የህግ የበላይነትን የማስጠበቅ ስራ ይጠናከር

ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ በተለያዩ አገራችን ክፍሎች ተከስቶ የነበረው ሁከትና ብጥብጥ ቀንሶ በአብዛኛው የአገራችን ክፍሎች አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል፡፡ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ የነበረው ሰላም ከሞላ ጎደል እየተሻሻለ የመጣበት ሁኔታ አበረታች ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን አሁንም ቢሆን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚቀሰቀሱ ግጭቶችና የዜጎች መፈናቀል ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ አፋጣኝ መፍትሄ ካልተሰጠውና በአጭሩ ካልተቀጨ ዘላቂ ሰላማችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩ አይቀርም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የህግ የበላይነትን የሚፈታተኑ ተግባራትም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ በተለይ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚፈፀሙ የወንጀል ድርጊቶችን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ከዚህ ቀደም ከሞላ ጎደል ቀንሰው የነበሩ የዝርፊያና የስርቆት እንዲሁም የቡድን ግጭቶች በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በተለይ በአዲስ አበባ አልፎ አልፎ ይታያሉ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ አንዳንድ ነጋዴዎች ህግ የሌለ እስኪመስል ድረስ ዋጋን እንደፈለጉ የመወሰንና ገበያን የማዛባት እንቅስቃሴ ውስጥም ገብተው ይታያሉ፡፡ እነዚህና ሌሎች ግጭቶችና የህግ የበላይነትን የሚፈታተኑ ተግባራትም መንግስት ገና በርካታ ስራዎች እንደሚጠበቅበት የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ የእነዚህ ግጭቶችና የዝርፊያ ተግባራት መንስኤ ስንመለከት ደግሞ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት መንግስት እየሰጠ ያለውን ይቅርታ በተዛባ መንገድ በመተርጎም ከዚህ በኋላ ተጠያቂነት የለም ከሚል የተዛባ ዝንባሌ ህገወጥ ተግባራትን የሚፈጽሙ አካላት ተበራክተዋል፡፡
በተለያዩ የፍትሐብሄርና የወንጀል ክሶች ተጠርጥረው ክሳቸው በሂደት ላይ ያሉ ዜጎች ክሳቸው እንዲቋረጥና ከእስር እንዲፈቱ እንዲሁም በተለያዩ የክስ መዝገቦች የተፈረደባቸውን ጨምሮ በርካታ ታራሚዎችን በይቅርታ መፍታቱን በአወንታዊ ጎኑ የሚመለከቱ በርካታ የአገራችን ህዝቦች ቢኖሩም ጥቂቶች ደግሞ ይህንን የመንግስት ውሳኔ በተሳሳተ መልኩ በመተርጎም የህግ የበላይነት እየተዳከመ የመጣበት ሁኔታ እንዳለ የሚናገሩም አልጠፉም፡፡
መንግስት በማረሚያ ቤት የነበሩ የህግ ታራሚዎችና ተጠርጣሪዎችን ሲፈታ የህግ የበላይነት እንዲሸረሸር ሳይሆን በአንድ በኩል የተጀመረውን የይቅርታ መንፈስ በሙሉ ልብ በመፈፀም ሁሉም ከባለፈው ትምህርት ወስዶ በአዲስ መንፈስ ለስራ እንዲነሳሳና የአንድነትና የፍቅር ባህል እንዲጎለብት በሌላ በኩል ደግሞ ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ውስጥ ጉድለት የነበራባቸው አንዳንድ አሰራሮች በመኖራቸው እነዚህን ለማስተካከል እድል እንዲሰጥ ታስቦ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ነገር ግን በወንጀልም ሆነ በፍትሐብሄር ህግ ጥሶ የተገኘ አካል አሁንም ቢሆን ከተጠያቂነት እንደማይድን መታወቅ አለበት፡፡ በተለይ በህዝብ መካከል ሆነው ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨትና የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማግለል የሚፈፀም የዘረኝነትና የወንጀል ድርጊት ዛሬም ሆነ ወደፊት በይቅርታ የሚታለፍ አለመሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች በራሳቸው የተጀመረውን የይቅርታ በጎ አሰራር የሚያኮላሹ በመሆናቸው መንግስትም ሆነ ህብረተሰቡ በፅኑ የሚታገላቸው ናቸው፡፡
ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሶሳ ከተማ የ15 ሰዎች ህይወት የተቀጠፈበት እና የበርካታ ዜጎች መፈናቀል የተከሰተበት ድርጊት በብዙኃኑ ሰላም ፈላጊ ህዝብ የተፈፀመ ሳይሆን በጥቂት ቡድኖች አስተባባሪነት የተፈፀመ እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ በዚህ የሁከትና ብጥብጥ ተግባር ውስጥ እጃቸው የተገኘ ማንኛውም አካል ለፍርድ ቀርቦ ተገቢውን ቅጣት እንደሚያገኝም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስታውቀዋል፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታም በአመራር ላይ ያሉ አካላትን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ተይዘው ጉዳያቸው እየተጣራ ነው፡፡
በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎችም ዜጎች ከኖሩበት ቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ ያደረጉ አመራሮችና ሌሎች እጃቸው በዚህ ችግር ውስጥ እንዳለ የተጠረጠሩ አካላት ከስራቸው ታግደው ጉዳያቸውም በህግ እየተጣራ ያለበት ሁኔታ አለ፡፡ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልልም ተመሳሳይ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው፡፡ በተለይ በቅርቡ የፊቼ ጫምባላላ በአል በሚከበርበት ወቅት በተፈጠረው ግጭት ከአስር የማያንሱ ሰዎች መሞታቸውና በርካታ ዜጎችም ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸውን ተከትሎ የክልሉ ከፍተኛ የድርጅትና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል፡፡
በአጠቃላይ አሁን አገራችን ያለችበት ሁኔታ አንጻራዊ ሰላም የሰፈነበትና ከዚህ ቀደም ያጋጠሙንን ችግሮች ሁሉ ወደኋላ ጥለን ስለወደፊቱ ብሩህ ተስፋ የምናልምበት የይቅርታ፣ የፍቅርና የአንድነት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ደግሞ ከሁከትና ከብጥብጥ በመራቅ መጪውን ጊዜያችንን ብሩህ ለማድረግ የእያንዳንዱ ዜጋ ብርቱ ጥረትና ርብርብ ያስፈልጋል፡፡ለዚህ ደግሞ የህግ የበላይነት በማክበርና በማስከበር መንግስት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ላይ የተጀመረው የአመራር ክፍተት ያሳዩ ኃላፊዎች ተጠያቂ የማድረግ ስራም አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።