የግብዓት ጥራት ችግር- የጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ተግዳሮት Featured

17 Feb 2017

በጨርቃ ጨርቅ ስፌት የተደራጁት የጰራቅሊጦስ ድርጅት አባላት በከፊል

ያደጉ አገራት መንግስታት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ለዜጎቻቸው ወይም በስደት በምድራቸው ለተጠለለ ህጋዊ የውጭ ዜጋ ራሱን ችሎ እንዲቆም ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር ቢኖር ክፍት የሆነ የስራ በር ማመላከት ነው። ይህም ማለት ዜጋው ስራ ሳይንቅ፣ ሳያማርጥ፣ ሙያ ያለው በሙያው ትምህርት ያለው በትምህርቱ ሌላው ደግሞ አቅሙ በፈቀደው የስራ መስክ ተሰማርቶ በጉልበቱ እንዲሰራና ራሱን እንዲለውጥ ማመቻቸት ነው።

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስትም ዜጎች ስራ ሳይንቁ ማንኛውንም ስራ እንዲሰሩና  ውጤታማ እንዲሆኑ በተለያዩ ዘርፎች ድጋፎችን እያደረገ ሲሆን፤ እነዚህን ከቁብ ባለመቁጠርና ስራ በማማረጥ በርካቶች ስራ አጥ /ቦዘኔ/ እንደሆኑ ሁሉ፤ ስራን ሳይንቁና ሳያማርጡ ከአንድ ሙያ ወደ ሌላው በመዘዋወር ብሎም አዋጭውን ይዞ በመቀጠል ውጤታማ መሆናቸውን የሚገልጹትም በርካቶች ናቸው። በተለይም በጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች ዘርፍ ተሰማርተው ህይወታቸውን መቀየር የቻሉ በርካቶች ናቸው። ይሁን እንጂ በጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ተሰማርተው ጥራታቸውን የጠበቁ ግብዓቶችን ማግኘት ባለመቻል ተፈላጊ፣ ከውጭ ጋር ተወዳዳሪ የሆኑና ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶችን ለማምረት መቸገራቸውን፤ ይህም በገበያቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያስከተለ እንደሚገኝ በዘርፉ የተሰማሩ ይገልጻሉ።

ፋኖስ ፀጋዬ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመካኒካል ኢንጂነሪንግ በዲግሪ ተመርቃ በአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በሽያጭ ሰራተኝነት መቀጠሯንና ለበርካታ አመታትም በድርጅቱ መስራቷን ትናገራለች፤ ሆኖም በድርጅቱ በሽያጭ ሰራተኝነት በሰራችባቸው ጊዜያቶች ልብስ መስፋት፣ የልብስ ዲዛይን ማውጣትና ሌሎችን ሙያዎች ከለመደች በኋላ ከቅጥር በመውጣት በ2005ዓ.ም በሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር በጥቃቅንና አነስተኛ እንደተደራጀች ትገልጻለች።

“መካኒካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት እንደመማሬ በጨርቃ ጨርቅ ስራ ህይወቴን እቀይራለሁ ብዬ አንድም ቀን አስቤ አላውቅም ነበር። ሆኖም በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ተቀጥሬ ስሰራ በጨበጥኩት ሙያና ከተማ አስተዳደሩ ባዘጋጀው የስራ ቦታ፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎትና ሙያዊ ድጋፎች በማግኘቴ  ጰራቅሊጦስ የአልባሳት ማምረቻ ድርጅት መስራች አባል በመሆን ህይወቴን መቀየር ችያለሁ” ትላለች። 

ወጣት ፋኖስ እንደምትለው፤ በሻሸመኔ ከተማ የሚገኘው ጰራቅሊጦስ የማምረቻ ድርጅት የተለያዩ  ቲሸርት፣ ፓካውት፣ ጋዎንና የህጻናት አልባሳት የሚያመርት ሲሆን፤  ለ25 ወጣቶች የስራ እድል ፈጥሯል። ድርጅቱ ስራውን በ20ሺ ብር ካፒታል መነሻነት የጀመረ ሲሆን፤ አሁኑ ወቅት የድርጅቱ ካፒታል 260 ሺ ብር ደርሷል። እንዲሁም በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የዲፕሎማ ትምህርት ያጠናቀቁ፣ ከ10 እና 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ያጠናቀቁና ጀምረው ያቋረጡ የከተማዋ ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል። ይሁን እንጂ ጥራታቸውን የጠበቁ፣ ጥሩ ዋጋ ሊያወጡና የውጭ አገር ምርትን ሊተኩ የሚችሉ አልባሳትን ለማምረት ጥራት ያለው ግብዓት አስፈላጊ በመሆኑና ደረጃውን የጠበቀ ምርት በቀላሉ ማግኘት ባለመቻሉ በስፋት እንዳንሰራ፤ ይህም በገበያ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ከመፍጠሩም ባሻገር ምርቱ በሁሉም ቦታ ተደራሽ እንዳይሆንና ተፈላጊነቱ እንዲያንስ ተጽዕኖ ማስከተሉን ይናገራሉ፡፡  

“ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች በጥራት ደረጃ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ በሁሉም አይነት ጨርቆች ምርቶችን ማቅረብ አለመቻላቸውና  ህብረተሰቡ ለአገር ውስጥ ምርት ከሚሰጠው ግምት አነስተኛ መሆን ጋር ተዳምሮ የሚመረቱ ምርቶች ገበያ ላይ ተግዳሮትን ይፈጥራል” የምትለው ወጣት ፋኖስ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምርቱ እየተለመደና እየተሻሻለ መምጣቱ የተሻለ ገበያ እንዲገኝ እድል ቢከፍትም፤ ለአልባሳት ግብዓት የሚውሉ ጨርቃ ጨርቆችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች የተሻለ ጥራት ያለው ምርት ቢያመርቱ እኛ የምናዘጋጃቸው ምርቶች በጥራት ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን ይችላሉ ባይ ነች።

በሂሳብ ትምህርት በዲፕሎማ ተመርቃ በተማረችበት ዘርፍ ስራ ባለማግኘቷ በድርጅቱ ተቀጥራ ያገኘኋት ወይዘሮ ከድጃ ጀማል፤ የአንድ ሙያ ባለቤት ስለሆንኩ ግዴታ በተማርኩበት ልስራ ማለት የለብኝም፤ በእርግጥ በሂሳብ ስራ በዲፕሎማ ተመርቄያለሁ፤ ሆኖም በተማርኩበት ዘርፍ ስራ ማግኘት ባለመቻሌ ስራ ሳላማርጥ ወደ ሙያው ገብቻለሁ። በጰራቅሊጦስ የአልባሳት ማምረቻ ድርጅት ተቀጥሬ በመስራቴ የልብስ ስፌት መኪና፣ ዲዛይን፣ ኦቨርሉክ መምታትና ሌሎችንም መማር ችያለሁ፤ ወደፊት የልብስ መኪና ማሽን በመግዛት የግል ስራዬን ለመስራት እያሰብኩ ነው ትላለች።

በድርጅቱ ተቀጥራ እየሰራች ያገኘኋት ወጣት ውቢት ግርማይ፤ ወደ ድርጅቱ የተቀጠረችው ምንም አይነት የልብስ ስፌት ሙያ ሳይኖራት 10ኛ ክፍል እንዳጠናቀቀች መሆኑንና አሁን ላይ የልብስ ስፌት ማሽን ስራ በደንብ መቻሏን ትገልጻለች። በቀጣይም ሙያውን በማሳደግ የተለያዩ ዲዛይን ያላቸውን አልባሳት መስራት ስትችልና አስፈላጊ ግብዓቶችን ስታሟላ የግሏን በመክፈት ለመስራት ማቀዷን ታስረዳለች።

በሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር የስራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ደስታ ዋሪቱ፤ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ በከተማዋ በርካታ ወጣቶች ተደራጀተው የተለያዩ አልባሳትን እያመረቱ ሲሆን፤ መንግስት ያመቻቸላቸውን የመስሪያ ቦታ፣ የማሽነሪ አቅርቦት፣ የብድርና ሌሎች ግብዓቶችን  በመጠቀም ገበያውን ሰብረው በመግባት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። በመጀመሪያ አካባቢ የገበያ ችግር የነበረባቸው በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ የገበያ ማዕከል በሆኑ የከተማዋ አካባቢዎች መሸጫና ማከፋፈያ ሱቅ እንዲያገኙ በማድረግ ችግሩ እንዲፈታላቸው አድርጓል። በተጨማሪም ቅዳሜና እሁድ መሸጫ ቦታ እንዲዘጋጅላቸው በማድረግ ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ እንዲያወጡና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በመደረጉ በከተማዋ በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ጰራቅሊጦስ የአልባሳት ማምረቻ ድርጅት አንዱ መሆኑንም ይናገራሉ።

ድርጅቱ ስራውን ሲጀምር አነስተኛ ካፒታል፣ ውስን የሰው ሃይል የነበረው ሲሆን፤ አሁኑ ወቅት ካፒታሉ ማደጉንና ተሽከርካሪ በመግዛትም ወደ መሃልና አጎራባች ከተሞች በመንቀሳቀስ ምርቶቹን እያስተዋወቀና እየሸጠ እንደሚገኝም የሚገልጹት  አቶ ደስታ፤ ከቴክኒክና ሙያ እንዲሁም ከኮሌጆች ለተመረቁ ወጣቶች በድርጅቱ የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ያስረዳሉ።

በተሻለ ደረጃ ምርቶችን ለማምረት የሚያስችሉ ጥራታቸውን የተጠበቁ ጥሬ እቃዎች በሚፈለገው ሁኔታ ገበያው ላይ አለመገኘት በዘርፉ ላይ የጥራት ችግር እያስከተለ እንደሚገኝ የሚናገሩት አቶ ደስታ፤ በአገሪቱ የሚገኙና ለግብዓትነት የሚውሉ ጨርቃ ጨርቆችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች የምርቶቻቸውን ደረጃ ማሳደግና የተሻለ ግብዓት ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። ምክንያቱም ጉዳዩ እየፈተነ ያለው ብትን ጨርቆችን ከአምራች ድርጅቶች ተቀብለው የተለያዩ አልባሳትን ማለትም ቲሸርት፣ ሹራብ፣ ጋዎን፣ ዩኒፎርም፣ የህጻናት ልብስ፣ ኮትና የመሳሰሉትን እያመረቱ የሚገኙ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የሚገኙ ድርጅቶችን ነው ይላሉ።

በከተማዋ በአገልግሎት፣ በማኑፋክቸሪንግ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች መኖራቸውንና ለሁሉም አስፈላጊ ግብዓቶችን ለማሟላት ከተማ አስተዳደሩ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ የሚገልጹት አቶ ደስታ፤ መንግስት በአገር አቀፍ ደረጃ ለወጣቱ የመደበውን 10 ቢሊዮን ብር እንደ ከተማ አስተዳደር በተገቢው ሁኔታ በጀቱን መቶ በመቶ ለመጠቀምና በከተማዋ ያሉ ስራ ፈላጊዎችን በማደራጀት የበለጠ ለመስራት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ይገልጻሉ።

አቶ ደስታ እንዳሉት፤ በከተማዋ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የተሰማሩ አንቀሳቃሾችን ወደ መካከለኛ ደረጃ ለማሸጋገር ድርጅቶቹ ያሉበት ደረጃና ያላቸው ጠቅላላ ካፒታል ሂሳብ ስራ እየተሰራ ሲሆን፤ አሟልተው የሚገኙት ወደ መካከለኛ ደረጃ የሚሸጋገሩበት ሁኔታ እየተመቻቸላቸው ነው። እንዲሁም ድርጅቶቹ የውጭ ምርቶችን የሚተካ ጥራት ያለው ምርት እንዲያመርቱ፣ አትራፊ እንዲሆኑና በቂ ገበያ እንዲያገኙ የበለጠ መስራት ያስፈልጋል።

በዑመር እንድሪስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።