ትውልዱን ከባህል ወረራ እንታደገው!

ባህል «ባህር» የሆነ ትርጓሜ እንዳለው የመስኩ ምሁራን ይናገራሉ። ሆኖም ቁሳዊና መንፈሳዊ ብሎ መክፈሉ ሁሉንም ያግባባል፡፡ አንድ ሕዝብ ቁሳዊና መንፈሳዊ ባህል ሊኖረው ግድ ነው፡፡ ሰው የባህሉ ፈጣሪና ውጤት ነው። ስለሆነም ባህል በሰው ይፈጠራል፤ በሰው ይከወናል። በሰው አዕምሮ የሚዘራ አዝመራ ነው፤ በሰው ልጅ አዕምሮ እየለማ፣ የሚያለማ የማህበረሰብ ፀጋ መሆኑም እሙን ነው።
ባህል የአንድ ሃገር ህዝቦች ወይም ማህበረሰቦች በጋራ የፈጠሩት ልማዳቸው፣ እምነታቸው፣ እውነታቸው፣ ስርዓታቸውን የሚያሳዩበት፣ አስተሳሰባቸውን የሚገሩበት እንዲሁም ማንነታቸውን የሚያሳውቁበት መገለጫቸው እንደሆነ ይታመናል፡፡ የማንነት መገለጫ የሆነው ዕሴት ከሌላ ዘመናዊነት ከምንለው አስተሳሰብ ጋር ብንቀይጠው ማንነትን አሳጥቶ በራሱ የማይኮራ ትውልድ እንዲበራከት ማድረጉ አይቀሬ ነው፡፡ ከዘመናዊነት ጋር የሚደባለቁትን ለይተን ብናደባልቀው የተሻለ ውጤት ማምጣቱ አይካድም፡፡ ለምሳሌ ቁሳዊ ባህላችን ከዘመናዊው ጋር ቢደባለቅ ውጤታማ ሊሆን ይችላል።
ከሩቅ ምሥራቆቹ እንደ ጃፓን፤ ከአህጉራችን ደግሞ ናይጀሪያና ደቡብ አፍሪካ ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውንና ታሪካቸውን ጠብቀው በማልማትና በማስፋፋት የተሻለ ለውጥ በማምጣት በአርአያነት ይጠቀሳሉ። ሀገራቱ የባህል ዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍ በማድረግ አሁን ላሉበት ደረጃ የመድረሳቸው ዋነኛ ምክንያት በአስተሳሰብና በአመለካከት መለወጥ መቻላቸው ነው።
ቀደም ሲል በሀገራችን ለባህላዊ አለባበስ፣ አመጋገብም ሆነ ባህል ነክ ለሆኑ ጉዳዮች የሚሰጠው ዋጋ እጅግ የገዘፈ ነበር። ምክንያቱም እንደዛሬው ሉላዊነት አልነገሠም፤ የባህል ወረራውም አሁን ባለው ልክ አልተስፋፋም፤ ሌሎችን የማየቱ ዕድልም እጅግ ጠባብ ነበር። አብዛኛው ሰው ለባህሉ ልዩ ፍቅር ነበረው። በመሆኑም በመጤ ባህሎች እንዲቀየጥበት አይፈቅድም፤ እራሱም አይቀይጥም።
ስልጣኔ በባህላችን ላይ ያሳደረው ጫና ብዙ ነው፤ በልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎችና የግንኙነት መስተጋብራችን ውስጥ ሥልጣኔ ስቦ ያመጣውን ጫና አዎንታዊውን ከአሉታዊ መለየት ይገባል። ካለው መልካም ባህል፤ አገራዊ ወግና ልማድ ጋር በተጣጣመ መልኩ ተያይዞ እንዲሄድ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነትም ግዴትም ነው።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ባህሎች የታደለች አገር ናት። ህዝቦቿ ለዘመናት ሲለማመዱት የቆዩትና የራሳቸው ያደረጉት ቱባ ባህል አላቸው። በዚህ ባህል ውስጥ ኖሯል፣ አልፏል ለልጆቹም አውርሷል፡፡ ተረካቢዎቹ ትውልዶችም በዘመን ሂደት እያሻሻሉ፤ በጎደለ እየሞሉ ጠብቀው አቆይተውታል። እንኳን ባህልን ማስጎብኘት የገቢ ምንጭ በሆነበት ዘመን ላይ ተገኝተን ይቅርና ባህል የዓለም ውበት በመሆኑ ብቻ የማይነጥፍ ሀብት ሆኗል። ለዚህም ነው መጠበቅ፣ መንከባከብ፣ ማስረከብና የተሻለውን ለማቆየት የባህሉ ባለቤቶች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው መባሉ።
በአሁኑ ወቅት ባህላችን እየተሸረሸረ ለመምጣቱ ጥናት ማቅረብ አይጠበቅም፡፡ ምክንያቱም የምናያቸውና የምንሰማቸው እውነታዎች በቂ ማስረጃዎች ናቸውና። አዲሱ ትውልድ ሙሉ ለሙሉ ባህሉን ረስቷል ባይባልም፤ የቀድሞውን ትውልድ ያህል ግንዛቤ አለው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ይህ የባህል ወረራ ለአገር ተረካቢው ትውልድ ስጋት መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡
ባህልን ማክበርና መጠበቅ ከቤት ይጀምራል፡፡ ባህልን በመጠበቅና ከብረዛ ለመከላከል ወላጆችና የትምህርት ተቋማት ከፍተኛውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል፡፡ ባህልን የመጠበቅ ሥራ ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሁላችንም በንቃት ልንሳተፍ ግድ ይለናል።
በመንግሥት ደረጃ ባህልን ከብረዛ ለመከላከልና ለማልማት የሚያስችል የባህል ፖሊሲ ወጥቶ በሥራ ላይ ይገኛል። ይሁን እንጅ ስለ ፖሊሲው ምንነት የሚያውቀው ማህበረሰብ በቂ ነው ለማለት አያስደፍርም። ግንዛቤው ሳይፈጠርና ሳይታወቅ ደግሞ ወደ ተግባር መግባት አይቻልም። ስለዚህ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት ባለመሆኑ ፖሊሲውን ያወጣውን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን ጨምሮ በጉዳዩ ላይ የሚሠሩ ባለድርሻ አካላት ሊያስቡበት ይገባል። ሰፊ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ በተከታታይነት ሊሠራ ይገባል፡፡ የባህል ወረራ በወረቀት ላይ በሰፈረ ፖሊሲ ብቻ የሚቆም አይደለም። በመሆኑም ፖሊሲውን በመተግባርና በማስተግበር ረገድ ብዙ ርቀት መጓዝ ይገባል።
የባህል ወረራን ለማስቀረት መጀመሪያ የራስን ባህል ማወቅና ማሳወቅ የግድ ይላል። የባህል ፖሊሲው የራሱ ግዴታዎችና አፈፃፀሞችን በዝርዝር ለማህበረሰቡ ማስረዳትም ይገባል። በፖሊሲው ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተሠራ ቢሆንም ፖሊሲው ከወጣ ጀምሮ ምን ለውጦች አምጥቷል? ቢባል ያን ያህል የገዘፈ መልስ ሊገኝ አይችልም። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የባህል ወረራው እየበዛ እንጂ እየቀሰነ አይደለም። የባህል ፖሊሲውን ሊያስተገብር የሚችለው የመጀመሪያው አካል ራሱ ማህበረሰቡ በመሆኑ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል።
የባህል ፖሊሲ መቅረጽ ብቻ በራሱ ግብ አይደለም፡፡ ለተግባራዊነቱ መትጋት ይገባል። ሥራው የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በመሆኑ ርብርቡ መጠናከር አለበት። የውጭ ናፋቂ ከመሆን አስቀድሞ የራስን ባህልና የባህል ፖሊሲውን ማወቅና ማስተዋወቅ ላይ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። ባህል በሃሳብና በልብ የሚሰርፅ እውነታም ጭምር ነው። የሌላን ናፋቂ ትውልድ ለአገሩ የማይጠቅም፤ በተበረዘ ባህል የሚናውዝና ማንነቱን የሚክድ ትውልድም መበራከት የለበትም። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ትውልዱን ከባህል ወረራ መታደግ የሚቻለው።

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።