ከማስጠንቀቂያ ያለፈ እርምጃ ያስፈልጋል

በፌዴራሉ ዋና ኦዲተር በተደጋጋሚ ስህተት መፈፀማቸው ከሚነገርላቸው ተቋማት ዩኒቨርሲቲዎች ቀዳሚውን ቦታ ይይዛሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹ በሀብት አጠቃቀም፣ በህግ አተገባበር እንዲሁም ግልፅነትና ተጠያቂነትን የተላበሰ አሰራር በመዘርጋት ረገድ ሰፊ ክፍተት እንዳለባቸው ዋና ኦዲተር በተከታታይ የኦዲት ግኝት ሪፖርት ያቀርባል፡፡
በአንድ ወቅት ዋና ኦዲተር የዩኒቨርሲቲዎችን የአሰራር ክፍተት ሪፖርት ሲያቀርብ ከአንድ የምክር ቤት አባል‹‹ ዩኒቨርሲቲዎቹ አውቀው ነው እንዴ የሚያጠፉት?›› እስከ ማለት የደረሰ አስተያየት ተሰንዝሯል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹ ለሌሎቹ ተቋማት አርዓያ መሆን ሲገባቸው በስህተት ጎዳና ላይ መራመዳቸው ‹‹ነገሩ እንዴት ነው?›› ማስባሉ አልቀረም፡፡
በየተቋማቱ የሚመደብ ባለሙያና አመራር ከእነዚህ የትምህርት ተቋማት የሚወጣ መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ ጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንደሚሻ ያሳያል፡፡ በአሰራር ክፍተት በተደጋጋሚ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠቀሱ ዩኒቨርሲቲዎች ከሚወጡ ባለሙያዎችና አመራሮች የተሻለ ነገር መጠበቅ አስቸጋሪ ማድረጉም አልቀረም፡፡
በቅርቡ እንኳን የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር መቀሌና ዲላ ዩኒቨርሲቲዎች ከህገ ወጥ ክፍያና ግዥ ፣ ከገቢ አሰባሰብ፣ ከንብረት ምዝገባና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ጉድለቶች እንዳለባቸው በኦዲት ግኝት ማረጋገጡን በመጠቆም የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ሪፖርቱን ለምክር ቤት አቅርቧል፡፡ እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ለማሳያነት ቀረቡ እንጂ ችግሩ በሌሎቹም በስፋት ይስተዋላል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎቻችን ሁሌም ከችግር ፀድተው ለመታየት አልበቁም፡፡ የዚህ ዋናው ችግር ደግሞ ኃላፊነትን በአግባቡ ካለመወጣት ይመነጫል፡፡ የዩኒቨርሲቲው አመራር ኃላፊነቱን በብቃትና በጥራት አለመወጣቱ ለብልሹ አሰራር በር ይከፍታል፡፡ የሥራ አፈፃፀሞችን በመገምገም ድክመትና ጥንካሬን ከመፈተሽ ይልቅ ለስህተቱ ምክንያት ፍለጋ እጁን ወደ ሌሎች ሲቀስርም ይስተዋላል፡፡ ይህ ደግሞ ለውጥም፣ ውጤትም አያመጣም፡፡
የዕውቀትና የአቅም ግንባታ ማዕከል የሆኑት ዩኒቨርሲቲዎች ከአቅም በታች አፈፃፀም ማስመዝገባቸው ከቆሙበት ተልዕኮ ጋር የሚቃረን ዕውነታ ነው፡፡ ተገቢውን ዕውቀትና ክህሎት የጨበጠ እና በመልካም ሥነ ምግባር የታነፀ ዜጋን ለማፍራት የሚጥር ዩኒቨርሲቲ የችግር ማሳያ ሆኖ መቅረብ የለበትም፡፡ ለችግሮች የተለያዩ መፍትሔዎችን ማፍለቅ የሚችሉ ባለሙያዎችን የሚያፈሩ ተቋማት በባለሙያ እጥረት ለስህተት መዳረጋቸውን በምክንያትነት ማቅረብ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
መስተካከል የሚገባውን በማስተካከል፤ ጥሩ ውጤት የተመዘገበበትን በማጠናከር መሄድ ይገባል፡፡ ችግር በታየባቸው አካላት ላይም ህጋዊውን ሥርዓት ተከትሎ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ተገቢነቱ አያጠያይቅም፡፡ ለዚህ ደግሞ የሁሉም ድርሻና ርብርብ ወሳኝ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹ ራሳቸውን በመፈተሽና በመገምገም ሥራዎች ህጋዊውን ሥርዓት ተከትለው እንዲከናወኑ መትጋት አለባቸው፡፡ ስህተቶች ሲኖሩም ሳይውሉና ሳያድሩ መፍትሄ እንዲያገኙ መጣር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዋናው ኦዲተርም በዩኒቨርሲቲዎች ላይ የሚያገኛቸው የኦዲት ግኝቶች መስተካከላቸውን በየጊዜው እየተከታተለ ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ባለሙያዎች ለሚፈጽሙት ችግር የበኩላቸውን ድርሻ መውሰድ አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓቱን ግልፅና ጠንካራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የትምህርት ተቋማቱ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሳይወጡ ሲቀር ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡ አሁን ላይ የሚታየው ግን ከጠንካራ እርምጃ ይልቅ ማስታመምን ትኩረት ያደረገው አካሄድ መስተካከል ይኖርበታል፡፡ በማሳሰቢያዎችና ማስጠንቀቂያዎች ለውጥና መሻሻል ካልታየ ቀጣዩን ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡
ይህን አለማድረግ አመራሮች ተጠያቂነትን ሳይፈሩ እንዳሻቸው እንዲንቀሳቀሱ ያበረታታል፡፡ አጥፊ ካልተጠየቀ በሌላው ዘንድ ‹‹የምን ይመጣል?›› እብሪት ይነግሳል፡፡ ስህተትን ዝም ብሎ የማየት አመለካከት ጉልበቱን አበርትቶ ‹‹በምን አገባኝ›› ጎዳና ተመላላሹ ይበዛል፡፡ ስለ እውነት የሚታገሉ ሰዎችንም ሞራል ይነካል፡፡ ብልሹ አሰራርና ማን አለብኝነት ይበረታል፡፡ የህዝብና የአገር ሀብት ከታሰበለት ዓላማ ውጭ ይውላል፤ይባክናል፡፡
ይህን መስመር በማስያዙ ሂደት የትምህርት ተቋማቱን በበላይነት የሚከታተለው ትምህርት ሚኒስቴር ትልቅ ድርሻ አለበት፡፡ ችግሮችን በየጊዜው ከሥር ከሥር የመፍታትን ልምዶች ማጠናከር ይኖርበታል፡፡ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓቱን ማዘመንም ይጠበቅበታል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ አለባቸው፡፡ የትምህርት ማዕከላት የመልካም ሥራ እንጂ የችግር ማሳያዎች እንዳይሆኑ መስራት ይገባል፡፡ በህዝብና በአገር ሀብት ላይ ለሚደርሰው ብክነትና ጥፋት የሚመለከታቸውን አካላት በህግ አግባብ የመጠየቁ እርምጃም ከማስጠንቀቂያ ያለፈ መሆን አለበት፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።