በተሻለ አሰራር የተሻለ ውጤት ያስመዘገበው-የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት Featured

17 Feb 2017

አቶ ሰለሞን አንባቸው

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት ችግር ዛሬም አልተቀረፈም ። በተለይ ከሁለት ዓመት በፊት በስራ መግቢያና መውጪያ ሰዓት በሰራተኛው ዘንድ ያደርስ የነበረው መጉላላትና መጨናነቅ አይዘነጋም።መንግስት እጥረቱ  በሰራተኞቹ ላይ ያሳደረውን ጫና ለመቅረፍ ያስችል ዘንድ  በስራ መግቢያ እና መውጪያ ሰዓት የሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙ  ማድረጉም እንዲሁ የሚረሳ አይደለም።

     ይሄን የትራንስፖርት አገልግሎት  መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል በሚኒስትሮች ም/ቤት ደንብ ቁጥር 298/2006 የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋቋም አድርጓል::

      ድርጅቱ የተቋቋመበትን ዓላማ በማስፈፀም ረገድ ለፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎትን በተገቢው መልኩ ተደራሽ ለማድረግ በዕቅድ የያዘውን 410 አውቶብሶች በመረከብ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።ድርጅቱ አሁን እየሰጠ ባለው የሰርቪስ ትራንስፖርት አገልገሎት በዕቅድ የተያዘውን ተደራሽነት ከግቡ ማድረስ የተቻለ ሲሆን እስከ ታህሳስ ወር መጨረሻ ድረስ ድርጅቱ በቀን በአማካይ 364 አውቶብሶችን በማሰማራት በቀን  በአማካይ  68,500 በላይ  የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞችን በማጓጓዝ ላይ ይገኛል። ድርጅቱ መስመር ሲዘረጋ ታሳቢ ያደረጋቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ነዋሪዎች ያለመግባታቸው እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ለተዘረጉት መስመሮች የተመደቡት አውቶብሶች የሰርቪስ ትራንስፖርት  አገልግሎት  በበቂ ሁኔታ እየሰጡ በመሆናቸው 46 አውቶብሶችን በስራ መግብያና መውጫ ሰዓት ለህብረተሰቡ የታክሲ አገልግሎት እንዲውሉ ማድረግ ተችሏል፡፡

     ድርጅቱ የአገልግሎቱን ተደራሽነት  በማሳደግ ረገድ መነሻ መስመሮችን ከ 27 ወደ 44 እንዲሁም የመዳረሻ መስመሮችን ከ11 ወደ 16 ማድረስ ችሏል፡፡ለፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኛው ከሚሰጠው የሰርቪስ የትራንስፖርት አገልግሎት ባሻገር ከስራ ሰዓት መግቢያ እና መውጫ ሰዓት ውጪ 156 አውቶብሶችን እንዲሁም በሙሉ ቀን የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ 46 አውቶብሶችን በማሰማራት በቀን በአማካኝ ለ 36,000 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

    ድርጅቱ በ2009 በጀት አመት  በመጀመሪያው ግማሽ አመት በዝግጅት እና በትግበራ ምዕራፍ የተከናወኑ  ተግባራትን  አስመልክቶ በፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት የኮሚኒኬሽን ኃላፊአቶ ሰለሞን አንባቸውን  አነጋግረናል፦

    እንደ ኃላፊው ገለፃ የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ለፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኛው በሚሰጠው የሰርቪስና ለከተማው ህዝብ በሚያከናውነው የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት የተሻለ አፈፃፀም እያስመዘገበ ይገኛል።

    የድርጅቱ የ2009 በጀት አመት የግማሽ አመት የስራ አፈፃፀም ሲታይም በስራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት 390 አውቶብሶችን በግማሽ አመት ውስጥ ለማሰማራት አቅዶ ቢነሳም 364 አውቶብሶችን በመመደብ የዕቅዱን 93 ፐርሰንት ማሳካት ችሏል።ከላይ በዕቅድ ባስቀመጣቸው አውቶብሶችም 10 ሺህ ሰራተኞችን በደርሶ መልስ አገልግሎት ለመስጠት አቅዶ የነበረ ሲሆን ወደ ስራ ባሰማራቸው አውቶብሶች ከስምንት ሺህ በላይ ሰራተኞችን በማጓጓዝ የዕቅዱን 86 ፐርሰንት ማሳካቱን አብራርቷል፡፡ይህም ካለፈው አመት አመታዊ የስራ  አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ትግበራን ያሳየ ሲሆን፤ ተቋሙ በ2008 ዓ.ም የስራ ዘመን አመታዊ ዕቅድ ክንውን 390 አውቶብሶችን ወደ ሥራ ለማስገባት አቅዶ በ337 አውቶብሶች 12‚551‚143 ሰራተኞችን በድግግሞሽ በማጓጓዝ የዕቅዱን 67.4 ፐርሰንት አሳክቶ እንደ ነበር አቶ ሰለሞን አስታውሰዋል።

    እንደ አቶ ሰለሞን አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የተጠቃሚ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ የዳሰሳ ጥናት በማከናወን አምስት አቅጣጫዎች ያሉት ሁለት የፐብሊክ ሰርቪስ የመነሻ መስመሮች በመክፈት የተገልጋዮችን ፍላጎት ማርካት ተችሏል።ይህም ድርጅቱ ለሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመበትን አላማ ለማሳካት ያለውን ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ያሳየም እንደሆነም ነው የሚያሰምሩበት።

    በሌላም በኩል የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልገሎትን የሚጠቀሙ የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩን የኮሚኒኬሽን ኃላፊው ገልፀዋል።በተያዘው የግማሽ አመት የስራ አፈፃፀምም 11‚000 ሴት 13‚564 ወንድ ሰራተኞች የአገልግሎት መጠቀሚያ መታወቂያ መውሰዳቸውንም ተናግረዋል። ይህ በስድስት ወራት አፈፃፀም የታየው የተጠቃሚዎች ቁጥር መጨመር ድርጅቱ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት የሚያመለክት መሆኑንም  ጠቁሟል፡፡ 

    አቶ ሰለሞን አክለውም እንደተናገሩት ተቋሙ ከሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች ባሻገር ለከተማው ህዝብ በተመጣጣኝ ዋጋ የታክሲ አገልግሎትም ከተቋቋመ አንስቶ እየሰጠ ይገኛል።በመሆኑም በ2009ዓ.ም የግማሽ አመት የስራ አፈፃፀምም በ166 አውቶብሶች ዘወትር በሥራ ቀናት እንዲሁም ቅዳሜ ግማሽ ቀን ጨምሮ በሰጠው አገልግሎት ከዕቅድ በላይ 106 ፐርሰንት ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ።በተጨማሪም በዕቅድ በተያዙ አውቶብሶች በቀን ከሶስት ሺህ በላይ የከተማውን ህብረተሰብ ለማጓጓዝ ታቅዶ፤ከአራት ሺህ በላይ ተሳፋሪዎች አገልግሎት በመስጠት የዕቅዱን 134 ፐርሰንት አሳክቷል።ይህም ካለፈው አመት አመታዊ የስራ ክንውን ሪፖርት ጋር ሲነፃፀር የ101 ፐርሰንት ዕድገት አሳይቷል።

    በተጨማሪም ፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በያዘው 2009ዓ.ም በጀት አመት ግማሽ አመት በሰጣቸው የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞችና የኮንትራት እንዲሁም የሊዝ ትራንሰፖርት አገልግሎት የተሻለ ገቢ ማስመዝገቡንም የኮሚኒኬሽን ሀላፊው ገልፀውልናል።

     አክለውም እንደገለፁት በዚሁ መሰረት ድርጅቱ ለፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች በሚሰጥ የትራንስፖርት አገልገሎት 238‚572‚174 ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ ነበር።ከፌዴራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኞች የዕቅዱን 100 ፐርሰንት ገቢ ማስግኘት ተችሏል። ይህም ድርጅቱ በ2008 አመታዊ ገቢው በዚሁ የአገልገሎት ዘርፍ 114,733,642.00ብር ገቢ ማስግኘት ችሎ የነበር ሲሆን፤ ይህም ከ2009 የስድስት ወር የስራ አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር በስድስት ወር አፈፃፀሙ የተሻለ እንደሆነ አብራርተዋል።

    በሌላ በኩልም በተቋሙ ለከተማው ማህበረሰብ በሚሰጠው የታክሲ አገልገሎት በዚሁ በስድስት ወር 8‚147‚310 ብር ገቢ ለማስግኘት ታስቦ፤  9‚735‚332.00 ገቢ በማስግኘት የዕቅዱን 119 ፐርሰንት ማሳካቱን አቶ ሰለሞን ገልፀው፤አክለውም እንደገለፁትም  በዚህ የታክሲ አገልግሎት የተገኘው ገቢ በ2008ዓ.ም ከተገኘው አመታዊ ገቢ ብር 13,412,985 ጋር ሲወዳደርም የግማሽ አመቱ የስራ አፈፃፀም  ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል።

    የኮንትራት ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጠው ይኸው ድርጅት ለተለያዩ ድርጅቶች አገልግሎት በመስጠት 3‚665‚587.00 ገቢ በማስግኘት በዕቅድ ተይዞ የነበረ ሲሆን፤ በትጋት በመስራት 1‚200‚000 ብር በላይ በማከናወን የዕቅዱን 305 ፐርሰንት ተግባራዊ መደረጉን ጠቁሟል።ባለፈው አመትም ድርጅቱ በበጀት አመቱ ውስጥ ለተለያዩ ድርጅቶች የኮንትራት አገልግሎት በመስጠት በድምሩ ብር 2,105,036.00 ገቢ ያስገኘ ሲሆን፤ ይህም በ2009ዓ.ም የግማሽ አመት የስራ አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር በሁለቱም የስራ ዘመን በኮንትራት ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፉ የተሻለ ሥራ ማከናውኑን ያመላክታል» ብለዋል።ይህን የተሻለ ገቢ ማግኘት የተቻለው ተቋሙ የሚሰጠውን አገልገሎት በሚዲያ የማስተዋወቅ ሥራ መሰራት በመቻሉም እንደሆነ ጠቁመዋል።

    አቶ ሰለሞን እንደገለፁት ፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል አንዱ በሆነው የሊዝ ትራንስፖርት አገልግሎትም መልካም የሚባል አፈፃፀም አስመዝግቧል። በዚሁ የአገልግሎት ዘርፍ 4‚633‚200.00 ገቢ ለማግኘት አቅዶ 4‚018‚809 ብር ገቢ በማስገኘት 87 ፐርሰንት የዕቅድ ክንውን አስመዝግቧል።

    ኃላፊው በመጨረሻ ምንም እንኳ ድርጅቱ አገልግሎቱን አዳዲስ በተከፈቱ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለመስጠት ዕቅድ ነድፎ ቢንቀሳቀስም ነዋሪዎቹ ባለመግባታቸው ፈተና ቢሆንበትም በ2009 ዓ.ም ባከናወነው የስድስት ወራት ስራ አፈፃፀም  ውጤታማ ሆኗል፡፡  በተጨማሪም በ2009ዓ.ም በግማሽ አመቱ የስራ አፈፃፀም የተገኘው ገቢ በ2008ዓ.ም ከተገኘው አመታዊ ገቢ ጋር ሲነፃፀር የተሻለ እድገት ማሳየት ችሏል።ይህም ውጤት ሊመዘገብ የቻለው በየስራ ዘርፉ የተሻለና ክትትል ያለው የስራ ክንውን በመካሄዱ ነው።

ወይንሸት ካሳ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።