በለሱን የጠበቀ ፍሬዋን ይበላል

በአሁኑ ወቅት ሱስም እንደፋሽን ተከታዩ በዝቷል። የአንዱ ቀዳዳ ሲዘጋ ሌላው እየተከፈተ፤ ቁጥጥሩ ጠንከር ሲል ሌላ መንገድ እየተቀየሰ፤ ወጣቱ እንደቀልድ ለሙከራ በጀመረው ስህተት እየተጠለፈ፤ በሱስ ሰንሰለት ታስሮ መውጫ ቀዳዳ አጥቶ ሲማስን ይታያል።
መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት በወጣቶች ላይ የተጋረጡትን ችግሮች የመቀነስና የወጣቶችን ሰብዕና ለመገንባት የተለያዩ ተግባራትን እንደሚያከናውን ይታወቃል። ይሁን እንጂ ሥራው በቅንጅት ባለመሰራቱ የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ ሲሆን አይታይም።
የተለያዩ የአደንዛዥ እፅ መሸጫዎችና መጠቀሚያዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፉ መምጣታቸው ደግሞ የመከላከል ስራው ውጤታማ አለመሆኑን ያሳብቃል። የአደንዛዥ እፆቹ እየተስፋፉ የሚገኙት ደግሞ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አልፈው በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አቅራቢያ መሆኑ ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል።
በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አቅራቢያ ያሉ የንግድ ቤቶች በሱስ የተጠመዱ ተማሪዎች መደበቂያ መሆናቸው ይፋ ተደርጎ እንደነበር አይዘነጋም። የሱስ ማዘውተሪያ ቤቶቹ በዋነኛነት በሱቆች፣ በፊልም ማከራያዎች፣ በጸጉር ቤቶችና በጀበና ቡና እንዲሁም በተለያዩ ንግድ ቤቶች ሽፋን አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው። በእነዚህ ቤቶች የሚገለገሉ ተማሪዎች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተጠቅሶ ተዘግቦ ነበር።
አሁን አሁን ደግሞ በይፋ ከሚታወቁት አደንዛዥ እፆች በተጨማሪ ለህመምተኞች የሚታዘዙ መድሃኒቶችን በመጠቀም ተማሪዎች ራሳቸውን እያደነዘዙ፤ ለከፋ የጤና ቀውስ እየተጋለጡ እንደሚገኙ መረጃዎች እየወጡ ነው። በተለይም የችግሩን ስፋት የሚያሳየው ድብርትን ለማስወገድ ወይም ለመነቃቃት ተብለው በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚገኙ የመድሃኒት መደብሮች ካለሃኪም ማዘዣ የሚቸበቸቡት መድሃኒቶች ተጠቃሽ ናቸው።
በመሆኑም አደንዛዥ እፆችና የወጣቶችን ሰብዕና በተበላሸ መልኩ የሚቀርጹ ሁኔታዎችና ተፅዕኗቸውን ማህበረሰቡ እንዲገነዘብ ማድረግ ያስፈልጋል። ማህበረሰቡም የእያንዳንዱ ወጣት ሰብዕና መበረዝና ሱስ ውስጥ መዘፈቅ ለአገር የሚያመጣው መዘዝ እጅግ ከፍተኛ መሆኑንና ለራሳቸው ለወጣቶቹም ቢሆን ከጉዳት በስተቀር ጥቅም እንደሌለው በትክክል መገንዘብና ማስገንዘብ ይጠበቅባቸዋል።
የወጣቶችን በመጤ ጎጂ ባህሎችና የአደንዛዥ እፅ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያስችል የአምስት ዓመት ስትራቴጂ እቅድ ማዘጋጀቱ አይዘነጋም። በአገሪቱ የተገነቡ የመዝናኛ ማዕከላት በቂ ካለመሆናቸው ባለፈ የተገነቡትም የሚሰጡት አገልግሎት በቂ አለመሆኑ ወጣቶችን ለሱስ ተጋላጭ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል። ይህን ችግር ያቃልላል የተባለው ስትራቴጂክ እቅድ መዘጋጀቱ ምን ውጤት እያመጣ እንደሆነ መገምገም ይገባል።
የሰብዕና ግንባታ ሥራው ወጣቶች በብዛት ከሚውሉበትና ጊዜያቸውን ከሚያሳልፉበት አካባቢ አኳያ የሚመጥን ሥራ እንዳልተሰራ ይታመናል። የወጣት ሰብዕና ግንባታ ሥራ ሲታቀድ ሱስ ውስጥ የገቡ ወጣቶችን ከሱስ ለማውጣት ብቻ መሆን የለበትም። ወጣቶች ወደሱስ ለመግባት ዕድሉ የተመቻቸ በመሆኑ አዳዲስ ሱስ ውስጥ የሚገቡ ወጣቶችንም ለመታደግ እቅድ ሊኖር ይገባል፡፡ ሁሌም ከችግር በኋላ መፍትሄ ሳይሆን አስቀድሞ የችግሩን መንስኤ በመግታት ወጣቶችን የመታደጉ ሥራ በይበልጥ ሊጠናክር የግድ ይላል፡፡
ህብረተሰቡ፣ ሱስ ህመም መሆኑንና በህክምና እንደሚድን ግንዛቤው አነስተኛ ነው፡፡ በመሆኑ ወጣቶች ሱስ ውስጥ ከተዘፈቁ በኋላ ማከም እንደሚቻል የማስገንዘብና ለሱስ እንዳይጋለጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል። ወጣቶች በብዛት የሚገኙባቸውና ለሱስ ተጋላጭ የሚያደርጉ ሁኔታዎችን ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት የትምህርት ተቋማት አካባቢ የሚስፋፉ ለሱስ አጋላጭ ንግዶችን ለማስወገድ በቅንጅት መስራት ይገባል፡፡
ነገ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለሚያስፈልጋት አገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ከሱስ የጸዳና ባለ ብሩህ አዕምሮ ተማሪዎች ያስፈልጉታልና ሁሉም ከወዲሁ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት አለበት። በለሱን የጠበቀ ብቻ ነው ፍሬዋን ሊበላ የሚችለው፡፡ ካልሆነ ግን ዛሬ በአግባቡ ያልጠበቅናቸውና ያልተንከባከብናቸው ወጣቶችና ታዳጊዎች ነገ የአገር ስጋት መሆናቸው አይቀርም፡፡
የወደፊት የአገር ተረካቢዎች በሱስ እንዲጠመዱና ከመንገዳቸው እንዲሰናከሉ ምክንያት የሚሆኑ የንግድ ተቋማትም ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል፡፡ የሚመለከተው አካል በቃችሁ ሊላቸው ይገባል፡፡ ትምህርት ቤቶችም የቀለም ትምህርትን ከመስጠት ባለፈ በስነምግባር የታነጹ ዜጎችን የማፍራት ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ በለሶቻችን ተንከባክበን በማሳደግ የነገ አገር ተረካቢዎችን ስብእና መገንባት የሁላችንም ኃላፊነት መሆን ይኖርበታል፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።