ማህበራዊ

ወደ አምራችነት የተሸጋ...

 ወደ አምራችነት የተሸጋገሩ እጆች

በርካታ ሴቶች ከተመጽዋችነት ወደ ሥራ ተሸጋግረዋል፤ አበው ሲተርቱ «ኑሮ ካሉት መቃብርም ይሞቃል» ይላሉ። የኑሮ ደረጃው ይለያይ እንጂ ኑሮ ከተባለ ሁሉም ከምድር በላይ በሕይወት እስከተኖረ ድረስ የሕይወትን ዘርፈ ብዙ...

You are here: Homeአዲስ ዘመንማህበራዊየብዙዎችን ተስፋ ያለመለመ ስልጠና

የብዙዎችን ተስፋ ያለመለመ ስልጠና

  

 ሥልጠናው የብዙዎችን ህይወት እንደሚቀይር ተስፋ ተጥሎበታል፤                               አስናቀች ኃይሉ ፤

 

እጅጋየሁ ከተማ ነዋሪነቷ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ነው። ሕይወቷን የምትመራው በድግስ ቤቶች ምግብ በማዘጋጀት ነው። ምንም እንኳን ሥራ አለኝ ብላ ብታስብም ሥራው ወቅት እየጠበቀ የሚመጣ በመሆኑ በኑሮዋ ላይ ጠብ የሚል ነገር አላገኘችም። ገቢዋንም አስተማማኝ ለማድረግ አልቻለችም። ይህ ደግሞ የተረጋጋ ሕይወት እንዳትመራ እንቅፋት ሆኗታል።

በአንድ አጋጣሚ ግን ሕይወቷን ሊቀይር የሚችል የስልጠና አጋጣሚ ተፈጠረ። ሴቶች ራሳቸውን ችለው ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ነፃ እንዲሆኑ ለማድረግ የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ከአውሮፓ ኅብረት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ እንዲሁም በጅጅጋ ለሚገኙ አነስተኛ ገቢና ምንም ገቢ የሌላቸውን ሴቶች የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው ለማድረግ በምግብ ዝግጅትና በመስተንግዶ ለማሰልጠን ምዝገባ ሲያካሂድ እሷንም የቀደማት አልነበረም። ነገር ግን ስትመዘገብም ደስ እያላት አልነበረም። ምክንያቱም ለስልጠናው «እጠራለሁ» የሚል ምንም አይነት ተስፋ ስላልነበራት በጥርጣሬ ነበር ምዝገባውን ያካሄደችው። በኋላ ጥሪው ሲደርሳት ደስታዋ ወደር አጣ።

«በቃ ሕይወቴ ተቀየረ ማለት ነው» በማለት ያገኘችውን እድል ሳታቅማማ ተቀብላ በምግብና መስተንግዶ ሙያ የስልጠናው ተሳታፊ የሆነችው። እናም ዛሬ ለሶስት ወራት የሙያ ስልጠና ካገኙ አምስት መቶ ሴቶች አንዷ ለመሆን በቃች። «ስልጠናው ከዚህ ቀደም በነበረኝ እውቀት ላይ ይበልጥ እንዳውቅ ረድቶኛል። በተለይ ደግሞ ለሰርግና ለተለያዩ ዝግጅቶች ሲኖሩ ምግቡንና ለእጅና አፍ መጥረጊያ የሚያገ ለግለውን ሶፍት በሚያምር ሁኔታ እንዴት ማስቀመጥ እንዳለብኝ ከበቂ በላይ እውቀት አግኝቼበታለሁ» ትላለች።

በልማድ የምታውቀውን ሥራ በእውቀት በመደገፏ ከነበራት እውቀት ላይ ከፍ እንድትልና በሯሷ እንድትተማመን አድርጓታል። «ጥረት ካለ ሁለም ይሳካል» የምትለው እጅጋየሁ በቀጣይ ለምታከናውነው ሥራ ስልጠናው እገዛ በማድረግ በሰዎች ዘንድ ተፈላጊነቷን እንደሚጨምርላትና ገቢዋንም እንደሚያሳድግላት ባለሙሉ ተስፋ ናት።

አስናቀች ኃይሉም የስልጠናው ተሳታፊ ናት። የመጣችው ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሲሆን፤ እርሷም የተመረቀችው በመስተንግዶ ነው። ከዚህ ቀደም በሙዚቃ ሥራ ላይ ተሰማርታ የነበረ ቢሆንም ስላልተሳካላት የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ትምህርቷን ከዘጠነኛ ክፍል አቋርጣ ወደ አረብ አገር ለመሄድ ተገድዳለች። በዚያም ሄዳ ለአንድ ዓመት ከሰባት ወር ቆይታ በእጇ ላይ ህመም ስላጋጠማት ያሰበችውን ሳታሳካ ተመልሳ ወደ አገሯ መጥታለች። እዚህም የተለያዩ ስራዎችን ብትሞክርም ሊሳካላት አልቻለም። ይህንንም እድል ያገኘችው በድጋሚ ወደ አረብ አገር ለመሄድ በዝግጅት ላይ በነበረችበት ወቅት ነው።

«ኑሮ በአረብ አገር ይከብዳል። ምርጫ ሲጠፋ አንዳንዴ የምንወስነውን አናውቅም። እዚያ ብሄድ ምን ሊደርስብኝ እንደሚችል አላውቅም። ልክ ሌሎች ሴቶችን እንዳጋጠማቸው እኔንም ምናልባት መጥፎ ነገር ያጋጥመኝ ይሆናል። ነገር ግን ምርጫ ስላልነበረኝ ሳልወድ በግድ ለመሄድ ተነሳስቼ ነበር። አሁን ይህ እድል አጋጥሞኝ ሳልሄድ ቀርቻለሁ። ሰልጥኜም የሙያ ባለቤት ለመሆን በቅቻለሁ። ከዚህ በኋላ በቤት ሠራተኝነት ወደ አረብ አገር መሄድ አይጠበቅብኝም። በአገሬ ሰርቼ ለመኖር የሚያስችል አቅም ተፈጥሮልኛል። ለእዚህም በመብቃቴ ደስተኛ ነኝ። ብችል የራሴን ሥራ አልያም ተቀጥሬ ለመሥራት ዝግጁ ነኝ»ትላለች።

ከሰልጣኞቹ መካከል አንዳንዶቹ ከትምህርት ገበታ ከራቁ ብዙ ጊዜ የሆናቸው ሲሆኑ፤ ትምህርት «አይሆንልኝም» ብለው ተስፋ የቆረጡም ይገኙበታል። ስለዚህ የመሰላቸትና ተስፋ የመቁረጥ መንፈስ እንዳይሰማቸው መምህሮቻቸው በሥነ ልቦና ከማዘጋጀት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን አድርገዋል። በዚህም ስልጠናውን እንዲወዱትና በትጋት እንዲ ጨርሱት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳደረገላቸው ትመሰክራለች አስናቀች።

እጸገነት ዘለቀ ትባላለች ፤በምግብና መጠጥ መስተንግዶ ነው የሰለጠነችው። ከዚህ በፊት በዚህ ዙሪያ ምንም አይነት እውቀቱ አልነበራትም። ስለዚህም የምግብና መጠጥ መስተንግዶ ሥራ ላይ የነበራት አመለካከት የተሳሳተ ነበር። በዚያም የተነሳ ስልጠናው ብዙም አላጓጓትም ነበር። ወደ ስልጠናው ከገባች በኋላ ግን ባገኘችው እውቀት የተነሳ ቀድሞ የነበራት አመለካከት ትክክል እንዳልነበር ተገንዝባለች።

ከዚህ ቀደም አረብ አገር ደርሳ ነው የተመለሰችው። «እንዲህ አይነት እድል በአገራችን ላይ ካለ ወደ አረብ አገር መሄዱ አስፈላጊም አይደለም። የሰው አገር ትርፉ ልፋትና ስቃይ ነው። በአገራችን ላይ ሰርተን የምንለወጥበት አጋጣሚ እየተፈጠረ ነው። መንግሥት ይሄን እድል ስላመቻቸልን ሊመሰገን ይገባል። ይህ አጋጣሚ ሌሎችም ሠርተው መለወጥ እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው»ትላለች።

ይህ አጋጣሚ ለእፀገነት በሕይወቷ አንድ ሽግግር ነው።ከዚህ ቀደም ራሷንም ሆነ ቤተሰቦቿን ለመርዳት አቅሙ አልነበራትም። አሁን ግን እውቀቱም አቅሙም ተፈጥሮላታል። ሠርታ በመለወጥ ዝግጁ በመሆኗ ደስተኛ ናት። አሁን ባለችበት ሁኔታ በሆቴሎች ውስጥ ተቀጥራ ክህሎቷን ይበልጥ ለማሳደግ ያሰበች ሲሆን፤ በቀጣይ ግን የራሷን ሬስቶራንት ለመክፈት እያሰበች ነው።

ሴቶቹ ተገቢውን እውቀት ጨብጠው ለራሳቸውም፣ ለአገራቸውም ጠቃሚ ተግባር እንዲያከናውኑ የስልጠና ማኑዋል፤ ዩኒፎርም፣ የትራንስፖርት አበል እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁስ ተዘጋጅቶላቸው ስልጠናውን ወስደዋል። በአዲስ አበባ የሚገኙት ሦስት መቶ ሰልጣኞችም ስልጠናቸውን አጠናቅቀው ሰሞኑን በሒልተን ሆቴል የምረቃ ሥነ ሥርዓታቸው ተካሂዷል።

እነዚህ ሴቶች ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው ጎልብቶ በሕይወታቸው ስኬታማ እንዲሆኑ ይህ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። ይህንን ዕድል ባያገኙ ሁሉም ሰልጣኞች ማለት ይቻላል ከፍለው ለመማር አቅሙ ስለማይኖራቸው ራሳቸውን የመቀየሩ ነገር በጥያቄ ውስጥ ይወድቃል። ነገር ግን መንግሥት የሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ በዘረጋው መስመር የበርካቶች ሕይወት ተቀይሮ የትናንት ማንነታቸው ዛሬ ላይ ታሪክ እንዲሆን ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ሼፍ ሄኖክ ዘሪሁን ሰልጣኞችን ለሦስት ወራት ካሰለጠኑት መካከል አንዱ ነው።ከሰልጣኞቹ ጋር የነበረው ቆይታ እጅግ አስደሳችና ከጠበቀው በላይ በመሆኑ ውስጣዊ እርካታ እንደተሰማው ይናገራል። ምክንያቱ ደግሞ ብዙዎቹ ከፍለው ለመማር አቅሙ የሌላቸው በመሆናቸውና ካሉበት ሕይወት ወጥተው ነገ ላይ የተሻለ ነገር እንዲያገኙ እድሉን በማግኘታቸው ነው።

እርሱ እንደገለጸው፤ሰልጣኞቹ ለማወቅና ራሳቸውን ለመለወጥ ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ የቦታ ርቀት ሳይገድባቸው በንድፈ ሃሳብና በተግባር የተማሩትን ትምህርት ያለ አንዳች ችግር በንቃት ተከታትለዋል። ይህም በቀጣይ ወደ ሥራ ዓለም ሲገቡ ውጤታማና በራሳቸው የሚተማመኑ ያደርጋቸዋል የሚል እምነት አለው።

በኅብረተሰቡ ዘንድ መስተንግዶና የምግብ ዝግጅት ሙያ እንደቀላል ተደርጎ ስለሚታይ ብዙዎቹ አዋጭ አይደለም የሚል የተሳሳት አመለካከት አላቸው። ይህ ሊሆን የቻለው ብዙዎቹ ወጥተው ሥራ ከመፈለግ ይልቅ ይዘውት ቁጭ በማለታቸው ነው። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ የሆቴል ኢንዱስትሪው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል። የባለሙያዎችም ተፈላጊነት፤ተካፋይነታቸውም እንደእዚሁ እየጨመረ ይገኛል ባይ ነው።

በተጨባጭ በአገሪቱ እንደሚታየው የሆቴል ኢንዱስትሪው አዋጭ በመሆኑ በርካታ ሆቴሎች እየተከፈቱ ነው። ይህን ተከትሎ በአግባቡ ሊመራና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻል በሙያው የሰለጠነ የሰው ኃይል ያስፈልጋል። ይህ የሚያሳየው ሙያው ምን ያህል ተፈላጊ እየሆነ መምጣቱን ነው። ስለዚህ ሥራ የማጣቱ ስጋት አይኖርም። ሰልጣኞቹም ሙያውን እንደቀላል እንዳይመለከቱ በበቂ ሁኔታ ግንዛቤ እንዲያገኙ ተደርጓል ይላል ሼፍ ሔኖክ።

ከዚህ በኋላ ቢፈልጉ ተቀጥረው፤ አለዚያም ተደራጅተው ወይም በግላቸው በሰለጠኑበት ሙያ መስራት ይችላል። መንግሥትም አስፈላጊውን ድጋፍ ካደረገላቸው በቀላሉ የተሻለ ደረጃ ላይ መድረስ ይችላሉ የሚል እምነት አለው።

የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ዘነቡ ታደሰ እንደተናገሩት፤በተለይ ሕገወጥ ስደትን ምርጫቸው ያላደረጉ፤በተለያዩ የሥራ መስኮች በግልና በቡድን ተደራጅተው ተምሳሌታዊ የኢኮኖሚ እድገት ያስመዘገቡ ሴቶችና ወጣቶች አሉ። እነዚህ አካላት በሂደትም ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ባለቤትነት ብሎም ወደ ኢንቨስትመንት ተሸጋግረዋል። ሰልጣኞችም የተፈጠረላቸውን ምቹ አጋጣሚ ተጠቅመው፤ አገሪቱ የያዘችውን ድህነትን የማስወገድና የሥራ አጥ ሴቶችንና ወጣቶችን ቁጥር የመቀነስ ስትራቴጂ ተፈፃሚ እንዲሆን ከሥራ ጠባቂነት አስተሳሰብ ተላቅቀው በትጋት እንዲንቀሳቀሱ መክረዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሴቶችንና ወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ብቃት፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብርና በቅንጅት እየሠራ ይገኛል። ተመራቂዎቹም በተሰማሩበት የሙያ መስክ ስኬታማ እንዲሆኑ ነፃ የብድር አገልግሎት ከመስጠት ጀምሮ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ቃል ተገብቶላቸዋል።

መንግሥት በችግር ውስጥ ያሉ ሴቶች የተለያየ ሙያ ባለቤት ሆነው ራሳቸውንን፣ ቤተሰባቸውን ብሎም ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ የተለያዩ እገዛዎችን እያደረገ ይገኛል። በተለይም ሴቶቹ ይህንን የሙያ ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉ በራሳቸው የመተማመን ስሜት እንዲኖራቸውና ተስፋቸው ለምልሞ በሀገራቸው መሥራትን እንደ ቅድሚያ አማራጭ እንዲወስዱ የሚያስችል ነውና ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

 

Add comment


Security code
Refresh

የፎቶ ክምችት

ድረገጹን በመጎብኘት ላይ ያሉ

We have 219 guests and no members online
2055658
ዛሬ
ትላንት
በዚህ ሳምንት
ባለፈው ሳምንት
በዚህ ወር
ባለፈው ወር
አጠቃላይ ድምር
3153
6360
14353
2006511
111118
112856
2055658

የእርሶ IP: 54.159.142.177
የአገልጋዩ ሰዓት: 2015-04-21 08:48:26