የአንድ ማሽን ብልሽት ሚሊዮን ዶላሮችን ሲያሳጣ Featured

17 Feb 2017

በኢታኖል አቅርቦት ሲሳተፍ የነበረው የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ፤

በወርሃ ጥር መጀመሪያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‹‹አገሪቱ በግማሽ ዓመቱ ምን አቅዳ፤ ምን ከወነች?›› ለሚለው ጥያቄ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ምላሽና ማብራሪያ አድምጧል፡፡ በወቅቱ ታዲያ፤ እንደራሴዎቹ ‹‹አሳስቦናል›› ካሏቸው ጉዳዮች መካከል የአገሪቱ የወጪና ገቢ ንግድ ሚዛን አለመመጣጠን አንዱ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም፤ የአገሪቱ የወጪ ንግድ የተመሰረተው በግብርና ምርቶች ላይ መሆኑን አስታውሰዋል። ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች መጠን በተከታታይ እየጨመረ ቢመጣም በዓለም አቀፍ ገበያ ዋጋቸው እያሽቆለቆለ በመሄዱ ከወጪና ገቢ ንግዱ የሚገኘው ገቢ ሊመጣጠን እንዳልቻለም አመልክተው ነበር፡፡

ከወጪ ንግድ የሚገኘው ገቢና አገሪቱ ለገቢ ንግድ የምታወጣውን ገንዘብ አለመመጣጠን ለመቀነስ በመንግስት በኩል የተያዙ የመፍትሄ አማራጮች እንዳሉና ተግባራዊ እንደሚሆኑ መግለጻቸውም ይታወሳል፡፡ የወጪና ገቢ ንግድ ሚዛን ተመጣጣኝ አለመሆን በአጠቃላዩ የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ የሚፈጥረው ጫና ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ወደ ውጪ የሚላከው ምርት አንሶ የሚገባው በጨመረ ቁጥር የምንዛሪ እጥረት እንደሚኖር ይታመናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ልዩነቱን ለማጥበብ ‹‹በእኛ አቅም ልናደርግ የምንችለው ነገር ቢኖር አሁንም ለውጪ ገበያ የምናቀርባቸውን ምርቶች መጠን መጨመር ነው›› ብለው ነበር፡፡ በመሆኑም የምንዛሪ እጥረቱ ለዓመታት የአገሪቱ ችግር ሆኖ ሊዘልቅ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡  

የምጣኔ ሀብት ምሁራን እንደሚስማሙት የውጪ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ የአገር ውስጥ ምርቶችን በዓይነትና በመጠን ከማብዛት ጎን ለጎን ከውጪ የሚገቡትንም ምርቶች በአገር ውስጥ መተካት ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከውጪ ከምታስገባቸው ከፍተኛ ወጪ ከሚጠይቁ ምርቶች መካከል ነዳጅ አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለአብነትም የብሔራዊ ባንክ ያለፈውን ዓመት ሪፖርት ብንመለከት አገሪቱ በአንድ ዓመት ውስጥ ያስገባችው የነዳጅ መጠን ሶስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን መሆኑን ያሳያል፡፡ ይሄ  ሲሰላ ወደ 30 ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር ይደርሳል፡፡

በእርግጥ ይሄ አሃዝ ከሁለት ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በ20 ነጥብ አንድ በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ በዋናነት ምክንያቱ ኢትዮጵያ የምታስገባው የነዳጅ መጠን መቀነስ ሳይሆን በወቅቱ በዓለም አቀፍ ገበያ የነዳጅ ዋጋ ማሽቆልቆሉ ነው፡፡ በእዚያን ወቅት የዓለም አቀፉ የነዳጅ ዋጋ መቀዛቀዝ ቢያሳይም ኢትዮጵያ የምታስገባው አጠቃላይ የተፈጥሮ ጋዝ መጠን በሰባት ነጥብ ስምንት በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡ በተቃራኒው ግን የመኪና ቤንዚን በ36 ነጠብ አራት በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡           

ዘንድሮ የዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ በኢኮኖሚ ላይ የከፋ ተፅእኖ በሚፈጥር መልኩ የዋጋ ውጣ ውረድ አላሳየም፡፡ ይሁንና ባሳለፍነው ሳምንት በአገሪቱ የተወሰነ የዋጋ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡ በተመሳሳይ ደረጃ ባይሆንም ከአስር ዓመት በፊትም የዓለም ኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ገብቶ ሲፈተን የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ አሻቅቦ ነበር፡፡ ለዚህም ከተወሰዱ አፋጣኝ የመፍትሄ እርምጃዎች መካከል አገራዊ የነዳጅ ፍጆታን መቀነስ ባይቻል እንኳን ዋጋ ለማረጋጋት ከስኳር ፋብሪካዎች የሚገኝ የኤታኖል ምርት ከነዳጅ ጋር መደባለቅ ይጠቀሳል። በስራውም ቀላል የማይባል የውጪ ምንዛሪ ለማትረፍ ተችሎ ነበር፡፡

በወቅቱ በመንግስት በኩል በተቀመጠው አቅጣጫ ኤታኖልን ከነዳጅ ጋር ከአምስት አስከ 10 በመቶ ሲቀላቀል ቆይቷል፡፡ ይሄ ውሳኔ ሁለት ነገሮችን ለማሳካት ያለመ ነበር፡፡ በአንድ በኩል የነዳጅን ዋጋ ማረጋጋት፤ በሌላ በኩል የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂን መደገፍ በሚችል ደረጃ የአየር ብክለትን መቀነስ፡፡ በዚህ መሰረት ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ ስትራቴጂ ወጥቶ ነዳጅን ከኤታኖል የመቀላቀል ስራ ሲከናወን ቆይቷል፡፡

ኤታኖልን ከነዳጅ ጋር በመደባለቅ በርካታ ጥቅሞች ተገኝተዋል፡፡ በማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የባዮፊውል ልማት ማስተባበሪያ ዳሬክቶሬት ተወካይ አቶ ሚካኤል ገሰሰ፤ ከ1999 ዓ.ም እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ 60 ሚሊዮን ሊትር ኤታኖል ተመርቶ ከቤንዚን ጋር መደባለቅ  እንደተቻለ ይጠቅሳሉ፡፡ ይሄም  50 ሚሊዮን ዶላር አድኗል፡፡ ነገር ግን  የመደባለቁ ስራ  ካለፈው ዓመት ጀምሮ ተቋርጧል፡፡ ምርቱ ለመቋረጡ የተለያዩ ምክንያቶች ቢቀመጡም በዋናነት ሂደቱ ሲጀመር በቂ ዝግጅት ስላልተደረገበት ስራውን ማስቀጠል አልተቻለም፡፡           

‹‹ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኤታኖል አቅርቦትን ለመቆጣጠር ሃላፊነት አልተሰጠውም›› የሚሉት አቶ ሚካኤል፤ በዚህ ምክንያት አቅርቦቱ ሲቋረጥ ስኳር ፋብሪካዎችን ‹‹ለምን ኤታኖል አላመረታችሁም?›› በሚል ለመጠየቅ የሚያስችል  ሕጋዊ መሰረት አለመኖሩን ይገልጻሉ፡፡ የሆነው ሆኖ የኤታኖል አቅርቦት መቋረጡ  ከፍተኛ ጥቅም አሳጥቷል፡፡ ‹‹በዚህ ዓመት ብቻ እስከ 20 ሚሊዮን ሊትር የሚደርስ ቤንዚን መተካት ይቻል ነበር›› የሚሉት አቶ ሚካኤል፤ ኤታኖል ላለመቅረቡ በስኳር ኮርፖሬሽን በኩል የተለያዩ ጉዳዮች በምክንያትነት መነሳታቸውን ጠቅሰዋል።

ከኤታኖል አቅርቦት ጋር በተያያዘ ለምን  ሕግ አልተዘጋጀለትም? የሚለውን በተመለከተም እንደሚያብራሩት፤ ስራው ሲጀመር ከነበረው አስገዳጅ ሁኔታ መነሻነት ክትትሉ በከፍተኛ ሚኒስትሮች ደረጃ የሚከናወን ነበር፡፡ ሆኖም በሂደት አሰራሩ እየተለመደ ሄዶ ስራዎችም በልምድ መካሄዳቸውን ቀጠሉ፡፡ ‹‹ወደ ስራ የተገባው በሕግ ተደግፎ ሳይሆን በችኮላ ነበር›› የሚሉት አቶ ሚካኤል፤ በአሁኑ ወቅት ለተፈጠረው ሁኔታም ይሄ የሕግ ክፍተት አንድ ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

አገሪቱ በሁለት ፋብሪካዎች ኤታኖል የማምረት ዓመታዊ አቅሟ 30 ሚሊዮን ሊትር ነው፡፡ ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ሲጨመር ብቻውን 50 ሚሊዮን ሊትር በአመት የማምረት አቅም ይኖረዋል፡፡ በዚህ ላይ አስር የስኳር ፋብሪካዎች ሲጨመሩ ወደ 339 ሚሊዮን ሊትር የማምረት አቅም ይፈጠራል፡፡ ይሄ ደግሞ ‹‹በዚህ ዓመት የገባውን አጠቃላይ ቤንዚን መጠን ማለት ነው›› የሚሉት አቶ ሚካኤል፤ በአግባቡ ማምረት ቢቻል የአገር ውስጥ ፍላጎትን ከማሟላት ባሻገር ለጎረቤት አገሮችም ማቅረብ እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡

የማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኳንግ ቱትላም፤ ስራው ላይ የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት በርካታ ቢሆኑም ‹‹በዚህ መልኩ ማቅረብ አለባችሁ›› የሚል ምንም አይነት አስገዳጅ ሕግ አለመኖሩ ዘርፉ ላይ ችግር አስከትሏል፡፡ ሕጉ አለመኖሩ ደግሞ ፋብሪካዎች ማቅረብ ያለባቸውን የኤታኖል መጠን ዕቅድ አውጥተው እንዳይንቀሳቀሱ አድርጓል፡፡ በመሆኑም ስራው በአብዛኛው በማግባባት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በቀጣይ ምን ታስቧል? የሚለውን በተመለከተም፤ ተግባሩ አዲስ እንደመሆኑ መጠን ሚኒስቴሩ ጨረታ በማውጣት ሕጉ ምን ጉዳዮችን ማካተት እንደሚገባው ለመለየት በአማካሪዎች በኩል ጥናት እያካሄደ ይገኛል።

በጉዳዩ ዙሪያ በሁለት ወገኖች ዘንድ የሚስተዋል ልዩነት አለ፡፡ በአንድ በኩል ሚኒስቴሩ ‹‹ኤታኖል በአግባቡ ላለመቅረቡ የሕግ አስገዳጅነት አለመኖር ምክንያት ሆኗል›› ሲል፤ ስኳር ኮርፖሬሽን በበኩሉ ‹‹ምክንያቱ የማሽን ብልሽት ነው›› ይላል፡፡ በስኳር ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አቶ ጋሻው አይችሉህም፤ የኤታኖል አቅርቦቱ የተቋረጠው ከማሽን ብልሽት ጋር በተያያዘ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በአገሪቱ ካሉት ስኳር ፋብሪካዎች መካከል ምርቱን በዋናነት የሚያቀርቡት ፊንጫ እና መተሃራ ስኳር ፋብሪካዎች ብቻ ናቸው፡፡ ከሁለቱ ደግሞ የመተሃራ ስኳር ፋብሪካ ‹‹ኤታኖል ፕላንት›› ላይ ብልሽቱ ቢያጋጥምም ፊንጫ ግን አሁንም እንደሚሰራ አቶ ጋሻው ያስረዳሉ፡፡ ሆኖም እንደ አገር ካለው ሰፊ ፍላጎት አንጻር መጠኑ በቂ ባለመሆኑ አቅርቦቱ ለመቋረጥ መቻሉን ይናገራሉ፡፡

በቀጣይ የኤታኖል ፍላጎቱን በስፋት ለማልማት ከውጪ ኩባንዎች ጋር በጋራ በመሆን በአዳዲስ ስኳር ፋብሪካዎች የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸው ተገልጿል፡፡ ይኸውም በፋብሪካዎቹ የኤታኖል ፕላንት እንዲተከል ማድረግ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ጋሻው፣ ነገር ግን የትኞቹ ድርጅቶች በየትኞቹ ፋብሪካዎች ስራ እንደሚጀምሩ የገለጹት ነገር የለም፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በመተሃራ ፋብሪካ የተበላሸው መሳሪያ መቼ ጥገና ተደርጎለት ወደ ስራ እንደሚገባ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹እየተሰራ ነው›› የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ሚኒስቴሩ የሚያነሳውን የሕግ ክፍተት በተመለከተ ‹‹የሚፈጥረው ችግር የለም?›› ለሚለው ጥያቄ፤ እስካሁን የተለመደ አሰራር በመሆኑ የተፈጠረ የተለየ ችግር አለመኖሩን አንስተዋል፡፡

የነዳጅ ዋጋ በባሕሪው በአለም አቀፍ ገበያ ላይ ለመተንበይ ከሚከብዱ ምርቶች ተጠቃሽ ነው፡፡ ከአለም ነዳጅ አምራች አገሮች ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ዋጋው አንዴ ከፍ አንዴ ደግሞ ዝቅ የሚልበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ነዳጅን በተመለከተ ከባሕር ማዶ ምርት ጥገኝነት እስክትላቀቅ ገበያ ለማረጋጋት የተከተለችው መንገድ ወሳኝና አዋጭ ነበር፡፡ በመሆኑም የኤታኖል ምርት ድብልቅ ከመቋረጡ በፊት ማትረፍ የተቻለውን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ዳግም መታደግ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ በቅድሚያ በዙሪያው ያሉ ችግሮችን ፈጥኖ መፍታት ተገቢ ነው፡፡

ብሩክ በርሄ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።