ኢኮኖሚ

አገሪቱ ከስጋቶች ይልቅ...

ከስድስት ወራት በፊት ነበር ስታንዳርድና ፑርስ፣ ፊች እና ሙዲስ የተባሉ ዓለም አቀፍ የምዘና ደርጅቶች የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ በተለይም ለኢንቨስትመንት ያላትን ምቹነት፣ የእዳ ጫናዋን፣ የሀብት ክፍፍልን፣ እና የመሳሰሉ ነጥቦችን በትኩረት...

You are here: Homeአዲስ ዘመንኢኮኖሚሞሪንጋ ለብዙዎች የገቢ ምንጭና ምግብ እየሆነ ነው

ሞሪንጋ ለብዙዎች የገቢ ምንጭና ምግብ እየሆነ ነው

የሥነ ምግብ ባለሞያዎች ተዓምረኛውና አስደናቂው ዛፍ ይሉታል። የአልሚ ምግቦች ግምጃ ቤት ሲሉትም ይደመጣል። ፀረ በሽታ እያሉም ይጠሩታል-ሽፈራውን (ሞሪንጋን) ሞሪንጋ ዛፍ የተለያዩ ለሰውነት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን(አልሚ ምግቦችን) ከመያዙም በላይ የተለያዩ በሽታዎችን የመፈወስ ኃይል አለው። ሞሪንጋ ሰዎች ጤናማ የሰውነት አካል እንዲኖራቸው የሚያስፈልጉንን ንጥረ ነገሮች ሁሉ በውስጡ አካትቶ ከመያዙም ባሻገር እንደ ተጨማሪ ምግብነት የሚጠቅም ነው።
ሞሪንጋ ለምግብነት የሚውለው በጎመን መልክና ከደረቀ በኋላ ደግሞ በዱቄት መልክ በማዘጋጀት ሲሆን፤ ሞሪንጋን በለጋነቱ መመገብ ከሌሎች አልሚ ምግቦች የሚበልጥ የምግብ ንጥረ ነገሮችን አካትቶ የያዘ ነው። ለምሳሌ በቫይታሚን ከበለፀጉ እንክብሎች ጋር በግራም ሲነፃፀር ሦስት እጥፍ የብረት ማዕድንና ሁለት እጥፍ ፕሮቲን አለው። እንዲሁም ከካሮት ከሚገኘው ቫይታሚን አራት እጥፍ፣ ከብርቱካን ከሚገኘው ቫይታሚን ሲ ሰባት እጥፍ፣ ከሙዝ ከሚገኘው ካልሲም ሦስት እጥፍ፣ ከወተት ከሚገኘው ካልሲም አራት እጥፍ፤ ከእንቁላል ከሚገኘው ፕሮቲን ተመሳሳይ፤ ከድንች ከሚገኘው ስታርች ሦስት እጥፍ በሞሪንጋ  ውስጥ ይገኛል።
ከ300 በላይ ለሆኑ በሽታዎችም መድኃኒት ይሆናል። ለአብነት ያህል የደም ግፊትን ኮሊስትሮል የስኳር በሽታን የመከላከልና የመፈወስ ኃይል አለው። ለምግብ ዘይትነትም ይውላል።ውሃንም ያጣራል። ሌሎችም ጥቅሞች አሉት። ይህ የተክል ዝርያ ኢትዮጵያ በስፋት በማልማት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥም ሆነ ለውጭ ገበያ በማቅረብ  ብዙ ጥቅም ማግኘት ሲቻል ሳትጠቀምበት ቆይታለች። አሁን ግን ሁኔታዎች እየተለወጡ ናቸው። ሞሪንጋን በምግብነት የማዋል ሁኔታዎች እየታዩ ነው። ሞሪንጋን አዘጋጅቶ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ የሆኑ ወጣቶች እየተበራከቱ ናቸው።
«ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ ስንጀምር ቅጠል ለቃሚዎች ሰልጥነው ሥራ ጀመሩ እያሉ የሚያጥላሉን ሰዎች ነበሩ ። በወቅቱ እኛ ግን መጥላላቱን ወደ ጎን በመተው የሽፈራውን( የሞሪንጋን) ቅጠል ከአርሶ አደሩ በመግዛት ለገበያ የማቅረቡን ሥራ ተያያዝነው» የምትለው በትግራይ ክልል አላማጣ ወረዳ ነዋሪ የሆነችው ወጣት ፍቅርአዲስ ወርቁ  ናት፡፡ ዛሬ እንደእዚያ ይሉን የነበሩት ሰዎች ተጠቃሚነታችንን ሲያዩ  እነርሱም እንደኛ  ተደራጅተው ሞሪንጋን ለሽያጭ በማቅረበ የበረከቱ ተቋዳሽ እየሆኑ ይገኛሉ ስትል ነው የገለጸችልን።
ከ2002ዓ.ም ጀምሮ እርሷን ጨምሮ የአካባቢው ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው  የሞሪንጋን ቅጠል ከአርሶ አደሩ እየገዙ በማዘጋጀት ለአካባቢው ኅብረተሰብና አዲስ አበባ አምጥቶ በመሸጥ የንግድ ሥራ መጀመራቸውን ታስታውሳለች። ስንጀምር  የግብርና ምርምር  ኢንስትቲዩት ስልጠና ሰጥቶንና የገበያ ትስስር ስለፈጠርልን፤ ቀሰ በቀስ ኅብረተሰቡም የሞሪንጋን ጥቅም እያወቀው ስለመጣ የእኛም ገቢ በእዚሁ ልክ እያደገ መጣ ስትል ታብራራለች። ሥራ እንደጀመርን አካባቢ አንዱን ኪሎ በሰባ ብር  ሸጠናል ትላለች። አንድ የማህበሩ አባል በወር ሦስትና አራት ኪሎ ሞሪንጋ እንደሚሸጥ የምትናገረው ወጣቷ በአሁኑ ጊዜ ሞሪንጋን ለምግብና ለመድኃኒት አገልግሎት የሚጠቀመው ሰው እየጨመረ በመምጣቱ በአሁኑ ጊዜ አንድ ኪሎ ሞሪንጋ 120 ብር እየሸጡና በየሦስት ወሩም እርሷን ጨምሮ አንድ የማህበሩ አባል ከሦስት ኩንታል በላይ ሞሪንጋ ለገበያ እንደሚ ያቀርቡ ነግራናለች።
ወጣት ፍቅርአዲስ እንዳለችው፤ የሞሪንጋ ጠቀሜታ በኅብረተሰቡ ዘንድ እውቅና ባገኘ  ቁጥር ገበያውም እየተስፋፋ መጥቷል። የእኛም ሆነ የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነታችን እየጨመረ ነው። እኛም የሞሪንጋን ምርት አዘጋ ጅተን ለገበያ ከማቅረብ ባሻገር በጎመን መልክ አዘጋጅተን ለምግብ እየተ ጠቀምንበት ነው። በሾርባ፣ በሳምቡሳ፣ በሻይና በጎመን መልክ በማዘጋጀት ለምግብ አገልግሎት እየዋለ ይገኛል።
ከሞሪንጋ ሽያጭ  በአማካይ አንድ ሰው በወር ስምንት ሺ ብር  ያገኛል የምትለዋ ወጣቷ የተጠቃ ሚው ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የማህበሩ አባላ ትም ተጠቃ ሚነታቸው እያደገ መሆኑን አመልክታ ለች። ሕዝቡም ጥቅሙን እያጣጣመው በመሆኑ በወረ ው የሞሪንጋ ዛፍ ቁጥር ከዓመት ዓመት መጨመሩን ጠቁማለች። እርሷም በግሏ ባላት መሬት ሃምሳ የሞሪንጋ  ችግኝ እያለማች መሆኗን ነው የነገረችን።
 ወጣት የውብዳር ደሳለኝም  የፍቅርአዲስን ሃሳብ ትጋራለች። ሞሪንጋ ለእኔ ትልቅ ትርጉም ያለው ተክል ነው የምትለው ወጣቷ፤ መጀመሪያ ላይ ተደራጅተን ሞሪንጋን ከአርሶ አደሩ ተረክበን በማዘጋጀት ገበያ ስናቀርብ ብዙም ፈላጊ አልነበረውም። እኛም ተስፋ ሳንቆርጥ በመስራታችን ዛሬ በሞሪንጋ ንግድ ሀብት ማፍራት ችለናል።አርሶ አደሩም ተጠቃሚ እየሆነ ነው። ሞሪንጋን በማዘጋጀት ገበያ ማቅረብ ከጀመርኩ ወዲህ ሦስት ዓመት ሆኖኛል።በእዚህ ጊዜ ውስጥ ከሞሪንጋ ንግድ በማገኘው ገቢ ሁለት ክፍል ቤት ሰርቻለሁ። ቤተሰቦቸን እያስተዳደርኩ ነው ስትል ትገልጻለች።
አንድ  ጆንያ ሞሪንጋ በ120ብር ከአርሶ አደሩ እንረከባለን። ይህን በተሸከሸከ ጌሾ መልክ በማዘጋጀት ለገበያ እናቀርበዋለን ያለችው ወጣት የውብ ዳር፣ አንዱን  ኪሎ 160 ብር በመሸጥ ተጠቃሚ እየሆኑ መሆናቸውን ታብራራለች።
 በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት የቴክኖሎጂ ማስፋፋት አስተባባሪና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሞሪንጋ  ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ካሌብ ቀለሙ እንዳሉት፤የፕሮጀክቱ ዓላማ በሀገር  አቀፍ ደረጃ የሞሪንጋን እሴት ሰንሰለት መዘርጋትና ማጠናከር ነው። ባለፉት አራት ዓመታት  ምርቱንና የገበያ ሥርዓቱን መዘርጋት የሚያስችል ፕሮጀክት ሲተገበር ቆይቷል።ይህ ፕሮጀክት ውጤታማ ሆኖ በፊት የማይታወቀው ሞሪንጋ አሁን በአዲስ አበባ ሳይቀር ተፈላጊነቱ እየጨመረ ነው።የሞሪንጋን ችግኝ የሚተክሉና ምርቱን የሚያከፋፍሉ  ሰዎች የጥቅሙ ተጋሪ እየሆኑ ናቸው።
ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በፕሮጀክቱ ታቅፈው በርካታ ወጣቶች ሞሪንጋን ለሽያጭ በማቅረብ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከማስተዳደር ባለፈ ሀብት እያፈሩ ይገኛሉ ያሉት አቶ ካሌብ፤  ቀደም ሲል ሞሪንጋ ዛፍ ጥቅሙ ባለመታወቁ ለጥላና ለአጥር አገልግሎት ብቻ የሚውል ዛፍ ነበር። አሁን ግን ከፍተኛ ዋጋ ያለው በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈለግ ሆኗል ነው ያሉት።
 በሌሎች የአፍሪካም ሆነ የእስያ ሀገሮች ሞሪንጋ ለምግብ አገልግሎት ከመዋሉ በተጨማሪ  ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ምርት ነው። በሀገራችን ግን ገና ብዙ አልተሰራበትም። ከጥቅሙ ተጋሪ ለመሆን በኢትዮጵያ ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ ሞሪንጋን በማምረት ያለውን  አቅም   ለመጠቀም መጀመሪያ የከተማውና የገጠሩ ሕዝብ ጥቅሙን ማወቅ አለበት።በፕሮጀክቱም ይህን የማስተዋወቅ ሥራ ነው የተሠራው። አሁን በአዲስ አበባ ገበያ ላይ እንደሚታየው አንድ ኪሎ ግራም ሞሪንጋ በትንሹ 160 ብር ይሸጣል።
ሞሪንጋ  ለሰዎች አስፈላጊ ንጥረ ነገሮች አሟልቶ የያዘ ነው ያሉት አስተባባሪው፤ ተክሉን ሰዎች ከምግብነት ባለፈ ለመድኃኒት ይጠቀሙበታል። ስኳር፣ደም ግፊት፣ የልብ ችግር ላለባቸው ሰዎች ሞሪንጋን ሲጠቀሙ የተሻለ ለውጥ እያሳዩ መሆኑን ነግረውናል።ስለዚህ ከጤናም አንፃር ትልቅ ጥቅም ያለው ተክል መሆኑን ያብራራሉ። በቀጣይ በሀገሪቱ የተጠናከረ  የሞሪንጋን እሴት ሰንሰለት በመፍጠር ምርቱን በሀገር አቀፍ ደረጃ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያ የሚቀርብበትና ሀገሪቱም ተጠቃሚ የምትሆንበት ሥራዎች እንደሚሰሩ ነው ያመለከቱት።
 ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው  በትግራይ ክልል አላማጣና ሌሎች ወረዳዎች በአማራ ክልል ባህርዳር፣ ደሴ፣ ሽዋሮቢት  በኦሮሚያ ክልል አዳማ፣ ሎሚ፣ ያቢሎ በደቡብ ክልል በምዕራብ አባያ፣ አርባ ምንጭ፣ ደራሼ፣ ኮንሶ እንዲሁም በድሬዳዋ አስተዳደር በተመረጡ ወረዳዎች ሞሪንጋ  የብዙ አርሶ አደሮችና ወጣቶች ከፍተኛ የሆነ የገቢ ምንጭ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ዛፎች ሁሉ ደርቀው ሳለ አንዲት ዛፍ ብቻ አረንጓዴ ሆና ትታይ ነበር፤ ይህችም የሞሪንጋ ዛፍ ናት። የእዚህን ዛፍ ጠቀሜታ ያወቀ ህብረተሰብ ቢኖር ኖሮ ረሃብ አይከሰትም ነበር ሲል  የድርቁን ሁኔታ ለመዘገብ የሄደ አንድ ጋዜጠኛ አስተያየቱን መሰንዘሩን አቶ ካሌብ ያስታውሳሉ።
ሞሪንጋ እጅግ ደረቅና በተጎዳ መሬት ላይ የሚበቅል ተክል በመሆኑ ድርቅን የመቋቋም ባህሪውም የምግብ ዋስትናን ብቻ ሳይሆን የስነ ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ከሚያስችሉ ዕፅዋቶች ተመራጭ እንደሆነ ነው የተናገሩት።የምግብ ዋስትናን ችግር ይህን ተክል በስፋት በማልማት  ማረጋገጥ ይቻላል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት የደን ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ውባለም ታደሰ  እንዳሉት፤ ሞሪንጋን ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል የኮንሶ ማኅበረሰቦች ለረጅም ጊዜ ለምግብነት የሚያውሉት ሀገር በቀል የዛፍ ዝርያ ነው። ዝርያው ከኮንሶ ውጪ በኢትዮጵያ ዝናብ አጠር በሆኑ  ደረቃማ አካባቢዎች ተስፋፍቶ ቢገኘም የአካባቢው ሰዎች በዛፍ ጥላነትና በአጥርነት ከመጠቀም ውጪ የጥቅሙ ተካፋይ አልሆኑም። ኢንስትቲዩት ይህን በመረዳት ባለፉት አራት ዓመታት  የሞሪንጋ ዝርያ በሚገኘባቸው አካባቢዎች የማስተዋወቅ ሥራ በስፋት በመስራት አሁን የሞሪንጋ ጥቅም በኅብረተሰቡ እየታወቀ ይገኛል።ኢንስትቲዩቱም  የሞሪንጋ ዛፍ ዘር በየዓመቱ ከ200ኪሎ ግራም በላይ  ያሰራጫል። ፕሮጀክቱ ተደራሽ በሆነባቸው አካባቢዎች በሚፈለገው መልኩ ባይሆንም ኅብረተሰቡ ሞሪንጋን በምግብንት እየተጠቀመበት ነው።
ሞሪንጋ ከእንቁላል፣ከወተት፣ ከስጋ፣ ከፍራፍሬ የሚበልጥ ንጥረ ነገሮችን የያዘ ነው።እናም ኢንስትቲዩቱ የሞሪንጋን ልማት በማስፋፋት ኅብረተሰቡን በብዙ መልኩ ተጠቃሚ ለማድረግ ይሠራል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ከ60 በመቶ በላይ የሀገሪቱ ክፍል ሞቃታማ  ነው። ይህም ለሞሪንጋ ልማት ተስማሚ አካባቢ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ። ይሁንና እስካሁን ኢትዮጵያ ከሞሪንጋ የምታገኘው ጥቅም ከሌሎች ማለትም ከሕንድ፣ ከኬንያ፣ ከጋና፣ ከላቲን አሜሪካ ሀገሮች ጋር ሲነጻጸር በጣም አነስተኛ ነው። እነዚህ ሀገሮች ሞሪንጋን ከምግብነት በተጨማሪ  መድኃኒቶች፣ቅባቶችንና ሎሽኖችን እያመረቱ ለገበያ ያቀርባሉ።ስለዚህ ሀገሪቱ ያላት ሞሪንጋን የማልማት እምቅ አቅም በመጠቀምና የምርምር አድማሷን በማስፋት ከሞሪንጋ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን በቀጣይ ትኩረት በመስጠት መሠራት እንዳለበት ሳይጠቅሱ አላለፉም።
 በኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው ሰው ተመጣጣኝ ምግብ አይመገብም። በተለይ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በየቀኑ ከሚመገቡት ምግቦች በቂ የሆነ የካሎሪ መጠን የማያገኙበት ሁኔታ አለ።ሞሪንጋን ለምግብነት የመጠቀም ባህልን በማጎልበትም ችግሩን በቀላሉ ማቃለል ይቻላል ሲሉ ያስረዳሉ። እናም ኅብረተሰቡ ሞሪንጋን ለምግብነት የማዋል ልምዱን በማዳበር ጤናውን መጠበቅ እንደሚችል ባለሙያው ምክራቸውን ለግሰዋል። በዓለም ላይ 13 የሚሆኑ የሞሪንጋ ዝርያዎች እንዳሉ ጥናቶች ያረጋግጣሉ።ሁለት የሞሪንጋ ዝርዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛሉ።

Add comment


Security code
Refresh

የፎቶ ክምችት

ድረገጹን በመጎብኘት ላይ ያሉ

We have 42 guests and no members online
2084693
ዛሬ
ትላንት
በዚህ ሳምንት
ባለፈው ሳምንት
በዚህ ወር
ባለፈው ወር
አጠቃላይ ድምር
3601
4578
43388
2006511
140153
112856
2084693

የእርሶ IP: 54.159.214.27
የአገልጋዩ ሰዓት: 2015-04-26 15:19:56