ክብር ለእናቶች!

«እናት ለምን ትሙት ትሒድ አጎንብሳ ታበላ የለም ወይ በጨለማ ዳብሳ» የሚል ዘፈን ሲሰማ ሁሉም ሰው እናቱን ያስታውሳል። በዚያው ቅጽበት እናትህ ምንህ ናት ቢባል ብዙ ነገር ይደረድርና በቃ ቃላት የለኝም ብሎ ይዘጋዋል። ምክንያቱም ስለእናት ብዙ ነገር ማለት ስለሚቻል። በተለይ ከሚያዝያ መጨረሻ ጀምሮ እስከዛሬዋ ዕለት የእናቶች ቀን ታስቦ በሚውልበት ዕለት ስለእናቶች ክብር ብዙ የምንሰማው ነገር አለ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር አብይ አህመድ መጋቢት 24 ቀን 2010ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአደረጉት ንግግር «የሰባት ዓመት ልጅ እያለሁ እንዲህ ከፊታችሁ እንደምቆም የምታውቅ እና ይህንን ሩቅ ጥልቅ እና ረቂቅ ራዕይ በውስጤ የተከለች፣ ያሳደገች እና ለፍሬ ያበቃች አንዲት ኢትዮጵያዊት እናት እንዳመሰግን በትህትና እጠይቃለሁ። ይህች ሴት እምዬ ናት፤ እናቴ ከሌሎቹ ቅን የዋህ እና ጎበዝ ኢትዮጵያውያን እንደ አንዶቹ የምትቆጠር ናትና ቁሳዊ ሀብት ብቻ ሳይሆን አለማዊ እውቀትም የላትም፡፡
በእናቶች ውስጥ ሁሉንም የኢትዮጵያ እናቶች ዋጋ እና ምሥጋና እንደመስጠት በመቁጠር ዛሬ በህይወት ካጠገቤ ባትኖርም ውዷ እናቴ ምሥጋናዬ ከአፀደ ነፍስ ይደርሳት ዘንድ በብዙ ክብር ላመሰግናት እወዳለሁ፡፡ ሌሎች ኢትዮጵያውያን እናቶቼ በልጆቻቸው የነገ ራዕይ ላይ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው በመገንዘብ ነገ ለሚያፈሩት መልካም ፍሬ ዛሬ ላይ የሚዘሩት ዘር ዋና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ለሚከፍሉት መስዋእትነት ያለኝን በምንም የማይተካ አድናቆት፣ ምስጋና እና ክብር እገልጻለሁ...» ብለዋል፡፡ ይህ ንግግር ብዙዎች እናታቸውን እንዲያስታውሱና የደስታን እንባን እንዲያነቡ አድርጓቸዋል፤በንግግራቸው ኢትዮጵያዊ እናቶች ለልጆቻቸው ያላቸው ዋጋ ምን ያህል ላቅ ያለ ስለመሆኑም ትምህርት የሰጠ ነው።
የእናት ፍቅር የሰው ህሊና ሊመረምረው፤ የሰው ልብ ሊሸከመው አይችልም። ስለዚህ ሆደ ሰፊና ለአገር ሟች፤ ሰዎችን ወዳጅ መሆንን ከእናቶች መማር ያስፈልጋል። ሁሉም ሰው በእናቱ ይመካል፣ ሁሉም ሰው የራሱን እናት የተለየች እንደሆነች ይመሰክራል፡፡ሁሉም የእናቱ ፍቅር፣ መስዋእትነት፤ መከራ፤ ከየትኛውም እናት የበለጠ እንደሆነ ይናገራል። ይህ የመጣው ደግሞ የእናትን ያህል አፍቃሪ ለመሆን እናት መሆን ግድ ስለሚል ነው።
እናትነትን ለመግለፅ ቅኔ ቢደረድሩ፣ ቋንቋ ላይ ቢራቀቁ፣ ዜማ ላይ ቢፈላሰፉ. . . ተገልፆ አያልቅም። እናትነት ጥልቅ ነው፤ ውስብስብ ነው፤ ምስጢር ነው። እናት ልጇ አድጎ ትልቅ ሰውም ቢሆን ራሱን ቻለ አትልም። ለእሷ አሁንም ልጅ ነው። እንደ ልጅነቱ ሁሉ በጉልምስናው ጊዜም ትጨነቅለታለች። በመሆኑም ከራስ ያለፈ ተቆርቋሪነትን፤ እንዲወድቅ አለማሰብን ከእናትነት የምንወስደው ልዩ ባህሪ ሊሆን ይገባል።
ፈጣሪ ነች የምትባለው እናት ኢትዮጵያ ውስጥ ለየት ያለ ትርጓሜ ይሰጣታል። ለምሳሌ አብዛኛዎቹ አውሮፓውያን እናቶች ልጆቻቸውን እስከ 18 ዓመት ድረስ ካሳደጉ በኋላ ለመተያየት እንኳን አይፈልጉም። ልጆችም ራሳቸውን ከቻሉ ወደ ወላጆቻቸው እምብዛም አይመጡም። ለአብነት ያህል ኖርዌያውያን፣ ጀርመናውያን እና የሌሎችም እናቶች በልጆቻቸው ናፍቆት እንደሚሰቃዩ ጥናቶች ያሳያሉ። እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን እናትና ልጅን የሚለያያቸው ሞት ብቻ ነው። ፍቅራቸው እስከ መቃብር ይወርዳል።
ይህንን ለማጠናከርም አበው “እናትነት እውነት፣ አባትነት እምነት ነው” ይላሉ፡፡ ምክንያቱም እናት ከእርግዝናዋ ጀምሮ እስከ ምጧ ድረስ በጭንቀት ታሳልፋለች። ከዚያም አልፋው በተለይ ኢትዮጵያውያን እናቶች አባትም እናትም ጭምር ሆነው ስለሚያሳድጉ ስቃያቸው የበረታ ነው። ስለሆነም እናቶች ተጎሳቅለው ልጆቻቸው እንዲያምርባቸው፤ ደክመው ልጆቻቸው እንዲበረቱ፤ ከስተው ልጆቻቸው እንዲፋፉ ሳይታክቱ የሚሰሩ ባለውለታዎቻችን ናቸውና ክብር ለእናቶች ይገባል።
የእናት ጥበብ የመኖርን ጥበብ ለልጆች ያስተምራል፤ የእናት ልብ የሕፃናት ትምህርት ቤት ይሆናል፤ እናት ጉዳታችንን እና ጭንቀታችንን ሁሉ የምንቀብርበት ስፍራ ናት። እናት ምግብ ናት፣ ፍቅር ናት፣ ምድር ናት፡፡ በእርሷ መወደድ ማለት በሕይወት መኖር፣ ስር መስደድና መታነጽ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን እናቶች ደግሞ ይህንን ሁሉ ያሟላሉ።
ለእናቶች ክብር መስጠት ሲባል ለእናቶች ቀን ስጦታ ከመስጠት በላይ ዘወትር አክብሮት ማሳየት ነው። ሁሉም ሰው ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም እናት ክብር ሊሰጥ ይገባል፡፡ እናቶችን ማክበርና ፍቅር ማሳየት ትልልቅ ስጦታ በመስጠት ብቻ ሳይሆን ለመስዋዕትነታቸው እውቅና በመስጠትም ነው።
እናት ስቃይዋ ከንቱ እንዳልቀረ በማሳወቅ፣ ሰው እንደወለደች እንድታውቅ መልካም ሰው ሆኖ በማሳየት፣ ህመሟ ልፋትዋ ውሃ እንዳልበላው በሥራ በመተርጎም፣ ደግነቷን ሳይበርዝ ለቀጣዩ ትውልድ በማስተላለፍና የምትፈልገውን ሙሉ አድርጎ በማሳየት ክብሯን መግለጽ ያስፈልጋል። እናት ሌሎች እናቶች እንደ እርሷ ሆነው ማየት ትፈልጋለች። ብዙዎች ለእናታቸው ማድረግ የማይፈልጉትን በሌሎች ላይ ሲተገብሩት ስታይ ያማታል፤ አልፎ ተርፎ እናቶች ይከበራሉ በሚባልበት የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ውስጥ በአደባባይ እናቶችን የሚያዋርዱ ስድቦች እንዲህ የተለመዱ ሲሆኑም ቅስሟ ይሰበራል። እናም ለእናት ክብር ሲሰጥ ይህም ግምት ውስጥ መግባት አለበት። ዘላለማዊ ክብር ለእናቶች ይሁን!

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።