ኢትዮጵያውያን አክሲዮኖቹን ለመቋደስ ተዘጋጁ !

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ ባካሄደው ስብሰባ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል የመንግስት ትላልቅ ኩባንያዎችን ወደ ግል ለማዛወር የደረሰበት ይገኝበታል፡፡ በመንግስት ይዞታ ስር ሲተዳደሩ የቆዩ ኢትዮ ቴሌኮምን ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን፣ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫዎችን፣የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅትን፣ የመሳሰሉ ግዙፍ ኩባንያዎችን ትልቁን የአክሲዮን ድርሻ በመያዝ ቀሪው የአክሲዮን ድርሻ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች እንዲተላለፉ ለማድረግ ነው የወሰነው፡፡ ኢህአዴግ እነዚህን ብቻም ሳይሆን በግንባታ ላይ የሚገኙትን የመንግስት የልማት ተቋማትንም ጭምር ለግሉ ዘርፍ ለማስተላለፍ ውሳኔ ላይ ደርሷል፡፡
መንግስት የደረሰበት ይህ ውሳኔ አለም አቀፍ ተቋማት ቀደም ሲል አንስቶ እንዲሆን ሲጠብቁት የነበረ እንደመሆኑ የግሉ ዘርፍም በጉጉት ሲጠብቀው የነበረ ነው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ከዚህ አንጻር የውጭ ባለሀብቶች ፍላጎት ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያስቸግርም፡፡ ይህንንም ስራ ኢህአዴግ እንዳለው በጥብቅ ጥንቃቄ የሀገርን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ማከናወን ይገባል፡፡
የውጭ ባለሀብቶቹ አክሲዮን መግዛት ሀገሪቱ በእውቀት፣በቴክኖሎጂ፣በክህሎት እና በውጭ ምንዛሬ ግኝት በኩል የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ እንደመሆኑም ታዋቂ ባለሀብቶች በአክሲዮን ግዥው እንዲሳተፉ ለማድረግ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል፡፡
ከዚህ አንጻር በኢንዱስትሪ ፓርኮች የባለሀብቶች ምልመላ ወቅት ታዋቂ ባለሀብቶችን ለመሳብ በተደረገው ጥረት የተገኘውን መልካም ተሞክሮ ጭምር ስራ ላይ በማዋል ለሀገር የሚጠቅሙ ባለሀብቶች በአክሲዮን ግዥው እንዲሳተፉ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ተግባር ማከናወንም ያስፈልጋል፡፡
ብዙ ሥራ የሚጠይቀው ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች በአክሲዮን ግዥ እንዲሳተፉ የማድረጉ ስራ ይሆናል፡፡ ለሽያጭ የሚቀርቡት ኩባንያዎች ግዙፍና በቢሊዮን ብሮች የሚጠይቁ እንደመሆናቸው በግሉ ዘርፍ ለዚህ የሚሆን የተዘጋጀ ካፒታል ሊኖር ይችላል የሚለው ያጠያይቃል፡፡
እንደሚታወቀው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲሰማሩ መንግስት በርካታ ጥረቶችን ቢያደርግም ወደ ዘርፉ የገቡት ውስን ናቸው፡፡ ባለሀብቶቹ በቀላሉ የሚተረፍበትን የአገልግሎት ዘርፍ ሙጥኝ ያሉ፣ የእውቀት፣ የክህሎትና የቴክኖሎጂ እንዲሁም የገበያ ችግር ያለባቸው እንደመሆናቸው አሁን መንግስት ይዞ የመጣውን መልካም እድል ይጠቀሙበታል ብሎ ማሰብ ለመገመት ይከብድ ይሆናል፡፡
የኩባንያዎቹ ብዙው ድርሻ የመንግስት እንደመሆኑ እነዚህ ባለሀብቶች ኩባንያዎቹን በማስተዳደር፣ በቴክኖሎጂና በክህሎት በኩል ባለሀብቱን ብዙም የሚያስጨንቁት አይሆኑም፡፡ስለሆነም ባለሀብቱ በግልም ይሁን እየተደራጀ ኩባንያዎችን በመግዛት የዚህ አክሲዮን ባለድርሻ የሚሆኑበትን ሁኔታ ለመፍጠር መንግስት አሁንም በትኩረት መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ጥቂት የማይባሉ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በተለያዩ ኩባንያዎች ውስጥ ባለአክሲዮን እንደመሆናቸው አሁንም አክሲዮኖችን በማቋቋም ይህን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ፈጥነው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት ህዝቡ አክሲዮኖችን በመግዛት ባንኮችን ኢንሹራንሶችን ወዘተ በማቋቋም አትራፊ እንደሆነ ሁሉ አሁንም ኩባንያዎችን እየመሰረተ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን አክሲዮኖች መግዛት ይችላል፡፡ በዚህም መንግስት ከፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመቋደስ ራሱንም ሀገሩንም መጥቀም ይኖርበታል፡፡
ይህ እንዲሆን ከተፈለገ የአክሲዮን ገበያዎችን በአስቸኳይ ማቋቋም ያስፈልጋል ሲሉ ባለሙያዎቹ ያስቀመጡትን ምክረ ሀሳብም ስራ ላይ ማዋል ይገባል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያውያን አይናችሁንና ቀልባችሁን የሚያውቋቸው ባለሀብቶች ላይ ብቻ ሳታደርጉ ራሳችሁም ከትንሹ አክሲዮን አንስቶ በመግዛት ባለሀብት መሆን እንደምትችሉ በመረዳት ራሳችሁን ማዘጋጀት ይኖርባችኋል፡፡ በእርግጥም ህዝቡን በዚህ አይነት መልኩ በማዘጋጀት አዳዲስ ባለሀብቶችን ጭምር በሀገሪቱ መፍጠር ይቻላል፡፡ ተሞክሮውም በሀገራችን አለ፡፡
በርካታ ኢትዮጵያውያን የባንክ ኢንሹራንስ፣ የሲሚንቶ ፋብሪካ እና የመሳሰሉትን አክሲዮኖችን በመግዛት ዛሬ ባለትርፋማ ኩባንያ ባለቤት ለመሆን በቅተዋል፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያውያን በየአመቱ የትርፍ ትርፍ ይከፋፈላሉ፡፡ የእነዚህ ኢትዮጵያውያን አኩሪ ተግባር እነሱን ጭምር ሌሎች ኢትዮጵያውያን ለእነዚህ ትርፋማ ኩባንያዎች አክሲዮን ግዥ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አቅም ይሆናሉ፡፡
እንደሚታወቀው ሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚሰሩ ባለሀብቶች በብዛት አፍርታለች፡፡ በተለያዩ የግብርናና ሌሎች ኢንቨስትመንት የህብረት ስራ ማህበራት ዛሬ በሀገራችን ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት ያንቀሳቅሳሉ፡፡ ይህ ሁሉ የሚያመለክተው እነዚህን ሃብት የሚታለቡ ኩባንያዎች እንዲሁም በቀጣይም ሊወልዱ የደረሱ ኩባንያዎችን ገዝቶ ለማለብ ባለሀብቱ መዘጋጀት አለበት፡፡
በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም የሀገሪቱን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና ማህበራዊ አቅጣጫ ምን እንደሆነ እንዲረዱ በማድረግ የልማቱ አካል እንዲሆኑ ማስቻል ይገባል፡፡ እነዚህ ዜጎች ይህን የሚረዱበትን መድረክ መፍጠርም ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንጻር መንግስት እነዚህ ኢትዮጵያውያን በስፋት ወደሚገኙባቸው ሀገሮች በመሄድ ስለሀገሪቱ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ሁኔታ ማስገንዘብ ይጠበቅበታል፡፡ በየትኛውም አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የአክሲዮኖቹ ተቋዳሽ ለመሆን ተዘጋጁ!!

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።