‹‹በመንገድ ጥገና አፈፃፀማችን ከፍተኛ ቢሆንም ጥራት ላይ አሁንም ይቀረናል››- ኢንጂነር መኮንን ጥበቡ Featured

01 Aug 2017

በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የራስ ኃይል አስፋልት መንገድ ጥገና  ስራዎች  ዳይሬክተር

  የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ከአሁን ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መጠነ ሰፊና ሁሉን አቀፍ የመንገድ ጥገና አከናውኗል፡፡ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳየው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በእቅድ ከተያዘው የ84 ኪሎሜትር የአስፓልት መንገድ ጥገና 132 ኪሎሜትር ማከናወን የተቻለ ሲሆን ይህም አፈፃፀሙ በእቅድ ከተቀመጠው በላይ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ለመሆኑ በመንገድ ጥገና ዘርፍ ምን የተለየ ስራ ቢሰራ ነው ከእቅድ በላይ አፈፃፀም ማምጣት የተቻለው? ፣በጥገናው ረገድ የነበሩ ክፍተቶችስ ምን ነበሩ? በሚሉና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የራስ ኃይል አስፋልት መንገድ ጥገና ስራዎች  ዳይሬክተር ከሆኑት ከኢንጂነር መኮንን ጥበቡ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

 አዲስ ዘመን፡-  በ2009 የመጀመሪያው ግማሽ አመት በመንገድ ጥገና የነበረው አፈፃፀም በጣም ከፍተኛ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ለመሆኑ አፈፃፀሙ ከፍተኛ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው?

ኢንጂነር መኮንን፡- በበጀት አመቱ 84 ኪሎሜትር የአስፓልት መንገድ ለመጠገን አቅደን 132 ኪሎሜትር ማሳካት ችለናል፡፡ ይህም አፈፃፀማችን በጣም ከፍተኛ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ለጥገናው ዘርፍ ትልቅ ትኩረት መስጠታችን የስኬቱ አንዱ ሚስጥር ነው፡፡  ከዚህ በፊት ለመንገድ ጥገና ከሚያዘው በጀት በአንፃራዊነት በአሁኑ አመት የተሻለ መሆኑም ለመንገድ ጥገናው ከፍተኛ አፈፃፀም የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ በሰራተኛው ላይ ጥሩ የሆነ መነሳሳት እንዲኖር ተከታታይነት ያለው ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ በየጊዜውም ሰራተኛው የሚያከናውናቸው ስራዎች ከጊዜ፣ ከጥራትና ደህንነት ከመጠበቅ አንፃር  ስለሚገመገም ይህም ለአፈፃፀሙ የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡

 አዲስ ዘመን፡- በሁለተኛው ግማሽ አመትስ የነበረው አፈፃፀም ምን ይመስል ነበር? ምንስ የተለየ ስራ ተሰርቷል?

 ኢ/ር መኮንን፡- የመጀመሪያውን ግማሽ አመት አፈፃፀማችንን መነሻ በማድረግና እቅዳችንን በመከለስ በበጀት አመት ውስጥ ከተያዘው 84 ኪሎሜትር የአስፋልት መንገድ ጥገና 65 ኪሎሜትር ማከናወን ተችሏል፡፡ ይህም ከመጀመሪያ ግማሽ አመት አፈፃፀም ጋር ሲወዳደር ተመሳሳይና አፈፃፀሙም ከመቶ ፐርሰንት በላይ ነው፡፡ በመጀመሪያው ግማሽ አመት የነበረንን ከፍተኛ አፈፃፀም ይዘን ስለቀጠልን በሁለተኛው ግማሽ አመትም ይህንኑ  መድገም ችለናል፡፡ ያልተቋረጡ ስልጠናዎችን ለሰራተኞቻችን መስጠት ችለናል፡፡ በጥገና ስራው ላይ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በስራ ላይ ለማዋል የጃፓን የልማት ተራድኦ ድርጅት ድጋፍም ጉልህ ነበር፡፡ በሌሊትም ጭምር ሳይቆራረጥ ስራዎችን መስራትና ለሰራተኞቻችን ክትትል አድርገናል፡፡ በተለይ ደግሞ ሰራተኞችን ለማነሳሳትና ለማነቃቃት የተለያዩ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት የተሻለ አፈፃፀም ላመጡ ሰራተኞች ወይም ቡድን ማበረታቻ ማድረጋችን የበለጠ ውጤታማ እንድንሆን ረድቶናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በመንገድ ጥገና ዋነኛ ችግሮች ምን ነበሩ? የተወሰዱ የመፍትሄ ርምጃዎችስ?

ኢ/ር መኮንን፡- የመንገድ ጥገናው በዋናነት በሌሊት ከመከናወኑ አንፃር አልፎ አልፎ  ጠጥተው የሚያሽከረክሩ በመኖራቸው የባለስልጣን መስሪያቤቱ ማሽኖች ይገጫሉ፡፡ ይህም ከማሽኖቹ መገጨት ባሻገር በሰራተኞች ደህንነት ላይ የራሱ አሉታዊ  ተፅእኖ አሳድሮ ነበር፡፡ ከክፍለከተሞች ፖሊስ ጋር በመነጋገርና እገዛ በማግኘት ድጋፍና ክትትል አድርገውልናል፡፡ በጥገናው ረገድ ብዙ የሰራን ቢሆንም አሁንም ጥገና የሚያስፈልጋቸው መንገዶች በመኖራቸው ይህን ተደራሽ ለማድረግ  ለቀጣይ አመት እቅድ እየሰራን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በሰራተኛው ላይ የአመለካከት ለውጥ በማምጣትና የለውጥ መሳሪያዎችን በመጠቀም በኩል ያለው አፈፃፀም ምን ይመስላል?

ኢ/ር መኮንን፡- መጀመሪያ ላይ ሰራተኛው ስራውን በአብዛኛው የሚያከናውነው ሌሊት ከመሆኑ አኳያ  ከደህንነት አንፃር የሚያነሳቸው በርካታ ችግሮች ነበሩ፡፡ እነዚህን ነገሮች ከሞላ ጎደል ለሰራተኞች ማሟላት ችለናል፡፡ ይህም በሰራተኛው ላይ ትልቅ መነሳሳት ፈጥሯል፡፡ በየጊዜው የማነቃቂያ ስልጠናዎችን እንሰጣለን፡፡ ችግሮች ሲያጋጥሙም ከሰራተኛው ጋር ቁጭ ብለን እንነጋገራለን፡፡ እያስተካከልን የምንሄድበት ሁኔታም አለ፡፡ ይህም በሰራተኛው ዘንድ ጥሩ  አመለካከት እንዲኖረው በር ከፍቷል፡፡ የበላይ አመራሩም እየመጣ ሰራተኛውን መጎብኘቱ ሰራተኛው እንዲበረታታ አድርጓል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል ጥገናን በጥራት ከማከናወን አንፃር በርካታ ቅሬታዎች ይነሱ ነበር፡፡ አሁን ላይ ጥገናውን በፍጥነት ከማከናወን አንፃርስ ጥራቱ ላይ ተፅእኖ አላሳደረም?

ኢ/ር መኮንን፡- በመንገድ ጥገና የጥራት ችግር እንዳይኖር ትክክለኛውን የጥገና ሂደት ለመከተል ሞክረናል፡፡ አንዳንድ የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችን፣ መብራቶችን ፣መቁረጫ መሳሪያዎችን  በመጠቀም የጥገና ስራውን ለማከናወን ሞክረናል፡፡ የጥገናውን ስራ የሚቆጣጠር በመንገድ ፈንድ ፅህፈት ቤት የተመደበ ስራውን የሚከታተል አደራ ኢንጂነሪንግ መድበናል፡፡ በተመሳሳይም ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የመንገድ ጥገና ስራውን የሚቆጣጠር ከላብራቶሪ፣ ጥራትና ቁጥጥር ክፍል የተውጣጣ የሞኒተሪንግ ቡድን እንዲመደብ አድርገናል፡፡ በዚህም መሰረት የጥራቱን ችግር ለመቅረፍ ጥረት አድርገናል፡፡ በመሆኑም በፊት ከነበረው አንፃር ብዙ ሄደናል፡፡ ነገር ግን አሁንም በጥራት ረገድ የሚቀሩ ነገሮች አሉ፡፡ የጥራት ችግር ካለ ሰራተኛውን በስልጠና፣እውቀቱን በማጎልበት ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት አድርገናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- መንገዶች ተጠግነው ወዲያውኑ ለትራፊክ ክፍት ሲሆኑ በመንገዶቹ ቆይታና ደህንነት ላይ ችግር አይፈጥርም?

ኢ/ር መኮንን፡- ስራው የመንገድ ጥገና ከመሆኑ አንፃርና ጥገናውም የሚከናወነው በከተማ ውስጥ በመሆኑ መንገዶቹን ጠግኖ ወዲያውኑ ለትራፊክ ክፍት ከማድረግ ውጪ አማራጭ የለንም፡፡ ነገር ግን ጥገናው  የሚፈለገውን የኮምፓክሽን ቆይታ፣ ጥራትና፣ የአስፋልት መጠን እስካሟላና ትክክለኛውን ደረጃ እስከጠበቀ ድረስ ምንም አይነት ችግር አይፈጥርም፡፡

አዲስ ዘመን፡- አሁንም ድረስ ጥገና ያልተዳረሰባቸው መንገዶችስ በባለስልጣኑ በኩል እንዴት እየታዩ ነው?

ኢ/ር መኮንን፡- ጥገና ያልተዳረሰባቸው መንገዶች በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሚታወቁ ናቸው፡፡ ነገርግን አብዛኞቹ በአዲስ መልክ እንዲሰሩ ለኮንትራክተሮች የተላለፉ ናቸው፡፡ ለአብነትም ከላምበረት በኮተቤ ካራ የሚወስደው መንገድ ይጠቀሳል፡፡ የጥገናውን ስራ ስንሰራ ቅድሚያ ጥገና የሚያስፈልጋቸውን በመለየትና በፌዝ በመከፋፈል ነው፡፡ በሚቀጥለው በጀት አመትም በጥገና ያልደረስንባቸው አካባቢዎች ላይ እንገባለን፡፡ በክረምቱ ወቅትም ችግር ፈቺ ጥገናዎች ባናደርግም ጊዜያዊ ጥገናዎችን  አከናውነናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአጠቃላይ በበጀት አመቱ በመንገድ ጥገና ረገድ የነበረው አፈፃፀም ምን ይመስላል?

ኢ/ር መኮንን፡- የጥገና ስራ ሲባል መንገድን ብቻ ሳይሆን የፍሳሽ ውሃ ማስወገጃ ቱቦዎችን፣ የእግረኛ መንገዶችንና የመንገድ ዳር መብራቶችን የሚያካትትና ሁሉን አቀፍ በመሆኑ እነዚህን ስራዎችን ሁሉ ለመስራት ሞክረናል፡፡  የጥገና ስራችን አስፋልትን ከመጠገን በዘለለ ሌሎች ጥገናዎችንም የሚያካትት ነው፡፡ አደባባዮችን በማፍረስ በመብራት እንዲለወጡም አድርገናል፡፡ ይህም ከመንገድ ጥገና ውጪ የሰራነው ተጨማሪ ስራ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ጨምረው በአጠቃላይ የጥገናው ስራ ከሚፈለገው በላይ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ባጠቃላይ አፈፃፀማችን ፣የሰራተኛው አመለካከትና ከውጪ የሚመጣው ግብረመልስ ጥሩ የሚባል ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የቀጣይ እቅዳችሁ ምንድን ነው?

ኢ/ር መኮንን፡- ቀደም ሲል የጥገና ስራው በሶስት ቡድን ብቻ ይሰራ ነበር፡፡ ነገር ግን  በቀጣዩ አመት የጥገና ክፍሉን ወደ አምስት ቡድን ከፍ ማድረግ  ነው የፈለግነው፡፡ ይህም ሲሆን በመንገድ ጥገና ረገድ ያለው ተደራሽነት ይሰፋል፡፡ ይህም የሰው ኃይል በማሟላትና የጥገና መሳሪያዎችን በመጨመር የሚከናወን ይሆናል፡፡ ከዚህም ባሻገር አምስት ሪጅኖችን አዋቅረናል፡፡ ከሪጅኖቹ በሚመጣው ዳታ መሰረት እኛ ጥገናውን ለመስራት ተዘጋጅተናል፡፡ አስፈላጊ የሚባሉ መሳሪያዎችን በመጠቀምና ተጨማሪ የሰው ኃይልና ባለሙያዎችን በመጨመርና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም  ከዘንድሮው በተሻለ በተደራሽነትም በጥራትም ለመስራት አቅደናል፡፡ አሁን የዝግጅት ስራ ላይ ነው ያለነው፡፡ የ2010 እቅድ እያወጣን ነው፡፡ ቅድሚያ ጥገና የሚያስፈልጋቸውን መንገዶች በመለየት ለመስራት እያቀድን ነው፡፡ 

  አስናቀ ፀጋዬ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።