መንግስት ችግሮችን ለመፍታት አቅሙም ቁርጠኝነቱም አለው

ኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች በርካታ ፈተናዎች ተጋርጠውባት እንደነበር የኋላ ታሪኮቻችን ያሳዩናል፡፡ ከነዚህ ፈተናዎችም ውስጥ በውጭ ሃይሎች የተፈጸሙ የወረራ ድርጊቶች እና በውስጥም ያጋጠሟት የመበታተን አደጋዎች ይጠቀሳሉ፡፡
በውጭ ወራሪ ሃይሎች ከደረሱብን ፈተናዎች ውስጥ በተለይ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ በቀኝ ገዢዋ ጣልያን የተካሄደው የወረራ ሙከራ አንዱና ዋነኛው ሲሆን በደርቡሾች ተከስቶ የነበረው የወረራ ሙከራም ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በቅርቡ በሻዕቢያ መንግስት የተካሄደው ወረራም አሁን ያለው ትውልድ በተጨባጭ የሚያውቀው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
እነዚህ ወረራዎች ከተነሱበትና ዓላማ ስንነሳ መነሻቸው እብሪት በመሆኑ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተቀባይነት አልነበራቸውም፡፡ በዚህ የተነሳም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሃገሩን ከወራሪው ሃይል ለመጠበቅ የህይወት መስዋዕትነትን ጭምር መክፈል ችሏል፡፡
በሌላ በኩል በተለያዩ ወቅቶች ሃገሪቱ በውስጥ የተከሰቱባትንም ችግሮች በብልጠትና በተጠና መንገድ በመፍታት ሃገሪቱ ሳትበታን እንድትቆይ መላው የሃገሪቱ ህዝቦች የየራሳቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የነበሩ የታሪክ መዝገቦችን ስናገላብጥ ከምናገኛቸው ታሪኮች ውስጥ በደርግ ውድቀት ወቅት የነበረውን ነባራዊ ሁኔታ ማንሳት ይቻላል፡፡ በወቅቱ ደርግ ሲወድቅ ሃገሪቱ ትበታተናለች፤ የሶማሊያ እጣ ፈንታ ይገጥማታል በሚል ሲያሟርቱ እና ሲተነብዩ የነበሩ በርካታ የውጭ ሃገር ሚዲዎችና የፖለቲካ ተንታኝ ነን የሚሉ ሃይሎች ነበሩ፡፡
ያም ሆኖ ግን የታሰበው ሳይሆን ቀርቶ ኢትዮጵያ ሰላማዊ የሽሽግር መንግስት በማቋቋም በአዲስ መልኩ ፊቷን ወደ ልማት ለማዞር ጊዜ አልወሰደባትም፡፡ ለዚህ ደግሞ የህዝቡ አስተዋፅኦ የላቀ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ለጠላቶቻችን የራስ ምታት፣ ለወዳጆቻችን እፎይታን የቸረ ጉዳይ ሆኖ አልፏል፡፡ ከዚያም በኋላ ቢሆን ኢትዮጵያ በውስጥ የገጠሟት በርካታ ፈተናዎች ነበሩ፡፡ በ1997 ዓ.ም የተካሄደውን ሃገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው ውዝግብና በውጭ ሃይሎችም የነበረው ጫናም በተመሳሳይ ሃገሪቱን ሊበታትን ይችላል በሚል በርካታ ትንበያዎች ነበሩ፡፡ በተለይ በወቅቱ ሃገሪቷ ስትታመስ በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ ያቆበቆቡ ሃይሎች እንደነበሩ የምናስታውሰው ነው፡፡ አንዳንድ የውጭ ሃይሎችም አጋጣሚውን በመጠቀም የሚፈልጉትን የአሻንጉሊት መንግስት ለማስቀመጥም በነበራቸው ፍላጎት ውስጥ ገብተው ለመፈትፈት የሞከሩበት ሁኔታ ተስተውሏል፡፡ ያም ሆኖ ግን መንግስትም ሆነ ህብረተሰቡ ጉዳዩን ሚዛናዊ በመሆነ መልኩ በመያዙ ችግሩ ሊፈታ ችሏል፡፡
በዚህ ሂደት በወቅቱ በአዲስ አበባ የነበረውን የህብረተሰቡን ሁኔታ ስንመለከት በመንግስት ላይ ከፍተኛ ቅሬታ ማንሳቱ ተገቢ ነው፡፡ በተለይ በከተማዋ የነበረው የመልካም አስተዳደርና የኢኮኖሚ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ባለማግኘቱና በየቦታው የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከፍተኛ የህዝብ ቅሬታን ፈጥረው እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ በዚህ የተነሳም ህዝቡ ይህንን ቅሬታውን የገለፀው በተለይ የመንግስትነት ስልጣን ይዞ የነበረውን ኢህአዴግን በምርጫ ካርድ በመቅጣት ስህተቱን በግልጽ ያሳየበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
መንግስትም ቢሆን ይህንን የህዝብ ቅሬታና ውሳኔ የተቀበለበት መንገድ ቅንነት የተሞላበትና ከብልህ አመራር የሚጠበቅ እንደነበር የምናስታውሰው ነው፡፡ በዚህ መሰረት መንግስት ህዝቡ ያቀረበው ቅሬታ ትክክልና ተገቢ መሆኑን በመረዳትና በካርድ ለመቅጣት የወሰደው እርምጃወም አስተማሪ እንደሆነ በመቀበል ችግሩን ፈጥኖ ለማረም ተንቀሳቀሰ፡፡ ቀጥሎ በነበሩት አምስት አመታትም ችግሮቹን አንድ በአንድ በመለየትና በማረም ለከተማዋ ነዋሪ ተስፋ የሚሰጡ እርምጃዎችን በመውሰዱ ህዝቡ ዳግም በ2002 በተደረገው ምርጫ ሚዛናዊ ፍርዱን ሰጥቷል፡፡ በዚህም መሰረት በዚህ ምርጫ መንግስት የወሰደው እርምጃ ትክክለኛና የሚበረታታ መሆኑን በማሳየት ዳግም ድምፁን ለገዢው ፓርቲ በመስጠት ፍላጎቱ እውነትም ልማት እደሆነ ማሳየት ችሏል፡፡
ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች እያሳየች የመጣችው የልማት እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መሄዱ ግልጽ ነው፡፡ በሌላ በኩል የህብረተሰቡም ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱ ግልፅ ነው፡፡ ሆኖም ይህንን ከፍተኛ የህዝብ ፍላጎት በአግባቡ ሊያረካ የሚችል ፈጣን አገልግሎት አለመኖሩ ደግሞ በህዝቡ ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል፡፡ ህብረተሰባችንም እያነሳ ያለው ቅሬታ ከዚህ የእድገት ፍላጎት የመነጨ በመሆኑ የሃገሪቷን የማደግ ራዕይና ጥረት የሚያሳይ አወንታዊ ጫና ነው፡፡
እነዚህን የህዝብ ፍላጎቶች የተረዳው መንግስትም የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችም ለዚህ ዝግጁ መሆናቸውን በተጨባጭ አሳይተውናል፡፡ ከነዚህም ውስጥ በዓለም ላይ በሰለጠኑትም አገራት ጭምር ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ የመፍትሄው አካል ለመሆን የገዢው ፓርቲ ሊቀመንበርና የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሃላፊነታቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸው መንግስት ምን ያህል የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንዳለው የሚያመላክቱ ናቸው፡፡
በአንጻሩ መንግስት ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ቁርጠኝነት ይዞ እየሰራ ባለበት ሁኔታ በአንዳንድ አካባቢዎች አሁንም እየታየ ያለው ግርግርና በህዝብ ንብረት ላይ እያጋጠመ ያለው ውድመት ችግሩን ቆም ብለን እንድናስብ ያደርገናል፡፡ በተለይ ሰሞኑን በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች የተከሰቱ ችግሮች መንስኤ ሰላም ከሚፈልግ ህብረተሰብ የመነጩ ሳይሆን ከጀርባ ሆነው ችግሩ እንዲባባስ ከሚያደርጉ ሃይሎች የሚለኮስ ክብሪት እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡ ስለዚህ መንግስት እየወሰደ ካለው ዘርፈ ብዙ እርምጃ አንጻር ህብረተሰቡ ሰላሙን በማስጠበቅ የጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዲሆን በሰላማዊ መንገድ ጥያቄውን ማቅረቡ መቀጠል ይጠበቅበታል፡፡
ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ትላንትም ሲያደርግ የቆየውና በሃገሩ ጉዳይ የማይደራደር በመሆኑ ይህንን ሃላፊነቱን እንደሚወጣው ይታመናል፡፡ በተለይ ወጣቶች፣ ወላጆች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎችና መላው ህብረተሰብ ከዚህ ቀደም ሲያደርግ እንደነበረው ሁሉ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት የተጀመሩ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ውጤታማ እንዲሆኑና ሃገራችንም ሰላሟን በማረጋገጥ የጀመረችውን የልማት እንቅስቃሴ ይበልጥ ትርጉም ባለውና በተጠናከረ ሁኔታ እንድታስቀጥል ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ በየደረጃው ያለው የመንግስት አካልም ለህብረተሰቡ ፈጣን ምላሽ በመስጠትና የጀመረውን የሰላም መንገድ ይበልጥ በማፋጠን ሃገራዊ ሃላፊነቱን ከመቼውም ጊዜ በላይ መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ ሃገርን ማዳን የሁሉም አካላት የተቀናጀ ጥረት ውጤት ነውና፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።