ማህበራዊ

ከጅምሩ መወያየት ያድ...

  ከጅምሩ መወያየት ያድናል ከጥፋት

ከኒያት ከአንድ ሰው ጋር ተጋብቶ ወይም አብሮ ለመኖር ወይም የፍቅር ግንኙነት ለመጀመር መወሰን በራሱ ትልቅ ቁርጠኝነት ነው፡፡ መቸም ከዚህ ሰው ጋር አብረው ሲኖሩ ወይም ሲወጡ በጥልቀት እያወቁት መምጣት አይቀሬ ነው፡፡ አንዳንዶች...

You are here: Homeአዲስ ዘመንማህበራዊ«...የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱ ሙሉ ለሙሉ እንዲለወጥ ተደርጓል»-አቶ ጥላሁን በቀለ

«...የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱ ሙሉ ለሙሉ እንዲለወጥ ተደርጓል»-አቶ ጥላሁን በቀለ

አቶ ጥላሁን በቀለ ይባላሉ። በሳይኮሎጂ እና በሥነ ሕዝብ ልማት የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። ወደ ኔዘርላንድስ በመሄድም በማኅበራዊ ዋስትና (social protection) በድህረ ምረቃ ዲፕሎማ ተመርቀዋል።

አቶ ጥላሁን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዳገኙ በደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ በባለሙያነት አገልግለ ዋል። አዲስ አበባ በመምጣትም በመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ በማኅ በራዊ ዋስትና ጥናት ባለሙያነት (ኤክስፐር ትነት)፣ በቡድን መሪነት፣ በሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን በትጋት አገልግለዋል።

አቶ ጥላሁን ከ2004 .ም ጀምሮ የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

ዝግጅት ክፍላችን ስለመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ተግባር ተኮር እንቅስቃሴ፣ ዜጐች ሁሉ የማኅበራዊ ዋስትና እንዲያገኙ ምን ዕቅድ እንዳለ፣ አዲሱ የጡረታ አዋጅ ለጡረተኞች ስለአስገኘው ጥቅም፣ ስለአገልግሎት አሰጣጥና ተደራሽነት፣ የኢትዮ ጵያ ማኅበራዊ ዋስትና ሽፋን ከሌሎች አፍሪካ አገሮች አንፃር እንዴት እንደሚመዘን አቶ ጥላሁን በቀለ የሰጡንን ቃለ ምልልስ አቅርበናል።

አዲስ ዘመን፡- የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ዓላማውና ተልዕኮው ምን ያህል ስኬታማ ነው?

አቶ ጥላሁን፡- የተቋሙ ዋና ዋና ተግባራት ተቋሙ በተቋቋመበት ደንብ ላይ ተዘርዝሯል። በዚህ ረገድ የመንግሥት ሠራተኞችን የጡረታ አቅድ ለማስፈፀም ቀልጣፋና ብቃት ያለው ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ዋናው ተልዕኮ የጡረታ መዋጮን ስብስቦ የጡረታ አበል መክፈል ነው። በዚህ በገቢ አሰባሰብ ሥርዓት ላይ ከዚህ በፊት የአሠራር ችግር ነበር። ችግሩን ለመፍታት የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱ ሙሉ ለሙሉ እንዲለወጥ ተደርጓል። ቀደም ሲል የጡረታ መዋጮ ገቢ ታች ድረስ ወርዶ የሚሰበስበው ተቋሙ ነበር። ይህ አሠራር ደግሞ በጣም አስቸጋሪና ጊዜም የሚወስድ ነበር። ይሁን እንጂ የአሠራር ሂደቱን ለማሻሻል ጥናት ሲካሄድ የሌሎች አገሮችን ልምዶች ሳይቀር በመውሰድ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱን ሙሉ ለሙሉ በመለወጥ ቀደም ሲል የነበረውን ችግር ለማስወገድ ተችሏል። በዚህም መሠረት ቀደም ሲል በተቋሙ ይተገበር የነበረው የገቢ ማሰባሰብ ሥርዓት ተቋርጦ ዛሬ በቀጥታ ከአገሪቱ የፋይናንስ ሥራ ጋር ግንኙነት በአላቸው በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን እንዲሁም በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በኩል እንዲሰበሰብ ተደርጓል። ይህን የመሰለ አሠራር በመከተላችን የገቢ አሰባሰብ ሥርዓታችንን ቀልጣፋ አድርጐታል። በዋነኛነት ደግሞ ገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ከባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የጡረታ መዋጮውን እዚያው ከምንጩ ማሰባሰብ በመቻሉ ቀልጣፋ የሆነ አሠራር መፍጠር አስችሎናል።

በሌላም በኩል ከአገልግሎት አሰጣጥና ከተደራሽነት አንፃርም መሠረታዊ ለውጥና ውጤት ተገኝቷል። እንደሚታወቀው ኤጂንሲው የአሠራር ለውጥ ከማድረጉ በፊት በአጠቃላይ በመላ አገሪቱ የነበሩት ጽህፈት ቤቶች ሃያ ስምንት ብቻ ነበሩ። ይሁን እንጂ ኤጀንሲው በአደረገው ጥረት አሥር የሪጂን ጽህፈት ቤቶችን፣ ሃያ ሰባት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን አምስት ልዩ የመስክ እና ስምንት የመስክ ጽህፈት ቤቶችን በመላ አገሪቱ በመክፈት የአገልግሎት አሰጣጡን ተደራሽነት ማሳደግ አስችሏል። በእዚህ ረገድ የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የአደረጃጀት ለውጥ ማድረጉ የተቋሙን ሁለንተናዊ የሥራ አፈጻጸም አሳድጐታል። በውጤት ረገድም በተለይም የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አጋማሽ ግምገማ እንዳመ ለከተን የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል። ለእዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ለመሰብሰብ ያቀድነው የጡረታ መዋጮ ስምንት ነጥብ ስድሳ አራት ቢሊዮን ብር ነበር። ተቋሙ ኃላፊነቱን በተደራጅና በቀልጣፋ የአሠራር ስልት ለመወጣት በአደረገው ጥረት ከዕቅዱ በላይ አንድ መቶ ሦስት በመቶ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።

ሌላው ተቋሙ የተሰጠው ኃላፊነት የጡረታ መዋጮ መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን የጡረታ አበል መክፈልና የቀረውን ገንዘብ ደግሞ አስተማማኝ በሆነ እና በአዋጅ በተቀመጠ የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲውል ይደረጋል። እናም በዕድገትና ትራንስፎርሜሽኑ የዕቅዱ ግማሽ ዘመን ጊዜ ውስጥ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ሁለት መቶ ሃያ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ 219 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር አግኝቷል። ስለዚህ በፋይናንስ ዘርፍ ማለትም ገቢ በማሰባሰብ፣ ክፍያ በመፈፀምና ቀሪው ገንዘብ በኢንቨስትመንት ላይ በማዋሉ ረገድ አበረታች እንቅስቃሴና ውጤት አግኝቷል። በእርግጥም ውዝፍ የመዋጮ ገቢን የማሰባሰቡ ተግባር የኤጀንሲው ግዴታ ነው። እናም ምንም እንኳ እንቅስቃሴያችንና ውጤታችን አበረታች ቢሆን ገና ብዙ መሥራት እንዳለብን እናምናለን። ያም ሆነ ይህ በሁለት ሺ ሦስት መቶ ስልሳ አንድ አሠሪ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የውስጥ ምርመራ አካሂደን 485 ነጥብ 07 ብር ውዝፍ ብር ማሰባሰብ ተችሏል። ይሁን እንጂ ውዝፍ ሂሳብ የማሰባሰቡ ጥረት አበረታች ቢሆንም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እናምናለን።

በእዚህ ሂደት ውስጥ ችግሮች አልተከሰቱም ለማለት ግን አንደፍርም። የጡረታ ፈንዱን ገንዘብ በአስቀመጥነው የጊዜ ገደብ በውጭ ኦዲተር ማስመርመር አልቻልንም። ይህንም እንደ አንድ የተግባር ክፍተት እናየዋለን። ቢሆንም የ2004 እና የ2005 .ምን የጡረታ ፈንድን የሂሳብ ምርመራ ዳር ለማድረስ የኤጀንሲው የትኩረት አቅጣጫ ይሆናል። ሌላም እንደ ክፍተት የምናየው የኤጀንሲው አሠራር ሙሉ ለሙሉ በቴክኖሎጂ አለመደገፉ ነው። ይህም በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ ከግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ጋር በጋራ የአቋቋምነው የፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ተልዕኮውን ሲያጠናቅቅ የተቋሙ አገልግሎት ዘመናዊነትን እንደሚላበስ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ዜጐች ሁሉ የማኅበራዊ ዋስትና ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግሥት ምን እቅድ አለው? እስከአሁንስ ምን ጥረት ተደርጓል?

አቶ ጥላሁን፡- ሕገ መንግሥታችን የአገሪቱ ኢኮኖሚ እስከፈቀደ ድረስ ሁሉም ዜጐች የማኅበራዊ ዋስትና ተጠቃሚ ይሆናሉ በማለት ደንግጓል። በእርግጥ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የማኅበራዊ ዋስትና ተጠቃሚዎች የመንግሥት ሠራተኞች ብቻ ነበሩ። ነገር ግን ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች የማኅበራዊ ዋስትና ሽፋን የሚያገኙበት ሥርዓት መጀመሩ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ውጤታማ መሆኑን የሚያመላክት ነው።

በተጨማሪም የግል ድርጅቶች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ መቋቋም ከመንግሥትም ሆኖ ከግል ድርጅቶች ውጪ በግላቸው ሠርተው የሚተዳደሩ ዜጐችንም ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ለዜጐች ማኅበራዊ ዋስትና ትኩረት መስጠቱን ያረጋግጣል። እንዲሁም በጤናው ዘርፍ የተቋቋመው የማኅበራዊ ጤና መድህን ኤጀንሲ ሌላው የማኅበራዊ ዋስትና ትሩፋት ነው። ሌላው አሁን በቅርቡ አዲስ የማኅበራዊ ዋስትና ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል። ፖሊሲው ፀድቆ ተግባራዊ ሲሆን ዜጐችን በየደረጃው ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይታመናል። በአጠቃላይ መላውን ህብረተሰብ የማኅበራዊ ዋስትና ተጠቃሚ ለማድረግ ለተጀመሩት ዘርፈ ብዙ የማኅበራዊ ዋስትና እቅጆች ተግባራዊ ሲሆኑ የአገልግሎት ሽፋኑን በዓይነትም ሆነ በስፋት ያሳድጋል።

አዲስ ዘመን፡- አዲሱ የመንግሥት ሠራተኞች የጡረታ አዋጅ የጡረታ አበል በየአምስት ዓመቱ እንዲጨመር ያዛል ይህ ድንጋጌ ምን ያህል ተግባራዊ ሆኗል?

አቶ ጥላሁን፡- አዲሱ የጡረታ አዋጅ ማለት አዋጅ ቁጥር 714 ነው። ይህ አዋጅ የወጣው ሰኔ 2 ቀን 2003 .ም ነው። ወርሐ ሰኔ 2003 .ምን አንድ ብለን ከቆጠርን አምስት ዓመት የሚሞላው በ2008 .ም ነው። ይሁን እንጂ መንግሥት ያለውን የኑሮ ውድነት በማመዛዘን የጡረታ አበል የመጨመሪያ ጊዜው ላይ ሳይደርስ በ2003 የጡረታ አበል መሻሻል ጭማሪ አድርጓል። ከአዲሱ አዋጅ በፊትም በ2000 .ም ለመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ሲያደርግ ለጡረተኞችም የጡረታ አበል ማሻሻያ ጭማሪ ተደርጓል። እናም በእርግጥ በአዋጅ ድንጋጌ መሠረት የጡረታ አበል በየአምስት ዓመቱ መጨመሩ በሕግ የተደነገገ ቢሆንም ነገር ግን መንግሥት አምስት ዓመት ሳይጠበቅ በየወቅቱ የሚከሰተውን የኑሮ ውድነት በማየት የአበል ጭማሪ እያደረገ መሆኑ እሙን ነው።

አዲስ ዘመን፡- የተሻሻለው የጡረታ አዋጅ (714/2003) ከአሠራር አንፃር ለጡረተኞች እና ለመንግሥት ሠራተኞች ያስገኘውን ጠቀሜታ ቢገልጹልኝ ?

አቶ ጥላሁን፡- የተሻሻለው 714/2003 የጡረታ አዋጅ ቀደም ሲል ከነበረው አዋጅ ቁጥር 341/95 አያሌ ተጠቃሚነትን ያጐናጽፋል። በእዚህም መሠረት ለአብነት ያህል አንዳንድ ማሳያዎችን መጠቃቀሱ ተገቢ ነው። ቀደም ሲል የነበረው የጡረታ አዋጅ አንድ ጡረተኛ ከአንድ ዓመት በላይ የጡረታ አበሉን ካልተቀበለ ውዝፍ አበሉን አያገኝም። የጡረታ አበሉንም የሚያገኘው ከጠየቀበት ጊዜ ጀምሮ ነበር። ነገር ግን አዲሱ አዋጅ አንድ ጡረተኛ እስከ ሦስት ዓመት ውዝፍ የጡረታ አበሉን እንዲያገኝ ይፈቅዳል። ቀደም ሲል በነበረው አዋጅ አንድ ጡረተኛ ሥራ ቢይዝ የጡረታ አበል መቀበያ ደብተሩን ለተቋሙ ይመልስ ነበር። በአዲሱ አዋጅ ግን ጡረተኛው የጡረታ አበሉን እየተቀበለ በማንኛውም መሥሪያ ቤት ሠርቶ ተጠቃሚ እንዲሆን የፈቀደ ነው። ሌላው በቀድሞው አዋጅ ለአካል ጉዳተኛ ተተኪዎች የሚሰጠው የጡረታ አበል እስከ አሥራ ስምንት ዓመት ነበር። በአዲሱ አዋጅ ግን አካል ጉዳተኛ ተተኪዎች እስከ ሃያ አንድ ዓመታቸው ድረስ የጡረታ አበል እንዲያገኙ ይደነግጋል። ሌላው የአዲሱ አዋጅ ትሩፋት በግልም ሆነ በመንግሥት መሥሪያ ቤት የሚሰጥ አገልግሎት በሁለቱም ዘርፍ የማኅበራዊ ዋስትና አገልግሎት በሚሰጡት ኤጀንሲዎች እኩል ተቀባይነት እንዲኖረው አስችሏል። ይህ ማለት በግልም ሆነ በመንግሥት ድርጅት ያገለገለባቸው ዓመታት ለጡረታ ዋስትና እንደሚያዙ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ኤጀንሲው በመላ አገሪቱ በተደራሽነቱና በአገልግሎት ረገድ ውጤታማነቱ ምን ያህል እንደሆነ ቢገልጹልኝ?

አቶ ጥላሁን፡- ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ደረጃቸውና ኃላፊነታቸው የተለያዩ ቢሆንም ስድሳ ጽህፈት ቤቶች አሉን። በፊት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በሌሉባቸው አካባቢ የሚገኝ ጡረተኞች ሪጂን ጽህፈት ቤት ድረስ ለመምጣት ይገደዱ ነበር። ዛሬ ግን ተገልጋዩ በአለበት ቦታ አገልግሎት እንዲያገኝ ኤጀንሲው ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። በመሆኑም እስከ መስክ ጽህፈት ቤቶች ድረስ መዋቅር በመፈጠሩ ተገልጋዮች በአቅራቢያቸው አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል። ቀደም ሲል በሪጅንና አዲስ አበባ የሚወሰኑት የማኅበራዊ ዋስትና ተግባራት በየጽህፈት ቤቶች እንዲከናወኑ የጽህፈት ቤቶች አቅም እንዲጐለብት ተደርጓል። በሌላም በኩል ጡረተኞች የጡረታ አበላቸውን የሚያገኙት በስምንት መቶ ስልሳ አንድ መክፈያ ጣቢያዎች ሲሆን፤ አበሉን እንዲከፍሉ የተደረጉት ደግሞ በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት አማካኝነት በኩል ነው። ለአብነትም ደደቢት፣ ኦሞ ማይክር ፋይናንስ ፣አዲስ ብድርና ቁጠባ፣ ኮሜርሺያል ኖሚኒስት፣ ፖስታ ቤት ወዘተ ናቸው። ይህም በመሆኑ ተደራሽነቱ ፍትሐዊ ነው እንላለን።

በሥራ ቅልጥፍና አንፃርም ለውጥ አለ። ድሮ አራትና አምስት ወር ይፈጅ የነበረ ሥራ አሁን መረጃው ሙሉ በሙሉ ከተሟላ በአንድ ቀን ማስተናገድ ይቻላል። በሰዓታት የሚፈፀሙ ተግባራትም አሉ። የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ግን ሙሉ ለሙሉ በቴክኖሎጂ መጠቀም ተገቢና አስፈላጊ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በመንግሥትና በግል የማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲዎች መካከል ያለው አንድነትና ልዩነት ምንድን ነው?

አቶ ጥላሁን፡- ሁለቱን ኤጀንሲዎች የሚያመሳስላቸው ዜጐች የማኅበራዊ ዋስትና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚሠሩ በመሆናቸው ነው። ሁለቱም ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎት በመዋጮ ላይ የተመሠረተ ነው። ሁለቱም በሥራ አመራር ቦርድ ነው የሚመሩት።

ልዩነቱን ስንመለከት የአቅዱ አባላት የመንግሥት እና የግል ሠራተኞች መሆናቸው ሲሆን፤ ሌላው ልዩነት ደግሞ የቦርዱ አወቃቀር ነው። የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የአመራር ቦርድ ሦስትዮሽ አወቃቀር አለው። ይኸውም በአሰሪው፣ በሠራተኛውና በመንግሥት የተዋቀረ ቦርድ ነው። የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የአመራር ቦርድ የሚዋቀረው በመንግሥት ብቻ ነው። ሌላው ልዩነት የመንግሥት ሠራተኞች የማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ አገልግሎት የሚሰጠው ለመንግሥት ሠራተኞች፣ ለመከላከያና ለፖሊስ ሠራዊት፣ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሠራተኞች ብቻ ነው። የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የሚሰጠው አገልግሎት ደግሞ ለግል ድርጅት ሠራተኞችና በግል ሠርተው ለሚተዳደሩ ዜጐች ነው።

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ዋስትና ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች አንፃር እንዴት ይመዘናል?

አቶ ጥላሁን፡- በአገራችን ዘመናዊ ማኅበራዊ ዋስትና ከተጀመረ ሃምሳ ዓመታት ተቆጥረዋል። በእርግጥ ምንም እንኳን የመንግሥት ሠራተኞች የማኅበራዊ ዋስትና ተቋም በዕድሜ አንጋፋ ቢሆንም ከሌሎች አገሮች ጋር ስናነፃፅረው የሚፈለግበት ደረጃ ላይ ደርሷል ለማለት አያስደፍርም። ለምሳሌ ሽፋኑን ስንመለከት ከአጠቃላይ ሕዝቡ ከአምስት በመቶ በታች ነበር። ምክንያቱም አገልግሎት የሚሰጠው ለመንግሥት ሠራተኞች ብቻ በመሆኑ ነው። ያም ሆነ ይህ አሁን የግል ድርጅቶችን ጨምሮ የማኅበራዊ ዋስትና ተጠቃሚው ቁጥር ወደ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን አካባቢ ደርሷል። ለምሳሌ በጋና የአንድ ሠራተኛ የጡረታ መብቱ የሚከበርለት አሥራ አምስት ዓመት ሲያገለግል ነው። በኢትዮጵያ ግን አሥር ዓመት ካገለገለ የጡረታ መብቱ ይከበርለታል። ይህ ማለት ግን በአሥር ዓመት የጡረታ አገልግሎት የጡረታ አበል ይሰጣል ማለት አይደለም። በእዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ዋስትና በጣም የተሻለ መሆኑን ባለሙያዎች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ። በአጠቃላይ ከሰህራ በታችም ሆነ ከአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነፃፀር ሰባ በመቶ የጡረታ አበል የሚፈቅድ የማኅበራዊ ዋስትና ሥርዓት በጣም ጥሩ የሚባል ነው። የጡረታ አበል የሚወሰነው በደመወዝና በአገልግሎት መጠን ቢሆንም የሠራተኛው ደመወዝ ሲሻሻል የጡረታ አበሉም እየጨመረ ይሄዳል። አሁን በአለው ሁኔታ ግን አንድ ጡረተኛ እንደ አገልግሎቱ የደመወዙን ሰባ በመቶ የጡረታ አበል ማግኘት ከቻለ የጡረታ አበሉ ደመወዙን የመተካት ደረጃው ጥሩ ነው ተብሎ የሚወሰድ ነው።

Add comment


Security code
Refresh

የፎቶ ክምችት

ድረገጹን በመጎብኘት ላይ ያሉ

We have 63 guests and no members online
2086122
ዛሬ
ትላንት
በዚህ ሳምንት
ባለፈው ሳምንት
በዚህ ወር
ባለፈው ወር
አጠቃላይ ድምር
5030
4578
44817
2006511
141582
112856
2086122

የእርሶ IP: 54.159.214.250
የአገልጋዩ ሰዓት: 2015-04-26 23:13:35