ውስጣዊ ጥንካሬያችን ለጠንካራ ዲፕሎማሲ

የኢፌዴሪ መንግሥት የውጭ ጉዳይና ደህንነት ፖሊሲ የሃገራችን ብሄራዊ ጥቅምን ማዕከል በአደረገ መልኩ ከሃገሮች ጋር መልካም ግንኙነት የመፍጠር መርህን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ በዚህ መርህ መሰረት ኢትዮጵያ በምታካሂደው የፀረ ድህነት ትግል እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት አጋዥ ከሚሆን ማንኛውም ሃገር ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲያው ግንኙነት ታደርጋለች፡፡በዚህም በስኬት ጎዳና ላይ እንዳለች ለወዳጅም ለጠላትም ግልፅ ነው፡፡
መንግሥት ከምዕራብ ሆነ ከምስራቅ ሃገራት፣ ከአሜሪካም ሆነ ከሩስያ፣ ከአውሮፓም ሆነ ከቻይና፣ ከዓረብ ሃገራት ሆነ ከላቲን አሜሪካ ሃገሮች ጋር የሚያደርገው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሃገሪቱን ሉዓላዊነትና ብሄራዊ ጥቅምን ለድርድር በማያቀርብ መንገድ መሆኑ ለማንም ግልፅ ነው፡፡ ይህ አቋሙ በአስቸጋሪ ወቅትና እንዲሁም ፈታኝ ሁኔታዎች በአጋጠሙት ወቅትም የማይለወጥ ነው፡፡ ለዚህ የቅርብ ግዚያት ሁለት አብነቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡ የ1997 ምርጫን ተከትሎ የተፈጠረው ሁከትና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሃገራችን ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ናቸው፡፡ በእነዚህ አስቸጋሪ ወቅቶች በጠንካራ አቋሙ ጸንቷል፡፡ በዚህም የሃገሪቱን ተሰሚነት ምን ያህል ደረጃ ላይ እንዳለ መገንዘብ ይቻላል፡፡ይህ ለወደፊቱም ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው፡፡
አገራችን በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ተሰሚነትና ተቀባይነት ሊኖራት የሚችለው በቅድሚያ ውስጣዊ ጥንካሬን መፍጠርና በሂደትም እያዳበረች መሄድ ስትችል ነው። ውስጣዊ ጥንካሬያችንን በማጎልበት ረገድ በቅድሚያ በውስጣችን የቅራኔ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ፣ የልማት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማስወገድ መንግሥት እና ህዝብ በጋራ መስራት አለባቸው። አሁን ላይ እዚህም እዚያም የሚታዩ ጊዜያዊ ያለመረጋጋት ችግሮች ቢኖሩም፣ በምንኖርበት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ካሉ አገራት ጋር በተነፃፃሪ ሲታይ አሁንም ድረስ ሰላሟን ያረጋገጠች አገር ኢትዮጵያ ናት።
ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ዛሬ እየገነባችው ያለው ግንኙነት የጥንቱን ታሪኳን በመተረክ ሳይሆን የአሁኑ ትውልድ እየሠራው ባለው ተጨባጭ ገድል ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ በመሆኑ፣ ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ በበለጸጉ አገራት የምትፈልገው እንደቀድሞው ዘመን በእርዳታ ሰጪነትና ተቀባይነት ስሜት ሳይሆን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን በአጋርነት ለመፈጸም ነው። የምሥራቁም ይሁን የምዕራቡ፣ የበለፀገውም ይሁን በማደግ ላይ ያለው ህዝብ ሁሉ ዓይን የሚያርፍባት ተፈላጊ አገር ሆናለች። ይህ የውሥጣዊ ጥንካሬያችን ውጤት መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ አካባቢዎች ያጋጠመንን ያለመረጋጋት ችግር ትውልዱ በፍጥነት ሊያስቆመው የሚገባ ነው። ማንኛውም ችግር ሊፈታ የሚችለው በሰለጠነ አካሄድ፣ በመወያየትና በመመካከር እንጂ በሁከትና ብጥብጥ ሊሆን እንደማይችል መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህ በማድረግም በዓለም ላይ ያለንን ተሰሚነት ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ እንችላለን፡፡ ይገባልም፡፡
ሰሞኑን የሦስት ሃገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል፡፡ የአሜሪካ፣ሩስያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፡፡ እነዚህ ሃገሮች ከሃገራችን ጋር በንግድና ኢንቨስትመንትን፣ በሰላምና ጸጥታ ...አብረው ለመስራት ፍላጎታቸውን አሳይተዋል፡፡ ለፀረ ድህነት ትግሉ አሜሪካ ድጋፍ ሠጥታለች፡፡ ሩስያ ብድር ሰርዛለች፡፡የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስም ንግድና ኢንቨስትመንት በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላት አሳይታለች፡፡ይህ ሁሉ የጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ውጤት ነው፡፡እነዚህ ሃገሮች የመጡበት ወቅት ሃገራችን በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በአለችበት ወቅት መሆኑ ሲታይ ደግሞ ምን ያህል ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ እየተሠራ እንዳለ መገንዘብ ይቻላል፡፡
በሌሎች ሃገሮች የውስጥ ጉዳይ ‹‹እኔ ያልኩት›› ካልተገበራችሁ ብላ ጫና በመፍጠር የምትታወቀው አሜሪካ እንኳ በሃገራችን የውስጥ ጉዳይ ላይ ለመፈትፈት ፍላጎት አላሳየችም፡፡ምክንያቱም የመንግሥትንና የሃገሪቱን ግልጽ አቋም ስለምትገነዘብ ነው፡፡በሃገራችን ሁከት እንዲኖር በውጭ ሃገራት ሆነው የሚሠሩ ሃይሎች አሉባልታም መና ያስቀረ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
የሃገራችን የሰሞኑ የተሳካ ዲፕሎማሲያዊ ድል እንዲሁም ለህዝቦች ሠላም፣ ልማትና ብልጽግና መረጋገጥ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ዋነኛ ተዋናይ መሆን የተቻለው በቅድሚያ የውስጥ ሠላም ለማረጋገጥ እና በተገኘው ሠላም አማካኝነትም ለእድገትና ብልጽግና መስራት በመቻሉ ነው። ስለዚህ ይህንን ጥረት አጠናክሮ በማስቀጠል የዲፕሎማሲው ድልም ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ይገባል፡፡ይቻላልም፡፡ ለዚህ ደግሞ የሃገር ውስጥ ችግሮቻችን በውይይት እና ሰላማዊ በመሆኑ መልኩ የመፍታት ባህል ማዳበር አለብን፡፡ ውስጣዊ ጥንካሬያችን የፈጠረልንን ድሎች ለማስቀጠል የምንችለው በዚሁ መንገድ ነውና፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።