በየመድረኩ ማስማሉ ይብቃ!

በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል በተለይም በአባይ ወንዝ ዙሪያ ላለፉት መቶ ዓመታት መተማመን ነበር ብሎ መናገር ራስን ማሞኘት ይሆናል። ስለሆነም የአገራቱ ሚዲያዎችና ባለስልጣናት በተለይም በግብፅ በኩል ያሉቱ፤ በህዝቦች መካከል መተማመንን ለመገንባት ከመሥራት ይልቅ ፍጹም አፍራሽ በሆነ ፕሮፖጋንዳ ተጠምደው ኖረዋል። ይህ ሁኔታ አለመተማመንን በማስፋቱ የአገራቱ መሪዎች በተገናኙባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ የሚያወሩትና የሚማማሉት ተመሳሳይ ነገር ሆኖ ዛሬም ድረስ ዘልቀናል።
ኢትዮጵያዊያን በታሪካቸው አብረው መዋኘትን እንጂ ተያይዘው መስመጥን የማይመርጡ ህዝቦች ናቸው። ይህን ደግሞ ግብፆችም፤ ዓለምም የሚያውቀው ሀቅ ነው። ለዚያም ነው የጎረቤቶቻችን ሰላም የእኛም ሰላም ነው፤ የጎረቤቶቻችን በሽብር መጠቃት የእኛም ጥቃት ነው በሚል ሰላም አስከባሪና ተዋጊ ወታደር ሳይቀር በመላክ ለጎረቤት አገራት ወንድሞችና እህቶች ሰላምና ፀጥታ የምንቆስለው፤ የምንሞተው። ከዚህ መለስ ያለው ሁሉ ለኢትዮጵያዊያን በጣም ቀላልና በሰጥቶ መቀበል የሚፈታ ነው ብለን እናምናለን፤ እንታመናለንም። የአባይ ወንዝም በዚህ አግባብ የሚታይ ነው።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሰሞኑን ለግብፃዊያን፤ «እኛ ኢትዮጵያዊያን ወንድምነትና ጉርብትና የምናውቅ ደግሞም እግዚአብሔርን የምንፈራ ህዝብና አገር ነን። ስለሆንም ነው መተኪያ ለሌለው ህይወታችን እንኳ ሳንሳሳ ለሰው አገር ሰላምና ጸጥታ ሰላም አስከባሪ ኃይል በመላክ አፍሪካዊ ኃላፊነታችንን እየተወጣን ያለነው። እውነታው ይሄ በመሆኑም በረሃ ለሚበላው የወንዝ ውሃ የምንሰስትበትና ‹እኛ ብቻ እንልማ› የምንልበት ምንም ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሠራሽ ምክንያት የለንም›› ሲሉ የገለጹት የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ትክክለኛ አቋም የሚያንጸባርቅ ነው፡፡
‹‹የአባይን ወንዝ ለግብፅ፤ ለሱዳን እና ለኢትዮጵያ ካለው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አንጻር በጋራ አልምተን በጋራ መጠቀም ቢገባንም፤ ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ሲጣል እንዳሉት፤ በአባይ ወንዝ ዙሪያ አብሮ መሥራት ስላልተለመደ በወንዙ ላይ ግድቡን ብቻችንን እየገነባን እንገኛለን። ለብቻችን ወገባችንን አጉብጠን እየገነባን ብንሆንም «እኛ ብቻ እንጠቀም» የሚል አገራዊም፣ ግለሰባዊም አመለካከትና አቋም ዛሬም ድረስ የለንም። ይህንን ደግሞ ገና የግደቡ መሰረት ድንጋይ ሲጣል ጀምሮ የተናገርነው፤ ቃል የገባነው ሀቅ ነው። ይህ የማይናወጥ የምንጊዜም አቋማችን ስለሆነም ጭምር ነው በታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ጊዜ፣ በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ዘመን እና አሁንም በዶክተር አብይ የስልጣን ዘመን ላይ ምንም ዓይነት የአቋም ለውጥ ሳናደርግ ለግብፅ ህዝብ እያረጋገጥን ያለነው።
የግብፅ ህዝብ ከእኛ ጋር ተመሳሳይ አቋምና አመለካከት እንዳለው በአንድ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩ የግብፅ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባላት ነግረውናል። ነገር ግን የግብፅ አንዳንድ ምሁራን ከሳይንሳዊ ምክንያት ይልቅ በመላምት በማመን ህዝቡን ግራ እያጋቡት ዛሬም ደረስ ቀጥለዋል። ዶክተር አብይ በካይሮው መግለጫቸው፤ እንደዚህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ምሁራንና ሚዲያዎች ሳይንሳዊ ካልሆነ አፍራሽ አካሄዳቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል። ይህ ተገቢ ማሳሰቢያ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግብፆች የመጀመሪያም የመጨረሻም ፍላጎትና ጥያቄ በሆነው በአባይ ወንዝ ዙሪያ የኢትዮጵያን የማይናወጥና በዘመናት የማይቀየረውን አቋም ደግመው ነግረዋቸዋል። ባልተለመደ መልኩም በአረብኛ ቋንቋ ሳይቀር ኢትዮጵያ ግብፅን ውሃ እንደማታስጠማ አረጋግጠውላቸዋል። ይህ የግብፅ ‹‹አሁንም አሁንም ንገሩኝና ማሉልኝ›› አካሄድ ያበቃ ዘንድም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለሁለቱም አገራት የመንግሥት ኃላፊዎችና የመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ለግብፅ ህዝብ ማለት ያለባቸውን ብለዋል።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት የእኛም መልዕክት ነው። «ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው» እንዲል ብሂሉ፤ የግብፅ መገናኛ ብዙሃን በፈጠራ ወሬ በይሆናል ዘገባ ህዝቡን ግራ ከማጋባት መታቀብ አለባቸው። የግብፅን ህዝብ ውሃ የማስጠማት ፍላጎት በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ዘንድ በፍጹም እንደሌለ ሊታወቅ ይገባል። እውነታው ይሄ ነው፡፡ መዘገብ ያለበትም ይህ የኢትዮጵያ አቋም ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በአሉባልታ የሚሠራ ዘገባ የሁለቱን አገራት ወንድምና እህት ህዝብ ቢያቃቅር፤ ቢያለያይ እንጂ ለግብፅም ሆነ ለኢትዮጵያ ጠብ የሚል አንዳች ነገር የለውም። እኛ ኢትዮጵያዊያን ፍቅርንም ጸብንም አሳምረን የምናውቅ ህዝብና አገር መሆናችንም ከግምት ውስጥ ቢገባ መልካም ነው።
ከግብፅ ህዝብ ይሁንታ ውጪ በስልጣን ላይ የነበሩ የአገሪቱ መሪዎች የስልጣን ጊዜያቸውን ለማራዘም፤ መገናኛ ብዙሃንም ገቢያቸውን ብቻ ታሳቢ በማድረግ እውነት ባልሆነ ጯሂ ዘገባ የተነሳ በሁለቱ አገራት ህዝቦች መካከል አለመተማመንን አንግሠው ኖረዋል። ይህ አለመተማመን ግን ምንም ዓይነት የወንዝ ዳር መሀላ ሳያስፈልገው በሁለትና በሦስት ዓመታት ከግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ጋር አብሮ ይቋጫል። እስከዚያው ድረስ ግን እውነት እውነቱ ብቻ ቢዘገብና ቢነገር ለሁለቱም አገር ህዝብ ይጠቅማልና ሁሉም ወገኖች በዚህ ዙሪያ ብቻ ይሥሩ። በየመድረኩ መማማሉም ይብቃ።

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።