ግንባታ የሚያጓትቱ ተጠያቂ ይደረጉ !

በአገሪቱ በርካታ የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ። የጋራ መኖሪያ ቤት፣ ዩኒቨርሲቲዎች ፣ መንገዶች፣ የባቡር መሰረተ ልማቶች ፣ የሀይል ማመንጫ ፣የመስኖ እና ሌሎችም ግንባታዎች ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ግንባታዎቹ በተለይ ከመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አንስቶ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በማካተት ጭምር ተጠናክረው ቀጥለዋል።
አንዳንድ የግንባታ ስራዎች በተያዘላቸው ዕቅድ መሰረት ተጠናቀው ለአገልግሎት የበቁ ሲሆን፣ በዚህም የህዝቡ የዘመናት ጥያቄ ተመልሷል፡፡አንዳንዶቹ ግን በጨርቄም ማቄም ይሁን በሌሎች አሳማኝ ምክንያቶች ግንባታቸው እየተጓተተ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ልማቱን የሚጠብቀው ህዝብ ጥያቄ ሳይመለስ ለአመታት ለመቆየት ተዳርጓል፡፡
ግንባታ በተጓተተ ቁጥር የግንባታ ዋጋ ቆሞ አይጠብቅምና ለተጨማሪ ወጪ መዳረግ ይኖራል፡፡ ይህ ችግር በሀገራችን በተጨባጭም የሚታይ ሀቅ ነው፡፡ የግንባታው መጓተት አመታትን እየቆጠረ ሲሄድ በህብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታና እሮሮን እያስከተለ ህዝቡ በመንግስት ላይ እምነት እንዳያስዳር እስከ ማድረግ ይደርሳል።
ባለፉት ዓመታት የኢኮኖሚ መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት በተደረገ ከፍተኛ ጥረት የሚያበረታታ ውጤት ተገኝቷል፤ ይሁንና አሁንም የመሰረተ ልማት አገልግሎት ዕጥረት ከፍተኛ የዕድገት ማነቆ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
መሰረተ ልማትን ለመገንባት የሚጠይቀው ኢንቨስትመንት ከፍተኛ ከመሆኑም ባሻገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይፈልጋል፡፡ የዘርፉን የማስፈፀም አቅምን ከመገንባት አንፃር ባለፉት ዓመታት በርካታ ሥራዎች የተከናወኑ ቢሆንም የዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይልና የማስፈፀም አቅም አሁንም በውስን ደረጃ ላይ ይገኛል።
የግንባታ መጓተት በተለያየ ምክንያት እንደሚከሰት ይታወቃል። በጥሬ ዕቃ አቅርቦት አለመኖር፣ በውጭ ምንዛሬ ዕጥረት፣ በፋይናንስ፣ እንዲሁም በሌሎች አሳማኝ ምክንያቶች ግንባታ ሊጓተት ይችላል። እንደነዚህ አይነት ምክንያቶች በታዳጊ አገራት የሚጠበቁ በመሆናቸው ልንታገሳቸው እንችላለን።
በቸልተኝነት፣ በአቅም ማነስ ፣ አስፈላጊ የግንባታ ግብአትን ሳያሟሉ ወደ ግንባታ በመግባት፣ በኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ፣ ሃላፊነትን በአግባቡ መወጣት ባለመቻልና በሌሎች መሰል የስነ ምግባር መጓደል ችግሮች የሚፈጠር የግንባታ መጓተት ግን ይቅር ሊባል አይገባም።
በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ በተደጋጋሚ እንደሚታየውና እንደሚነገረው ግንባታን በወቅቱና በጥራት መሰረት ገንብቶ ለታለመለት አገልግሎት ማዋል ላይ በርካታ ችግሮች ይስተዋላሉ። ይሄ ችግር እንደ 40/60፣ 20/80 በመሳሰሉት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ላይ አሁንም እየታየ ነው።
በተያዘው ዓመት ይጠናቀቃሉ የተባሉት የ40/60 17ሺ መኖሪያ ቤቶች ግንባታቸው አሁን 72 ነጥብ 8 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡ 80 በመቶ ይጠናቀቃል የተባለው የ40/60 20ሺ 503 መኖሪያ ቤቶች አፈጻጸመም 56 ነጥብ 4 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡ በ20/80 የቤት ልማት 26ሺ 480 ቤቶች ግንባታም 20 በመቶ ይቀረዋል።
ለዚህ ዋናው ምክንያት ተቋራጮቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራው አለመግባታቸው ፣ሁለትና ሶስት ህንፃ ይዞ አንዱን ብቻ መስራት ፣ እጅግ አነስተኛ ቁጥር ያለው ሰራተኛ ስራው ላይ ማሰማራት እና የተቋራጭ አቅም ማነስ ትልቅ ፈተና መሆኑ ነው። በዚህም ምክንያት ለበርካታ ተቋራጮች የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።
በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በተለይ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን (የግድቦች ግንባታ፣ የመንገድ ግንባታ፣ የመስኖ ግንባታ... ወዘተ) የማስተዳደርና የመምራት እንዲሁም በተያዘላቸው ወጪ እና ጊዜ የመፈፀም አቅም እስካሁን በተገኘው ተሞክሮ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ግብ መጣሉ፣ የአንድ አገር ዕድገት የሚገለጽበትና የዕድገትም ውጤት የሆነው መሠረተ ልማት በከፍተኛ ደረጃ ማስፋፋትና ጥራቱ የተጠበቀና በዋጋም ተወዳዳሪ የሆነ አቅርቦት መኖር ለዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ያለው ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል፡፡
የኮንስትራክሽን ግንባታው በተጓተተ ቁጥር በጊዜና በወጪ አገር ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖ ቀላል አይሆንም።ኮንስትራክሽኑም ለታለመለት ዓላማ ውሎ ተገቢውን ጠቀሜታ እንዳይሰጥ ያደርጋል። በመሆኑም ጨረታ አሸንፈው ፣ አቅምና ችሎታው አለን ብለው ተወዳድረው ገብተው ለአገሪቱ የመሰረተ ልማት ግንባታ መጓተት ምክንያት የሚሆኑ አካላት ሊጠየቁ ይገባል።ፕሮጀክቶችን የመከታተልና የመቆጣጠር ሃላፊነት ያለባቸው ተቋማትና ግለሰቦችም ተጠያቂ መሆን አለባቸው ።

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።