ለግብርና ሜካናይዜሽን ስርነቀል ለውጥ ያስፈልጋል

የአገራችን ግብርና ውጤቶች በምርታማነትም ሆነ በጥራት ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በስፋት ጥቅም ላይ አለመዋሉ እክል ሆኖ መኖሩ በምክንያትነት ይነሳል፡፡ በተለይ አብዛኛው አርሶ አደር በአነስተኛ ማሳ የሚጠቀም በመሆኑ እንደ ትራክተር ያሉ ዘመናዊ መሳሪያዎችን የመጠቀም ልምዱ አነስተኛ እንዲሆን እንዳደረገው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ለአብነት በትራክተር ብዛት ከምሥራቅ አፍሪካ አገራት ጋር ያለውን ንጽጽር ማየት ይቻላል፡፡ ለ10 ሺ ሄክታር በኢትዮጵያ 2 ነጥብ 24 ትራክተር ያለ ሲሆን፤ ሱዳን 9 ነጥብ 61፣ ኤርትራ 7 ነጥብ 12፣ ሶማሊያ 12 ነጥብ 06 ፣ ኬንያ 26 ነጥብ 28 ትራክተር አላቸው፡፡
በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ከ80 በመቶ በላይ የምርት እድገት አነስተኛ አርሶ አደሮች በሚያስመዘግቡት የምርት መጨመር እንደሚመጣ እንዲሁም በእቅድ ዘመኑ የዋና ዋና ሰብሎችን የድኅረ ምርት ብክነት አሁን ካለበት ከ15 እስከ 25 በመቶ ወደ 5 በመቶ ዝቅ ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ማላመድና መጠቀም ወሳኝ ነው፡፡ ከእዚህ ባሻገር የምግብ ዋስትናን በቤተሰብ ደረጃ ከማረጋገጥ አልፎ ወደ ኢንደስትሪ ለመሸጋገር የተያዘውን እቅድ ለማሳካት፤ ግብዓት የሚያቀርብ ግብርና ለማጠናከርና እሴት ተጨምሮ የውጭ ምንዛሪ የሚስያገኝ ዘርፍ ለመፍጠር ሜካናይዜሽን አስፈላጊነቱ ከፍተኛ ነው፡፡
የግብርና ሜካናይዜሽንን ወሳኝ ሚና የተገነዘበው መንግሥት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን መጀመሪያ 3 በመቶ የነበረውን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ አርሶ አደር 53 በመቶ ለማድረስ ግብ አስቀምጧል፡፡ በአሁኑ ወቅትም 11 በመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡ በአርሶ አደሩ ዘንድ ግንዛቤውን ለማስፋትም በተያዘው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የግብርና ሜካናይዜሽን ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲከበር ተደርጓል፡፡ ይሁንና የተያዘውን ግብ ለማሳካትና ከትሩፋቱም ለመቋደስ የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠልና ያሉትን ጉድለቶች እየፈተሹ ማሟላት እንደሚገባ በገሃድ የሚታየው ነባራዊ ሃቅ ይጠቁማል፡፡
የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት በአነሰተኛ ማሳ የሚካሄደው የግብርና ልማት የፈጠረውን እክል ለመቀነስ የክላስተር እርሻን የማጠናከሩ ጉዳይ ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ባለፉት ዓመታት አመርቂ ወጤት የተገኘ ሲሆን አሁንም ግንዛቤውን በማስፋት የተጠቃሚ አርሶ አደሮችን ቁጥር የማበራከቱ ጉዳይ ሊጠናከር ይገባል፡፡ ለእዚህም በየቀበሌው የተመደቡ የግብርና ባለሙያዎች ሚናቸውን መወጣት አለባቸው፡፡
የአገሪቱ ዋንኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ግብርና የመሆኑን ያህል ቴክኖሎጂን በመቅዳትና በማላመድ እንዲሁም አርሶ አደሩ ድረስ በመውረድ አጠቃቀሙን፣ ሲበላሽም እንዴት እንደሚጠገን የሚያሰለጥን ባለሙያ በማፍራት ረገድ ከፍተኛ ውስንነት ይታያል፡፡ ለእዚህ አሁን ቁጥራቸው እየተበራከተ የመጣው ዩኒቨርሲቲዎች እና የቴክኒክ ኮሌጆች የመፍትሄ አቅጣጫ የመተለም ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ እንደ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ምርምር ማድረግ፣ ስርዓተ ትምህርት መቅረጽና ባለሙያ ማፍራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
የግብርና ምርምር ማዕከላት የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገቡ ቴክኖሎጂዎችን የማውጣት ተግባራቸው እንዲጠናከር ተገቢው እገዛ ሊደረግላቸው ይገባል፤ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሮቹ የማስተዋወቅና እንዲጠቀሙበት የማስተማር ሃላፊነት የተጣለባቸውም ተቋማትም ሚናቸውን ይወጡ፡፡
የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን የሚያመርቱ፣ ከውጭ አገር የሚያስገቡና በኪራይ አገልግሎት የሚሰጡ የግል ባለሀብቶችን የሚያበረታታ ስርዓት መዘርጋትም እንደ መፍትሄ መወሰድ አለበት፡፡ ዘርፉ ዓለም ከደረሰበት ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ ወደ ኋላ የቀረበት ዘመን እንዲካካስ የቀረጥ ነጻና ሌሎች የማበረታቻ ፓኬጆች ተቀርጸው ቢተገበሩ የሚጠበቀው ውጤት ይመዘገባል፡፡ የግል ባለሃብቶች ሚና እንዲጠናከር የብድር አገልግሎት የሚመቻችበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ ለእዚህም ባለድርሻ አካላት በጋራ በመምከር ተጨባጭ እቅድ ማቅረብና ወደ ተግባር በመግባቱ ሂደትም ተገቢውን ሚናቸውን መወጣት አለባቸው፡፡
ዛሬ የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎች በምርታማነት፣ በጥራት እንዲሁም ብክነትን ከማዳንና ከሌሎችም ትሩፋታቸው ባሻገር አርሶ አደሩ በስፋት ልጆቹን ዘመናዊ ትምህርት እንዲቀስሙ ከሚያደርገው ጥረት አንጻር የሚፈጠረውን የሰው ሀይል እጥረትም ከመፍታት አኳያ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ የግብርና ሜካናይዜሽን በከፍተኛ ደረጃ የሰው ሀይል ከሚጠቀመው የግብርና ዘርፍ ጋር ተያይዞ ብዙዎችን ሥራ ያሳጣል የሚለው ስጋት ሚዛን የማይደፋና ይልቁንም የአርሶ አደሩን ልጅ ጨምሮ በሂደት ለበርካቶች ሥራ የሚፈጥር ዘርፍ መሆኑ ስለታመነበት ዘመኑ የሚጠይቀውን ስር ነቀል ለውጥ ማካሄድ ይገባል፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።