የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት ሊፈተሽ ይገባል

አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና፣ የልዩ ልዩ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት ማዕከል፣ ከ100 በላይ ኤምባሲዎች መቀመጫና የበርካታ ዲፕሎማቶች መኖሪያ መሆኗ በተደጋጋሚ የሚገለፅ እውነታ ነው፡፡ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በየጊዜው ወደ ከተማዋ በሚገቡ ዜጎችና ከፍተኛ በሆነው አገራችን የህዝብ ቁጥር ምጣኔ የተነሳም የከተማዋ የህዝብ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ይገኛል፡፡
በከተማዋ የሚካሄደው የመረሰተ ልማትና ሌሎች አገልግሎቶች እድገትም የአገሪቱ እድገት መጠን ማሳያ ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው፡፡ ከተማዋ በየጊዜው በሚካሄዱባት ግንባታዎች የተነሳ “ፈርሳ እየተገነባች ያለች ከተማ” ለመባል ጭምር በቅታለች፡፡
ያም ሆኖ ግን በህዝቧና በግንባታዎቿ እድገት ልክ ማደግ ያልቻለ ባህልም አላት፡፡ የከተማዋ የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት በአገሪቱ ከሚገኙ አነስተኛ ከተሞች ጭምር ወደኋላ የቀረና ደካማ ነው፡፡ በተለይ ክረምት በመጣ ቁጥር የከተማዋን የንፅህና ጉድለት አጉልቶ የሚያሳየው  የቆሻሻ ሽታ ለዚህ ማሳያ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የከተማዋን ገጽታ ከማበላሸቱም በላይ ለነዋሪው የበሽታ ምንጭ በመሆኑ ችግሩ ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡
ባለሙያዎች እንደሚመክሩት የግልና የአካባቢ ንፅህናን መጠበቅ ጤናማ ማህበረሰብን ለመፍጠር ዋነኛ መንገድ ነው፡፡ አገራችንም መከላከልን መሰረት ባደረገው የጤና ፖሊሲዋ እነዚህን ነገሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት በመላ አገሪቱ ከ39 ሺ በላይ የሚሆኑ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በማሰልጠንና በእያንዳንዱ ቀበሌ በመመደብ እየሰራች ትገኛለች፡፡
በመዲናችን ያለው የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት ግን ከዚህ በተቃረነ መልኩ ደካማ ነው፡፡ አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ ደረቅ ቆሻሻን ከቤቱ ማውጣቱ እንጂ በአግባቡ ስለመሰብሰቡና ስለመወገዱ ብዙም ትኩረት አይሰጥም፡፡ በዚህ የተነሳ በአንዳንድ ንፁህ የመኖሪያ ግቢዎች ውጭ ላይ ቆሻሻ ተከምሮ ማየት የተለመደ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ለፍሳሽ ቆሻሻ ያለው አተያይም ተመሳሳይ ነው፡፡ በርካታ መኖሪያ ቤቶችና ንግድ ቤቶች መፀዳጃ ቤቶቻቸውን ከጎርፍ ማስወገጃ ቱቦ ጋር በማገናኘት መጠቀምን እንደነውር የማይቆጥሩበት ሁኔታ ይታያል፡፡ በየመንገዱም ቱቦ ላይ ወይም አጥር ስር ጠጋ ብሎ መሽናት መብት የሚመስላቸው በርካታ ነዋሪዎች አሉ፡፡
በከተማዋ ይህንን የፅዳት ችግር ለመፍታት በመንግስት በኩል የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ከሰባት ወራት በፊት ጀምሮ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የሚሳተፉበት ወርሃዊ የፅዳት ዘመቻ ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በወቅቱም በየመንደሩ ተፈጥሮ የነበረው ተነሳሽነት አበረታች ነበር፡፡ በተለይ  ሞዴል ለሆኑ መንደሮች ሽልማት እንደሚሰጥ መገለፁን ተከትሎ  በተነሳሽነት አካባቢያቸውን የሚያፀዱና የሚያስውቡ  ነዋሪዎችን ፈጥሮ  ነበር፡፡
ነገር ግን ይህ ተነሳሽነት ዘላቂ ሊሆን አልቻለም፡፡ ይህ በዘመቻ የተጀመረ ስራ የአንድ ሰሞን ተግባር ብቻ ሆኖ እየተቀዛቀዘ ይገኛል፡፡  አሁን የምንገኝበት ወቅት ደግሞ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ አያያዝ ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡
በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች ደግሞ ከመልሶ ማልማት ጋር ተያይዞ ፈርሰው የቆዩ አካባቢዎች የቆሻሻ መጣያ ሆነዋል፡፡ ለዚህም በልደታ ክፍለ ከተማ በተለምዶ  የአሜሪካን ግቢ የሚባለው ስፍራ ማሳያ ነው፡፡ የዚህ ስፍራ ነዋሪዎች በመልሶ ማልማት ከተነሱ ከሁለት አመት በላይ ቢሆናቸውም አካባቢው እስካሁን ባለመልማቱ የቆሻሻ መጣያ ሆኗል፡፡ በዚህም የተነሳ ከአካባቢው የሚወጣው የቆሻሻ ሽታ ለበሽታ የሚያጋልጥ እንደሆነ ነዋሪዎች ያማርራሉ፡፡
ሌላው የከተማዋ ችግር የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች ሁኔታ ነው፡፡ በየቦታው የተቆፈሩት እነዚህ ቱቦዎች የጎርፍ ማስወገጃ ቱቦዎች ቢሆኑም አብዛኞቹ ግን በየመንደሩ ከመፀዳጃ ቤት ጋር በመገናኘታቸው  የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ ማስወገጃ ሆነው ይታያሉ፡፡ አብዛኞቹ ቱቦዎች ደግሞ ሞልተው ስለሚፈሱ ከተማዋንም ሲበክሉ ይስተዋላል፡፡
የአዲስ አበባ ወንዞችም የአካባቢው ነዋሪዎች የቆሻሻ መጣያ ስፍራዎች ናቸው፡፡ በነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች  ደረቅም ሆነ ፍሳሽ ቆሻሻን ወደ ወንዝ መልቀቅ ህጋዊ መብት እስኪመስላቸው ድረስ   ወንዞችን በግልፅ የቆሻሻ መጣያ ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ በዚህ የተነሳም ዝናብ በጣለ ቁጥር የከተማዋ ወንዞች ቆሻሻ ማጓጓዣ  እስኪመስሉ ድረስ ተበላሽተው ይታያሉ፡፡
በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ያለው የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት ለዘርፉ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ  የሚያሳይ ነው፡፡ በተለይ ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያዞ እንዲህ አይነት የተበላሸ የቆሻሻ አያያዝ ስርዓት አደገኛ የጤና ችግር ሊፈጠር ይችላል፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ የከተማችን ነዋሪ ቆሻሻ ዋነኛ የበሽታ ምንጭ መሆኑን በመረዳት፣ የግልም ሆነ የአካባቢውን ንፅህና መጠበቅ ይኖርበታል፡፡  ደረቅም ሆነ ፍሳሽ ቆሻሻ በአግባቡ ካልተያዘና በአግባቡ ካልተወገደ ለተላላፊ በሽታ መንስኤ በመሆኑ ከወዲሁ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።