የጥፋት ኃይሎች ቅዠት መና ይቀራል

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ሥልጣን ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ መያዝ የተከለከለ መሆኑን በአንቀጽ 9 ቁጥር 3 ላይ ደንግጓል፡፡ ይህ ማለት የኢትዮጵያ ብሔር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤቶች በመሆናቸው ማንኛውም ሥልጣን የሚያዘው በአጸደቁት ሕገ መንግሥት መሠረት በየአምስት ዓመቱ በሚካሄድ ምርጫ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ በቀለም አብዮትም ሆነ በማንኛውም አመጽና የሁከት መንገድ ሥልጣን ለመያዝ መሞከር የተከለከለ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ካለ የሕዝብ ይሁንታና ድምጽ ለሥልጣን የሚደረግ ሩጫና ጥረት ሕዝቡንና ሀገሪቱን ወደ ከፋ ቀውስ የሚያስገባ በመሆኑም ሊወገዝ ይገባል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራችን በተወሰኑ አካባቢዎች የተከሰተውን የሰላም መደፍረስ ተከትሎ የዜጎች ሕይወት እያለፈ፤ የሕዝብና የመንግሥት ንብረት እየወደመ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሁኔታው በዚሁ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ኃይሎች መኖራቸውም የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው የሕዝቡን ትክክለኛ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄን በመጥለፍ ለእኩይ ዓላማቸው ለመጠቀም ጥረት በአደረጉ ጸረ ሰላም ኃይሎች ነው፡፡ የእነዚህ ኃይሎች መሪዎችና የሁከቱ አቀነባባሪዎች ኑሯቸውን በውጭ ሀገር ያደረጉ እና በአቋራጭ ሕገመንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ ወደ ሥልጣን ለመውጣት የሚሹ ናቸው፡፡ ይህ መቼም የማይሳካ ከንቱ ህልምና ቅዠት ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ታውቆ ወጣቱ የእኩይ ተግባራቸው ተባባሪ እንዳይሆን መጠንቀቅ አለበት፡፡
የቀለም አብዮት አራማጆች ዋና ግባቸውና ህልማቸው ሥልጣን ነው፡፡ ይህን የሚያደርጉት ደግሞ ሕገመንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ በማህበራዊ ሚዲያ ተደጋጋሚ የሐሰት ዘገባ በማቅረብ፣ ውዥንብር በመንዛትና በማሸበር ነው፡፡ በተጨማሪም በመንግሥታዊ አገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤቶች ፈጣን አገልግሎት እንዳይኖር አሻጥር በመስራት ሕዝቡ እንዲማረር ያደርጋሉ፡፡ ምክንያቱም የያዙት የፖለቲካ አቋም ለሕዝብ ምርጫ ቀርቦ የማይመረጥና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ስለሚገነዘቡ በተለያየ ምክንያት የሚፈጠሩና በቀላሉ የሚፈቱ ቅሬታዎችን በማባባስ ሁከት እንዲፈጠር ይሠራሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ኃይሎች የሠላማችንና ልማታችን ጠንቅ ስለሆኑ መወገዝ አለባቸው፡፡ አላማቸውና ህልማቸው እንዳይሳካም መላው የሀገራችን ሕዝቦች በተለይ ደግሞ ወጣቶች ራሳቸውን ከእነዚህ ኃይሎች ማራቅ አለባቸው፡፡ በተሳሳተ መረጃ የአላማቸው ማስፈጸሚያ እየሆኑ ያሉ ዜጎችም መንገዱ የአለመረጋጋት፣ የጥፋትና የውድመት መንገድ በመሆኑ ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው፡፡ ወላጆች፣ ዘመድ አዝማድና ጎረቤት እንዲሁም ጓደኞችም ወጣቶቹን በመምከር ከጥፋት መንገድ ለመመለስ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የሰላም እጦቱንና አለመረጋጋቱን ለመለወጥ መንግሥት እየሰራ ነው፡፡ ለዚህም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አውጇል፡፡ ይህ አዋጅ ለሕዝቡ ውስጥ ትልቅ አቅም ፈጥሯል፡፡ የፀጥታ አካላትም በአዋጁ መሠረት ሥራቸውን በተገቢው መንገድ እንዲያከናውኑ ዕድል ፈጥሯል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች በተደራጀ የነውጥ አግባብ የፀጥታ ኃይሎችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት አጋጥሟል፡፡ ይሄ እርምጃ የሁከትና ብጥብጥ ኃይሎች የተጀመረው ሰላምና መረጋጋት እንዳይቀጥል በመፈለግ የሞት ሽረት በማድረግ ብጥብጡን ለማስቀጠልና በአቋራጭ ወደ ሥልጣን የመምጣት ህልማቸውን ለማሳካት የሚያደርጉት ጥረት ነው፡፡ ይህ በአብዛኛው ሕዝብ ተቀባይነት የሌለው እኩይ አላማ በመሆኑ መቼም ቢሆን እንደማይሳካ ሊያውቁት ይገባል፡፡
በአሁኑ ወቅት መንግሥት የሀገሪቱን ሁኔታ ወደነበረበት ለመመለስ ከሕዝብ ጋር እየሰራ ነው፡፡ በመሆኑም ይህንን ሁኔታ ለመለወጥ የሚያስችል አቅምና ብቃት አለው፡፡ ችግሮችን በመሠረታዊነት ለመፍታት በጥልቅ ተሃድሶ ሂደት ላይ ያለ በመሆኑ በማያዳግም ሁኔታ ይፈታቸዋል፡፡ ወደ ቀደመው ፈጣን ልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመመለስ የፖለቲካ ምህዳሩ የማስፋት ሥራ እየሰራ ነው፡፡ ትክክለኛ የሕዝብ ጥያቄዎችም ደረጃ በደረጃ ይመልሳል፡፡ ይህም የጥፋት ኃይሎችን ቅዠት መና ያስቀራል፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።