የኮንስትራክሽን ዘርፍ የስራ ላይ ደህንነት ትኩረት ይሻል

የውጭ መገናኛ ብዙሃን አዲስ አበባ ከተማን ግንባታ እያበበባት የምትገኝ ይሏታል፡፡ እውነትም ነው፡፡አዲስ አበባ በመልሶ ልማትና በማስፋፊያ ስፍራዎች የሚካሄደው የቤቶች፣ የኢንዱስትሪ፣ የሆቴል፣ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚገነቡና ሌሎች ህንጻዎች ማረጋገጫዎች ናቸው፡፡ግንባታ የማይካሄድበት የከተማዋ ክፍል አለ ለማለትም አያስደፍርም፡፡የሚገነቡት ህንጻዎች ባለብዙ ወለል ህንጻዎች ናቸው ፡፡
ተመሳሳይ ግንባታዎች በመላው ሀገሪቱም እየተካሄዱ ናቸው፡፡በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄዱ የመንገድ ፣የግድብ፣ የስታዲየም የስኳር ፋብሪካ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ፣ ወዘተ ግንባታዎች የኮንስትራክሽን ዘርፉን እያደገ መምጣት የሚያመላክቱ ሌሎች ማሳያዎች ናቸው፡፡በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ስራ ተቋራጮች በስፋት እየተሳተፉበት የሚገኝና ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠርም በኩልም ተጠቃሽ ነው፡፡
እነዚህ ግንባታዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂ ፣ እውቀት እና የተማረ የሰው ሀይል የሚፈልጉ እንደመሆናቸው ለሰራተኞች ደህንነት ጥንቃቄ ማድረግንም ይጠይቃሉ፡፡ ከዚህ አንጻር የኮንስትራክሽን ዘርፉ የመስፋፋቱን ያህል በቴክኖሎጂ አጠቃቀም በኩል ክፍተት ይስተዋላል፡፡ አንዳንዶች ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እስከ መጠቀም የደረሱ ቢሆንም ለሰራተኛ ደህንነት በሚደረግ ጥንቃቄ በኩል ግን በሁሉም ዘንድ ችግር አለ፡፡
ችግሩ ለሰራተኞች የደህንነት መጠበቂያ ቁሳቁስ አለመቅረብ፤የደህንነት ጥንቃቄ አስፈላጊነት ላይም ተገቢውን ግንዛቤ የማስጨበጥ ተግባር አለመከናወን በሰራተኞች ላይ አደጋ እያደረሱ መሆናቸው ነው፡፡
አሰሪዎች / ስራ ተቋራጮች ለመወጣጫ የሚጠቀሙት እንጨት ነው፡፡ እንጨቱ መበስበሱ እና ከአገልግሎት ውጪ መሆኑ እየታወቀም ጥገና የማይደረግለት በመሆኑም በሰራተኞች ላይ አደጋ እያስከተለ ይገኛል፡፡የግዙፍ ህንጻዎች ግንባታ ጭምር በእንጨት መወጣጫ እየተካሄደ ነው ፡፡ አንዳንድ ህንጻዎች ጥራታቸውን በጠበቁ ግብእቶች ባለመካሄዳቸው ሳቢያም ግንባታቸው እየተካሄደ ባለበት ወቅት ጭምር ሲፈርሱ ታይቷል፡፡
ይህ ችግር እንዳይፈጥር ማድረግ የሚያስችል በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ በዋናነት ትኩረቱን በደህንነትና ጤንነት ላይ ያደረገ አዋጅ ቁጥር 724/2001 ያለ ቢሆንም ስራ ላይ በማዋል በኩል ክፍተት በመታየቱ ሰራተኞችን ከሞትና ከአካል ጉዳት መታደግ አልተቻለም፡፡ በአደጋው የሞቱም ሆነ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች መረጃ በሚገባ እየተሰበሰበ ባለመሆኑም በደፈናው የስራ ላይ አደጋ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው ከማለት በዘለለ ይሄ ነው የሚባል በሚገባ የተጠናከረ መረጃ የለም፡፡አንዳንዶች ጉዳቱን ያሳውቃሉ፤እያንዳንዱ በስምምነት ይጨርሳሉ፡፡
በዚህ ግዙፍ ኢኮኖሚ በሚንቀሳቀስበት፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ሰራተኛ በሚውልበት ዘርፍ መንግስት እና ባለድርሻ አካላት በአደጋው እየተጎዳ የሚገኘው ሰራተኛ ደህንነት ማስጠበቅ አለመቻላቸው እና ኃላፊነታቸውን አለመወጣታቸው በእጅጉ ያሳስባል ፡፡
አሰሪዎች / ስራ ተቋራጮች በእንጨት መወጣጫ ሳቢያ ሰራተኞች ከፍታ ካለው ህንጻ እንደ ቅጠል እየረገፉ ሲያልቁ ዝም የሚባል ከሆነ ትልቅ ኃላፊነት ጎድሏልና ቁጥጥርና ክትትል መደረግ ይኖርበታል ፣እርምጃውም ጠንካራ ሊሆን ይገባል፡፡በተወሰነ የግንባታ ቦታም ቢሆን ሰራተኞች የተሰጣቸውን የደህንነት መጠበቂያ ቁሳቁስ ሳይጠቀሙ ይሰራሉ፡፡ይህም ቢሆን አደጋ ከደረሰ ተጠያቂው አሰሪው መሆኑም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ሰራተኞቹ ወጣቶች እንደመሆናቸው የእነሱ ሞት እና ጉዳት እነሱን ብቻ ጎድቶ አያበቃም፡፡ከእነሱ ጀርባ ቤተሰብ እና ሀገር አሉ፡፡ጉዳቱ እየከፋ ሲሄድም ዘርፉን ሰራተኞች ላይመርጡ የሚችሉበት ወይም ከፍተኛ ክፍያ የሚጠይቁበት ሁኔታ ሊከሰትም ይችላል፡፡ ተቋራጮችም ቢሆኑ ክስተቱ በተፈጠረ ቁጥር በሰራተኛው ላይ በሚያሳድረው አሉታዊ ተጽእኖና በሌሎች ህጋዊ ጉዳዮች ሳቢያ ግንባታ ሊስተጓጎልባቸውም ይችላል፡፡ስለዚህ የስራ ላይ ደህንነት መጠበቅ እጅግ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
ይህንን ችግር ለመፍታት አሰሪው መንግስት ያወጣውን አዋጅ መተግበር ይጠበቅበታል፡፡የመንግስት አካላትም አዋጁ ስለመፈጸሙ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ችግሩን በፈጠሩ አካላት ላይ ተገቢውን አስተማሪ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡ ለሰራተኛው በየጊዜው በደህንነት ዙሪያ ግንዛቤውን ማዳበር፣ የደህንነት ቁሳቁስ የማይጠቀም ከሆነም በስራ ላይ ባለማሰማራት ጭምር ለህጉ መከበር መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እያደገ መገኘት ህንጻ ለማቆም ብቻ መሆን የለበትም፡፡እድገቱ ሁሉን አቀፍ መሆን ይኖርበታል፡፡ አሰሪው በዘርፉ የደህንነት መጠበቂያ ስርአት ባለመኖሩ ሳቢያ ሰራተኞች እንደ ዋዛ ሲሞቱና ሲጎዱ ዝም ብሎ መመልከት ወይም ካሳ ወርውሮ መቀመጡ ተገቢ አይደለም፡፡
የስራ ላይ ደህንነት የሚያረጋግጠውን ህግ መተግበር አለበት፡፡ለሰራተኞች ሞትና አካል መጉደል ዋና ምክንያት ተደርጎ እየተወሰደ ያለው የእንጨት መወጣጫ በብረት መሆን ይገባዋል፡፡የዘርፉን ችግር እንደሚፈታ የሚጠበቀው የኮንስትራክሽን ምክር ቤትም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት አስቸኳይ መፍትሄ ማኖር ይኖርበታል፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።