካለፈው አመት አንስቶም ዴሞክራሲ አማራጭ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው በሚል የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት አስፈላጊነት ላይ ጽኑ አቋም ይዞ እየሠራ ነው።

ባለፉት ምርጫዎች ምክር ቤቶች በአብላጫ ድምጽ የምርጫ ሥርአት መሰረት በተካሄዱ ምርጫዎች ሳቢያ አብላጫው ወንበሮች የተያዙት በገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ  መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህም ድምጻቸውን ለተቃዋሚ ድርጅቶች የሰጡ ህዝቦች ድምጽ እንዳይሰማ አድርጓል፡፡ መንግሥት ይህን የሚያስተካክልና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ድምጽ በምክር ቤቶች የሚሰማበት አሰራር ለመዘርጋት አስቦ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ይህ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት አመላካች ነው።

የዚህ ቁርጠኝነቱ ማሳያ ከሆኑት አንዱ  የምርጫ ህጉን ጭምር በማሻሻል የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር እያካሄደ ያለው ውይይትና ድርድር ነው፡፡ በዚህም ሀገሪቱ ስትከተል የቆየችው የአብላጫ ድምጽ ሥርአትን በቅይጥ ትይዩ የምርጫ ሥርአት ለመተካት የሚያስችል መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ፓርቲዎቹ በሌሎች አጀንዳዎች ላይም እየተደራደሩ ይገኛሉ። የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ይህ አንድ ትልቅ እርምጃ ነው፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በቅርቡ ለ17 ቀናት በአካሄደው ስብሰባ ከአሳለፋቸው ውሳኔዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች መካከልም የፖለቲካ ምህዳር ማስፋት ተጠቃሽ ነው። የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ቀደም ሲል ከወሰዳቸው እርምጃዎች በተጨማሪ  በራሳቸው ጥፋት በእስር ላይ የሚገኙ እንዲሁም ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችንና ሌሎችን ሰዎች የህግ የበላይነትን በማይፃረር መልኩ በምህረት ለመፍታት ወስኗል፡፡ ይህ  እርምጃ በተለያዩ ወገኖች ዘንድ አድናቆት  ተችሮታል። የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያለው ቁርጠኝነት ከፍተኛ መሆኑን ይበልጥ ማረጋገጫ ነው።

ገዥው ፓርቲ /መንግሥት/ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችንና ሌሎችን ለመፍታት የደረሰበት ውሳኔ  የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ከተጀመሩ ሌሎች ተግባሮች ጋር ተዳምሮ በእርግጥም የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያሰፋነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ለምህዳሩ መስፋት ያሳየውን ቁርጠኝነት አጠናክሮ የቀጠለበት ብሎ መውሰድም ይቻላል፡፡

የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ሆነ ሌሎቹ ለእስር የተዳረጉትና በህግ ጥላ ስር የሆኑት ያለምክንያት እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሲባል ነበር እርምጃው የተወሰደባቸው፡፡ ይሁንና መፈታታቸው ለሀገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርአት አዎንታዊ ሚና እስካለው ድረስ ገዥው ፓርቲ /መንግሥት/  ለመፍታት መወሰኑ የሀገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ለማስፋት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት ከመሆኑ በተጨማሪ ሆደ ሰፊነቱን ያመለከተበትም ነው፡፡

በምህረት እንደሚፈቱ እና ክሳቸው እንደሚቋረጥ የሚጠበቁት ፖለቲከኞችና ሌሎች እንዲሁም ፓርቲዎቻቸው ይህን የገዥው ፓርቲ /መንግሥት/  ሆደ ሰፊነት በመመልከት ፣ የሀገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርአቱ እንዲጎለብት፣ የህዝቦች ድምጽ እንዲሰማ ለማድረግ የቤት ሥራ የተቀበሉበት መሆኑንም ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ እነሱም ህግ አክብረው በመንቀሳቀስ ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል። ገዥው ፓርቲ /መንግሥት/  የወሰዱት ምህዳሩን የማስፋት  ተጨማሪ እርምጃ ደግሞ የሚደነቅ እንደሆነ መገንዘብ ይገባል።

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።