የህዳሴ ግድቡን ለሌሎችም ፕሮጀክቶች !

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የዛሬ ሰባት ዓመት ይፋ ሲደረግ መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከ ዳር በመነቃነቅ ድጋፉን በሰላማዊ ሰልፍና ለግድቡ ዕውን መሆን ከተረፈው ሳይሆን ከዕለት ጉርሱ ቀንሶ ለመስጠት ቃል በመግባት ወዘተ አረጋግጧል፡፡ በተለይ ታላቁ መሪ ጓድ መለስ ዜናዊ የግድቡ መሀንዲሶች እኛው ፣ የገንዘብ ምንጮችና አስፈጻሚዎችም እኛው ባሉት መሰረት ህዝቡ ይህንኑ ባለፉት ዓመታት በተግባር አሳይቷል፤ አሁንም በማሳየት ላይ ይገኛል።
በአባይ ወንዝ በከንቱ መፍሰስና በበይ ተመልካችነታችን ሲቆጭ የኖረው እና ይህን ቁጭቱን በእንጉርጉሮ ፣ በስነቃሎች እና በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልጽ የኖረው የኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፉን በገንዘብ ፣በሙያው፣ በጉልበቱ ለማረጋገጥ በገባው ቃል መሰረትም በቦንድ ግዥ፣በስጦታ፣ በህዳሴ ግድብ ዋንጫና ችቦ ፣እንዲሁም በአጭር የጽሁፍ መልዕክት አማካኝነት ማድረጉን ቀጥሏል፡፡ እስከ አሁንም ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥ እና በስጦታ ገቢ በማድረግ በግንባታው ላይ አሻራውን አሳርፏል፡፡ በተፋሰስ ልማትም እንዲሁ በብዙ ቢሊዮን ብር የሚገመት ሥራ ተከናውኗል፡፡
ህዝቡ ግንባታውን በተለያዩ የመገናኛ እና የመረጃ ምንጮች አማካኝነት እየተከታተለ ሲሆን፣ በአካል እየተገኘም እየጎበኘ ይገኛል። በዚህም ለግንባታው የወጣው ገንዘብ በትክክል ሥራ ላይ መዋሉን በማረጋገጥም ለተጨማሪ ድጋፍም ዝግጁነቱን እየገለጸ ነው፡፡ይህ ብቻም አይደለም የግድቡ ግንባታ የህዝብ ግንኙነት ጭምር እየሆነ መላ ህዝባችንን ለግንባታው እያነቃነቀ ነው፡፡
ህዝቡ ከድጋፉ በተጓዳኝ በተሰለፈበት የሙያ መስክም ኃላፊነቱን በመወጣት ኢኮኖሚውን ማሳደጉን እንደሚቀጥል ባረጋገጠው መሰረትም የግድቡ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት ሲመዘገብ የነበረውን ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ከግንባታው መጀመር በኋላም በማስቀጠል የልማቱ አጋርነቱን በተጨባጭ አሳይቷል፡፡
የግድቡ ግንባታ የጋራ ተጠቃሚነት ጉልህ ማስረጃ ነውና በዲፕሎማሲ መስክ ታላቅ ድል የተገኘበትም ነው፡፡ በአጠቃላይ ከናይል ተፋሰስ ሀገሮች በተለይም ከታችኛው የተፋሰሱ ሀገሮች ጋር የግንባታውን ሀገር ተሻጋሪ ጥቅሞች ለማስረዳት በርካታ ጥረቶች ተደርገውም አመርቂ ውጤት ተገኝቶባቸዋል፡፡
ግንባታው በከፍተኛ ህዝባዊ ተሳትፎ ታጅቦ ወሳኝ ምዕራፎችን እየተሸጋገረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም የግንባታው 64 በመቶ ተጠናቅቋል፡፡ ዘንድሮም ከግድቡ የመጀመሪያውን ፍሬ የሚያቋድሰው የኃይል ማመንጨት ሥራ እንደሚጀመርም ይጠበቃል፡፡ የሁለቱ የግድቡ ክንፎች ግንባታ ባብዛኛው የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የሚቀረው እነዚህን ክፍሎች የሚያገናኘው ግንባታ ነው፡፡ የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ተከላ ፣ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ዝርጋታ፣ውሃ የሚተኛበት አካባቢ ምንጣሮ እና ግድቡ እየሞላ ሲሄድ ውሃ ሊሾልክበት እንደሚችል በታመነበት ሥፍራ ሳድል ዳም ግንባታም በተቀላጠፈ ሁኔታ እየተካሄደ ነው፡፡
በዚህ ሁሉ ክንውን ውስጥ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሕዝብን ፍቅር ፣ ቀልብ እንደገዛ ሰባተኛ ዓመቱን ሊይዝ የአንድ ወር ዕድሜ ብቻ ቀርቶታል፤የህዝብ ኃያልነትና ቁጭት እንዲሁም የመንግሥት ቁርጠኝነት የት ሊያደርስ እንደሚችል እያመለከተ ያለ ታላቅ ፕሮጀክት ነው፡፡ በግድቡ ግንባታ የታዩ ታላላቅ ክንውኖች ግድቡን የአሸናፊነት አመለካከት ፣የሀገራዊ መግባባት መግለጫ አድርገውታል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የህዝብና የመንግሥት ጥብቅ ትስስር የተገለጸበት ውጤታማ ፕሮጀክት ነው እና በእርግጥም ታላቅ ነው፡፡ የሀገር እና ህዝብ ራእይ እውን የሚሆንበት ብቻ ሳይሆን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳው የጎላ ግድብ ነው፡፡ በዚህ የግድብ ግንባታ ድልን መቀዳጀት አይደለም ከደህነት ለመውጣት ለምትታር ሀገር ለአደጉትም ቢሆን ብርቅ ነውና ድጋፋችንን አሁንም ልንቸረውና እንደ ዓይናችን ብሌንም ልንጠብቀው ይገባል፡፡
የሀገራችንና የህዝቦቿ ቀንደኛ ጠላት አሁንም ድህነት ነው፡፡ የህዳሴ ግድብን ለመገንባት የተፈጠረው ብሄራዊ መግባባት ፣ የአሸናፊነት አመለካከት ሌሎች ድህነትን ድል ለማድረግ ሲባል በተቀረጹ ፕሮጀክቶች ላይም እንዲንጸባረቅ በማድረግ በድህነት ላይ የተያዘው ዘመቻ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
እንደሚታወቀው መንግሥት የታላቁ ህዳሴ ግድብ እውን እንዲሆን አስፈላጊውን ሀብት ከመመደብ አንስቶ የቅርብ ክትትል ቁጥጥር እያደረገ ይገኛል፡፡ በመንግሥት የቅርብ ክትትል ይህን ያህል ግዙፍ ተግባር ማከናወን እንደሚቻልም ማየት ተችሏል፡፡
የህዳሴ ግድቡን ለሌሎች ለተጓተቱ እንዲሁም በቀጣይ ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶችም መልካም አርአያ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ ሁሉም ፕሮጀክቶች የሚገነቡት ይህችን ሀገር ከድህነት ለማውጣት አልፎም ተርፎ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለማሰለፍ ነውና በህዳሴ ግድቡ ላይ የታየው አፈጻጸም በስኳር እና ማዳበሪያ ፕሮጀክቶችም ላይ መደገም ይኖርበታል፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።