ልማትን የሚሻ መሰረተ ልማትን አያወድምም!

ስለ ዛሬም ሆነ ስለነገ ማሰብ የሚቻለው በሰላም ውስጥ ሆኖ ነው፡፡ አገራችንም ለበርካታ ዓመታት በሰላም እጦት ውስጥ ያሳለፈቻቸው የባከኑ ወቅቶች ያደጉ አገራት የደረሱበት የዕድገት ደረጃ እንዳትደርስ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፡፡
አገራችን እነዚያን ውጣ ውረዶች አልፋ ዛሬ በምናየው ተነፃፃሪ ሰላም፣ ልማትና እድገት ውስጥ የተገኘችውም ሆነ አሁን ያለችበት ደረጃ የደረሰችው የሕይወትና የአካል መስዋዕትነት ተከፍሎበት ነው፡፡ ዜጎች ከሕፃን እስከ አዛውንት መስዋዕትነት ከፍለው የአሁኑ ትውልድ በሰላም ወጥቶ መግባት የሚችልበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል፡፡
ዛሬ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ መስኮች አገሪቱ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ድህነትን ለማስወገድ የምታደርገው ርብርብ በተሳለጠ ሁኔታ እንዲካሄድ ምቹ ሁኔታ የተፈጠረው እና ለውይይትና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ምቹ ሁኔታ የተፈጠረው አምባገነኑን የደርግ ሥርዓት ለመታገል በተካሄደ ፍልሚያ በተገኘው ድል ነው፡፡ ለዚህም በርካታ ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ስለዚህ በመስዋዕትነት የተገኘው ሰላም፣ልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ወደ ኋላ መመለስ የለበትም፡፡
ዛሬ ከሰላምና ልማት ወዳዱ ህዝብ ሳይሆን ከጥፋት መልዕክተኞች ተልዕኮ ተቀብለው በሚፈፅሙት አፍራሽ ተግባር ለዓመታት ተገንብቶ የቆየው ሰላማችን ላይ የተጋረጠ አደጋ አለ፡፡ ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ የታየው አለመረጋጋት ለዓመታት በገነባናቸው ልማቶችና ሃብቶች ላይ ያነጣጠረ መሆኑ በዕውነት የልማት፣ የዴሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብት ዕጦት ያንገፈገፋቸውና ለአመፅ ያነሳሳቸው ዜጎች የውስጥ ስሜት ነው ለማለት የማያስደፍሩ በርካታ ማሳመኛ ምክንያቶችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ለሰላም፣ለልማትና ዴሞክራሲ የቆመ ሃይል ለእነዚህ ተጻራሪ ሆኖ በውድመትና በጥፋት መንገድ አይሰለፍምና ነው፡፡
ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ የሚተጋ፣ ከድህነት ጋር የምናደርገውን ትግል የሚያደናቅፍና ለሰላማችን መደፍረስ መንስዔ የሆነው አለመረጋጋት መንስኤ የሆነ ሃይል ጸረ ሰላም መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡
አርቆ አሳቢ ዜጋ ልማት እየፈለገ የለማውን የሚያወድም አይሆንም፤ መጓጓዣ ትራንስፖርት እንዲሟላለት የሚፈልግ ተሽከርካሪዎችን አያቃጥልም፣ የአገሩንና የራሱን ዕድገት የሚፈልግ ለማደግ ዋነኛ መሰረት የሆኑ ፋብሪካዎችንና መሰረተ ልማቶችን የሚያወድም አይሆንም፡፡ ስለዚህ የዚህ ድርጊት ተዋናዮች አላማ ሰላምም፣ልማትም ሆነ ዴሞክራሲ አለመሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ አላማቸው ከቻሉ ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በሃይል በመናድ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ ስልጣን መውጣት ነው፡፡ ይህ ካልተሳካ ደግሞ ሃገር መበተንና የእርስ በርስ እልቂት እንዲከሰት ማድረግ ነው፡፡ ስለሆነም መላው የሃገራቸን ህዝብ ይህን አውቆ ለሰላም ዘብ መቆም አለበት፡፡
በአሁኑ ወቅት ግን በሁከት የሚሳተፉ አካላት መኪኖችን ሲያቃጥሉ፣ ተሽከርካሪ የሚያልፍባቸውን መንገዶች በእሳት በነደደ ጎማ ሲጠብሱና በድንጋይ ክምር ሲዘጉ፣ የራሳቸው ቤተሰቦች ተቀጥረው የሚሰሩባቸውን ፋብሪካዎች ሲያወድሙ፣ በሕዝብ ሀብት የተገዙ የግልና የመንግስት መኪኖች በእሳት ሲያጋዩ ፣ ህዝብ የሰላም አየር እየተነፈሰ እንዲኖር መስዋዕትነት እየከፈሉ በሚገኙ የፀጥታ ሃይል አባላት ላይ ቦምብ ሲወረውሩና በስለት ሲያጠቁ ተስተውለዋል፡፡ ይህ አስነዋሪ፣ ጸረ ሰላምና ጸረ ልማት ድርጊት መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ መወገዝም ይገባዋል፡፡
መንግሥት አስተማማኝ ሰላም አስፍኖ ፣ ሀሳብን በነፃነት መግለፅ የሚቻልባቸውን ምህዳሮች ፈጥሮ፣ የአገሪቱን ጅምር ዕድገት ለማስቀጠል ደፋ ቀና በሚልበት ወቅት አንዳንድ የህዝብ ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም እኩይ ተግባር ውስጥ የሚዘፈቁ አመራሮች ቢያጋጥሙ እንኳ፤ ችግሩን ከስሩ ለማስወገድ ራሱን ከመፈተሽ ጀምሮ የሕዝብ አገልጋዮች በጥብቅ ዲስፕሊን እንዲሰሩ እርምጃ ለመውሰድ በሚንቀሳቀስበት ወቅት በሕዝብ ጥያቄ ስም የሚነሳው ብጥብጥና ሁከት ከበስተጀርባው የኢትዮጵያ ሰላምና ልማት የማይጥማቸው ኃይሎች አጋጣሚውን በመጠቀም አገር የማፍረስ ተልዕኮ ለማስፈፀሚያቸው እየተጠቀሙበት እንዳለም ግልጽ ነው፡፡
ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን መፈታተን፣ የሰው ህይወት ማጥፋት፣ መሰረተ ልማት ማውደም፣ የልማት አውታሮችን ማቃጠል ወዘተ...የሚጎዳው ሥራ አጥቶ ስራ ፍለጋ የሚያማትረውን፣ ሰርቶ ቤተሰቡን የሚያስተዳድረውን፣ በአጠቃላይ ከልማቱ ተጠቃሚ የሚሆነውን ዜጋ ሁሉ በመሆኑ ጉዳቱ የጋራ ነውና አገር ተረካቢ የሆነው ወጣት ከብጥብጥ ይልቅ ሰላም የሚበልጥበት መሆኑን ተገንዝቦ ለከንቱ ዓላማቸው የሚያነሳሱትን፣ አገር ለማበጣበጥ የሚቀሰቅሱትን በቃችሁ ሊላቸው ይገባል፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።