ባዮ ሪፋይነሪ-ቀጣዩ የኢኮኖሚ ደጋፊ Featured

28 Jul 2017

የሸንኮራ ተረፈ ምርት በዚህ መልክ ተቀነባብሮ ወደ ተለያዩ ምርቶች ይቀየራል፤

በሸንኮራ አገዳ የስኳር ምርት ላይ የተመሰረተ የባዮ ሪፋይነሪ ልማት ፍኖተ ካርታ የኢ.... ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት በተመ ራማሪዎች ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት ባሳለፍነው ሳምንት መዘገባችን የሚታወስ ነው። ዘርፉ አዲስ እና ቀጣይነቱ አስተማማኝ የሆነ የዕድገት ምንጭ መሆኑ ታምኖበት መንግሥት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሂደቱን ለመጀመር በተመራማ ሪዎች ጥናቶችን እያስጠና ይገኛል።

ይህ ዘርፍ በሚኒስትር ማዕረግ የግብርና እና ባዮ ኢኮኖሚ ጉዳዮች ፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ዘርፍ አስተባባሪ በሆኑት በዶክተር ካሱ ይላላ የሚመራ ነው። ከስኳር ተረፈ ምርት የሚገኘው የባዮ ሪፋይነሪ ልማት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ባለሙያዎች በተለያየ ጊዜ ጠቁመዋል። መንግሥት በሰጠው መመሪያና በተደራጀ መንገድ በፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ማእከል መሪነት አገሪቷ በዘርፉ ያላት አቅም እንዲለይ ተደርጎ የመጀመሪያው ዙር ለውይይት ቀርቧል።

በውይይቱ ላይ ፍኖተ ካርታውን እና ደጋፊ ጥናቶችን ያቀረቡት ምሁራን መንግሥት በዚሁ ጉዳይ ላይ በቁርጠኝነት የሚሠራ ከሆነ በቀጣዮቹ ጊዜያት ዋንኛ የኢኮኖሚ ደጋፊ መሆን ይቻላል በማለት አመላካች ምክረ ሀሳብ ሰንዝረዋል። ስኬታማ ለመሆንም የተቀናጀ የኢንዱስትሪ መንደር መገንባት፤ልማቱ ይዞት የሚመጣውን ዕድል አሟጥጦ ለመጠቀም ዘግጅት ማድረግ፤ እንዲሁም ቴክኖ ሎጂን፣ ኢንዱስትሪዎችን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ማቀናጀት ያስፈልጋል ብለዋል።

ባዮቴክኖሎጂን ለእድገት ትልቅ አቅም ሆኖ የሚያገለግል ወሳኝ ኢንዱስትሪ አድርጎ በመውሰድ ምርምሩን የሚያስተባብር ብሔራዊ «የባዮ ቴክኖሎጂ ምርምር ኢንስቲትዩት» ማቋቋሙን ትልቅ ጅምር ነው የሚሉት ምሁራኑ ከዚህም ባለፈ ተግባራዊነቱ ላይ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚያስፈልግ ምክረ ሀሳብ ይለግሳሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት የባዮ ሪፋይነሪ ልማት ፍኖተ ካርታ ጥናት አጠቃላይ ይዘትን ያስቀመጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁር ፕሮፌሰር በላይ ወልደየስ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሸንኮራ አገዳ ለማምረት መልከዓ ምድሩ የተመቸ መሆኑን በጥናታቸው ላይ አስቀምጠዋል። አሁንም በስፋት የሸንኮራ አገዳ ምርት እርሻዎች እየተከናወኑ መሆኑን ይናገራሉ። በዚህ ግብአት በጣም በርካታ ጠቀሜታ ያላቸው ኬሚካሎችን ማምረት እንደሚቻልም ያስረዳሉ። የሸንኮራ አገዳ ለስኳር ምርት ከሚሰጠው ጠቀሜታ ባሻገር 50 እና ከዚያ በላይ ለሆኑ ኬሚካል ማምረቻዎች ሊውል ይችላል በማለት ያለውን ሰፊ ጠቀሜታም ይተነትናሉ። ይህም አገሪቷ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የምታስገባቸውን ምርቶች በቀላሉ እዚሁ በማልማት መቀነስ ያስችላል ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር የሠሩትን የጥናት ውጤት ያስገኘውን ሲዘረዝሩ ።

ኢኮኖሚ ጉዳዮች ፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር ካሱ ኢላላ በበኩላቸው የልማታዊው ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ባዮ ቴክኖሎጂ ለአገሪቷ ፈጣን የህዳሴ ጉዞ ትልቅ አቅም ሆኖ የሚያገለግል ወሳኝ ኢንዱስትሪ አድርጎ በመውሰድ ምርምሩን የሚያስተባብር ብሔራዊ የባዮ ቴክኖሎጂ ምርምር ኢንስቲትዩት ማቋቋሙ ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ መሆኑን ይገልፃሉ። ይህ እንዳለ ሆኖ ባዮቴክኖሎጂ ብቻውን የቆመ እንዳልሆነ ለማሳየት ባዮ ቴክኖሎጂያዊ ስርዓቱን ከኬሚካል ሳይንስ ኢንጅነሪንግ ስርዓት ጋር በተመጋጋቢነት እንዲተሳሰሩ እየሠራ ይገኛል ይላሉ። ከግብርናው መዘመን ጋር ተያይዞ እያደገ የሚመጣው የባዮማስ ምርት አማካኝነት በታዳሽ ሀይል ብቻ ሳይሆን በታዳሽ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች አቅርቦት ዘላቂና አስተማማኝነት ባለው መልኩ የህዳሴው ጉዞ አንዱና አይነተኛ የማምረት ስርዓት እንዲሆን አቅጣጫ መቀመጡን ነው የሚያስረዱት።

መንግሥት እንደ መነሻ ከሸንኮራ ስኳር ተረፈ ምርት ባዮ ማስ ላይ የተመሰረተ የባዮ ሪፋይነሪ ልማት ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱን የሚናገሩት በዶክተር ካሱ፤ በዚህ ሂደትም ከ50 የሚበልጡ ለተለያዩ ግልጋሎቶች መዋል የሚችሉ ምርቶችን ማግኘት እንደሚቻል በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉት ምሁራን ማመላከ ታቸውን ይናገራሉ። በመሆኑም በዘርፉ ላይ ትኩረት በመስጠት ባዮ ኢኮኖሚውን በመገንባት በዓለም ላይ በፍጥነት ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረ ያለውን የንግድ ሂደት ለመቀላቀል ታስቧል። እየዳበረ ባለው የዚህ አይነቱ ኢኮኖሚ እንደ አገር መቀላቀል መቻል ለህዳሴው ፈጣን ጉዞ ትልቅ ትርጉም እንደሚኖረውም መረጋገጡንም ነው የሚናገሩት። ቀጣይ እና አስተማማኝ የእድገት ምንጭ መሆኑም በጥናቶቹ ላይ ተመላክቷል።

«መንግሥት ከዘርፉ ስፋት አኳያ ጥናቱ በሁለት ተከፍሎ እንዲሠራ አድርጓል። አንደኛው ክፍል ተጠናቆ ለከፍተኛ የመንግሥት አካላት ለውይይት ቀርቧል። ሁለተኛው ጥናት በደቂቅ ዘአካላት ባዮ ቴክኖሎጂ የሸንኮራ ስኳር ተረፈ ምርቶችን ወደ በርካታ ጠቀሜታ ወዳላቸው ምርቶች በምን መልኩ መቀየር እንደሚችሉ እና ዝርዝር ጉዳዮችን የሚያመላክት ይሆናል» የሚሉት ዶክተር ካሱ፤ ግኝቶቹ የለውጥ ሂደቱ ላይ ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ሲሆን፤ በዚህ ዙሪያ እየተደረገ ያለው የፍኖተ ካርታ ጥናትም «በደቂቅ ዘአካላት» ምርምር በላብራቶሪ ሥራ ላይ ብቻ ሳያተኩር የምርት ሂደቱንም በመከታተል ሰፊ ምርምር የሚያደርግ ይሆናል ይላሉ። ከተረፈ ምርቱ የሚገኝ በርካታ ምርቶች የአገሪቷን ኢኮኖሚ ከመደገፍ አልፈው ከዚህ ቀደም ከውጪ አገራት በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የሚገባውን ምርት የሚያስቀር ይሆናል። በሂደትም ምርቶቹን ወደ ውጭ የመላክ እቅድ አለ። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ተረፈ ምርቱ አላግባብ እየባከነ እና እንዲያውም ለማስወገድ ትልቅ ችግር እንደሚፈጥር አላስፈላጊ ነገር እየታየ መሆኑን ይገልፃሉ።

«ዘርፉ በሳይንስ አና ኢንጅነሪንግ እውቀት እና ክህሎት እንደየደረጃው ብቁ የሆኑ ወጣቶችን ማፍራት ይጠይቃል» የሚሉት ዶክተር ካሱ ሌላኛው ትልቅ ሥራ መሥራት ያለበት በብቁ የሰው ሀይል ላይ መሆኑን ያስረዳሉ። ለዚህ ምክንያት የሚሉትንም ያስቀም ጣሉ።

መንግሥት በሚከተለው የ70/30 የትምህርት ፖሊሲ መሰረት በየዓመቱ ከ80 ሺ በላይ የተፈጥሮ ሳይንስ እና ኢንጅነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቃን ማፍራት ተችሏል። አገሪቷ በስፋት እያገኘች ያለችውን የተማረ አምራች ሀይል በዚህ ዘርፍ ላይ ለማሰማራት እቅድ ተይዟል። ይህ ሰፊ የኢኮኖሚ ምንጭ የስራ እድል በመፍጠሩ ረገድም ላቅ ያለ ሚና ይጫወታል ማለት ነው።

በአብዛኛው ጊዜ በአንድ ዘርፍ ላይ የእውቀትም ሆነ የክህሎት እጥረት መኖሩን መረዳት የሚጀምረው ችግሩ በሚከሰትበት ወቅት ነው ይላሉ የዘርፉ አስተባባሪ። በመሆኑም የሰው ሀይል የሚያበቁ ዩኒቨርሲቲዎች ለኢንዱስትሪው የሚያስፈልገውን የሰው ሀይል በትምህርት አይነት፣ በእውቀት የትምህርት ደረጃ የስልጠና ፕሮግራም ቀደም ብለው ማዘጋጀታቸው ለዚህ አዲስ ዘርፍ ስኬታማነት ወሳኝ መሆኑን በምሁራኑ የተጠናው ፍኖተ ካርታ ማመላከቱን ይጠቁማሉ።

በድንገት ለሚፈጠረው ለዚህ አይነቱ የሰለጠነ የሰው ሀይል ፍላጎት እንደ ጅምር ዘርፉን ሊቀላቀሉ የሚችሉ ባለሙያዎችን ባፋጣኝ ለማብቃት ዩኒቨርሲቲዎቹ በጋራ እና በተናጠል መሥራት እንደሚጠ በቅባቸውም ነው የሚያሳስቡት።

ትምህርት ሚኒስቴር እና ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለእነርሱ ተጠሪ የሆኑትን ዩኒቨርስቲዎች በምርምር፣በመሰረተ ልማት እንዲሁም ብቃት ያላቸው ተመራማሪዎችን የማፍራት ቁመናቸው እየገዘፈ እንደመጣ ዶክተር ካሱ እምነታቸውን ያስቀምጣሉ። በመሆኑም ለአገሪቷ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ይሆናል ተብሎ የሚታሰበው «የባዮ ኢኮኖሚ» ዘርፍ በዘመናዊ ሳይንስ እውቀት እና ክህሎት የሚደግፉ ባለሙያዎችን በተጨማሪ ማፍራት አስፈላጊ መሆኑ እንደማያጠ ያይቅና በዚህ ዘርፍ ላይ ገብቶ በብቃት የሚሠራ ባለሙያ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን ጥናቱ ያመላክታል። እንደ አማራጭ አገሪቷ ባላት የባለሙያ አቅም ሥራውን በማስጀመር ወደ ፊት በጥራት እና በብዛት በዘርፉ የሚሰማራ የሰው ሀይል መፍጠር እንደታሰበም ይገልፃሉ።

«ፍኖተ ካርታውን ወደ አፈፃፀም ለማሸጋገር ቀጣይ ሥራዎች ይሠራሉ» የሚሉት አስተባባሪው፤ በቅድሚያ እንደ ተሞክሮ መቅሰሚያ በተለያዩ አገራት የሚገኙ የተመረጡ የማምረቻ ማእከላት፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና በዘርፉ ያሉትን የምርምር ተቋማት በመጎብኘት በጥናቱ ላይ ማስተካከያ እንደሚደረግ አመላክተዋል። ዘርፉ ግዙፍ ከመሆኑ አኳያ ከአገሪቷ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ተፈፃሚ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ያስረዳሉ። በዚህም የተለያዩ ፕሮግራሞችን፣ ፕሮጀክቶችና የኢንቨስትመንት ሀሳቦች እንደ ቅደም ተከተላቸው እንደሚቀርቡ ይገልፃሉ። የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ማእከል ከአስፈፃሚ ተቋማት ጋር በመሆን በእውቀት ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ሀሳብ ያቀርባል በማለት ሀሳባቸውን ይቋጫሉ።

ከዚህ ዘርፍ ከሚገኙት ጠቀሜታዎች መካከል የኤታኖል ምርት አንዱ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ይህም የመኪና ናፍጣ እና ነዳጅን በከፊል አንዳንዴም ሙሉ ለሙሉ በመተካት የሀይል ምንጭ ይሆናል። የኤሌክትሪክ ሀይል ለማመንጨትም ከሸንኮራ ስኳር ተረፈ ምርት የሚገኘውን ግብዓት መጠቀም ይቻላል። ይህም ብቻ ሳይሆን ከዚህ ዘርፍ በርከት ያሉ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች ያሉት ምርት ማግኘት ይቻላል። ለፕላስቲክ ቱቦ፣ለቤት ቁሳቁስ ማምረቻ፣ ለቀለም ፋብሪካ ኬሚካል ግብዓት...እና ሌሎችም በርካታ ጠቀሜታዎችን ማግኘት ይችላል።

መንግሥት በጉዳዩ ላይ ይህንን ትኩረት አድርጎ መንቀሳቀሱ አበረታች ጅምር ቢሆንም ሌሎች ባለድርሻ አካላት አጋዥ ሀይል መሆን ካልቻሉ ጥረቱ «በአንድ እጅ እንደ ማጨብጨብ» ይሆናል። በተለይም ባለሀብቱ በዚህ ዘርፍ ላይ ሙዋዕለ ንዋዩን በማፍሰስ አገርን፣ ማህበረሰቡን ብሎም እራሱንም የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ ሰፊና ትልቅ እድል ይኖረዋል ሲሉ ምሁራኖች አስተያየታቸውን ያስቀምጣሉ።

ዳግም ከበደ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።