የውስጥ ሠላምን የጎረቤት አጋርነትንም ማጠንከሩ ይቀጥል !

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ 100 ኛ ቀናቸውን ትናንት አስቆጥረዋል፡፡ እርሳቸው ወደ ስልጣን የመጡት በአገሪቱ ለሦስት ዓመታት አንዴ ጠንከር አንዴ ላላ እያለ የዘለቀው የሠላም መደፍረስ ከፍተኛ አደጋ በደቀነበት ወቅት ነበር፡፡
ኢትዮጵያ የምትገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና አስተማማኝ ሠላም የሚታይበት አይደለም፡፡ ሶማሊያ ለዓመታት የአሸባሪዎች መናኸርያ ከመሆኗም ባሻገር ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት የላትም፡፡ ደቡብ ሱዳን በእርስ በርስ ግጭት የምትታመስ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ባደረገችው ደም አፋሳሽ የድንበር ግጭት ምክንያት ሞት አልባ ጦርነት ላይ ነበረች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አጭር በሚባል ጊዜ አገሪቱን የመበታተን ጫፍ ላይ አድርሰዋት የቆዩ የተጠራቀሙ ችግሮች እንዲፈቱ እንዲሁም፤ ህዝብን ለምሬት የዳረጉ ብሶቶች እንዲቀንሱ በቁርጠኛ አመራራቸው ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ ተስፋ ሰጪው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ወደ ኋላ እንዳይመለስ የሚያግዙ አቅጣጫዎችን ጠቁመዋል፤ ተግብረዋል፡፡ በመልካም አንደበታቸው ለመላው ህዝብ ተስፋንና ብሩህ ዘመናትን አመላክተዋል፡፡ በይቅር ባይነት የሚሻር መጥፎ ጠባሳ መኖሩን አስተምረዋል፡፡ የእስከዛሬው ቆይታቸውም በደማቅ ስኬት የታጀበ ሲሆን፤ ቀጣይ የቤት ሥራዎች መኖራቸው አይካድም፡፡
ኢትዮጵያ ከፊት የሚጠብቃት ወሳኝ የቤት ሥራ ለመወጣት የውስጥ ሠላሟን ማረጋገጥና ከቀጣናዊ መረጋጋት የሚገኘውን ትሩፋት ለማጣጣም ይቻል ዘንድ የድርሻዋን ማበርከት አለባት፡፡
በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በመቶ ቀናት ጉዟቸው ሠላም ርቋት የነበረችውን አገር ለማረጋጋት ያደረጉት አድካሚ ጥረት ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ነው፡፡ በጅግጅጋ፣ አምቦ፣ መቀሌ፣ ጎንደር፣ ባህር ዳር፣ ሀዋሳ፣ ባሌ፣ ደንቢዶሎ፣ አሶሳ፣ ጋምቤላ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ወልቂጤና አፋር ከተሞች የሠላም መልእክት አንግበው ኅብረተሰቡን አወያይተዋል፡፡ችግሩን አዳምጠው ስለ መፍትሄው መክረዋል፡፡
በተደረገው ጥረት አሁን በብዙ የአገሪቱ አካባቢዎች አንጻራዊ ሠላም ቢሰፍንም፤ በተለያዩ ስፍራዎች ብሄርን መሰረት አድርገው የሚታዩ ግጭቶች ሙሉ ለሙሉ አልቆሙም፡፡ የተጀመረው ለውጥ ሙሉ እርካታን ያጎናጽፍ ዘንድ ችግሮችን ከምንጫቸው በመፈተሽ መፍትሄ መስጠት ይገባል፡፡ በተለይ በየክልሉ ለውጡ ያልተዋጠላቸው በስርዓቱ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ሲያጋብሱ የነበሩ አመራሮች ወንበራቸው ሳይነቀነቅ ለመዝለቅ ግጭትን እንደ እድሜ ማሰንበቻ ስልት ሊጠቀሙበት ስለሚችል ምርቱን ከግርዱ መለየት ያስፈልጋል፡፡
ላለፉት ዓመታት ዜጎች ለውጥ ያስፈልጋል በሚል መንፈስ በተለያየ መንገድ ሀሳባቸውን ሲገልጹና ሲታገሉ የቆዩት የእነርሱ መብት ተከብሮ የሌሎች እንዲጣስ አይደለም፡፡ ስለሆነም በአገሪቱ ዘላቂ ሠላም ይሰፍን ዘንድ የዞረ ድምር አለ በሚል የተሳሳተ ስሌት ለብቀላ መነሳቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ መደመር በሚል ጽንሰ ሀሳብ ያለመታከት ካስተላለፉት መልእክት በተቃራኒ መቆም ነው፡፡ መደመር ያለ ዘር ልዩነት በአንድ ላይ በመቆም የጋራ ቤታችን የሆነችውን ኢትዮጵያ ህዳሴ እውን ማድረግ ነውና በየስፍራው የሚንጸባረቀው የልዩነት ግንብ ሊፈርስ ይገባል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በቅርብም በሩቅም ከሚገኙ የኢትዮጵያ ስትራቴጂክ አጋር ወደ ሆኑ አገሮች አቅንተው በጋራ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ግብጽ፣ ሶማሊያ፣ ዩጋንዳና ኤርትራ ከመካከለኛው ምስራቅ ደግሞ ሳዑዲ ዓረቢያና ዩናይትድ ዓረብ ኢሜሬቶችን ጎብኝተዋል። በተለይ ከኤርትራ ጋር የሞት አልባ ጦርነት ሁኔታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመዝጋት የወሰዱት ቁርጠኛ አቋም ለዓመታት ተራርቀው የኖሩትን ህዝቦች ለማቀራረብ፣ መልካም ጉርብትና የሚያስገኘውን ትሩፋት ለመቋደስ የሚያስችል በመሆኑ ከፍተኛ አድናቆት የተቸረው ነው፡፡
ከጎረቤትና ከስትራቴጂክ አጋር አገሮች ጋር የሚካሄደው ጠንካራ ግንኙነት ጠቀሜታው የበዛ ነው፡፡ በወደብና በየብስ የሚደረገው ግንኙነት የጋራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ያሳድጋል፡፡ በተለያዩ የኢኮኖሚ መስኮች በጋራ ለማደግና ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ የበኩሉን ሚና ይጫወታል፡፡ ከምንም በላይ አገሪቱ ሰላሟ የተረጋገጠ እንዲሆን በጸጥታ ረገድ የሚያበረክተው ሚና ጉልህ በመሆኑ በተጀመረው ልክ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
ኢትዮጵያ የጀመረችው የህዳሴ ጉዞ መድረሻው ሩቅ በመሆኑ ከምንም በላይ ከውስጥ የሚመነጭ ሠላም ለአካባቢ ይተርፋልና መላው ኅብረተሰብ ሠላሙን በማስጠበቅ፤ ከጎረቤት አገራት ጋር በጋራ ለማደግ ለሚደረገው ጥረት የበኩሉን ያበርክት፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።