በአግባቡ ያልተጠቀምንበት «ሆርቲካልቸር» Featured

07 Aug 2017

አገሪቱ ለዘርፉ ትኩረት ከሰጠች በዓመት ከአትክልትና ፍራፍሬ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ትችላለች ፤

የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን ለማሳደግ ከገቢ ምርቶች ይልቅ ወጪ ምርቶችን ማሳደግ እንደሚገባ ይታመናል። የሀገር ውስጥ ምርቶችን ወደ ውጭ መላክ ሲባል ተወዳዳሪ ሆኖ መቅረብ ላይ ቅድሚያ ሊሰጠው  እንደሚገባም ዕሙን ነው። በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ መውጣት፤ ለዚህም ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ገበያው የሚያስፈልገው ምንድነው? የሚለውን መለየትም ይገባል።

 በመቀጠልም በመጠንና በጥራት ተወዳዳሪ ሆነው መውጣት የሚችሉ ምርቶችን ማቅረብ፤ እንዲሁም ገበያው በሚፈልገው መጠን ደረጃውን የጠበቀ መሆንም ይኖርበታል። ይሁን እንጂ ሀገሪቱ ከሌሎች አጎራባች ሀገራት በተሻለ የምርት ዓይነትና ብዛት ቢኖርም ከኬንያ እንዲሁም ሌሎች ሀገራት ከዘርፉ ከሚያገኙት ጥቅም ባነሰ ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ። እኛም ለዛሬ በጉዳዩ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራች ላኪዎች ማህበር፤  እንዲሁም የዕውቅና ማረጋገጫ እና ቁጥጥር ጋር ተያይዞ የሚመለከ ታቸውን አካላት አነጋግረናል።

ስለ ዘርፉ 

አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራች ላኪዎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር ናቸው። ሀገሪቱ ከዘርፉ በዓመት ከአትክልትና ፍራፍሬ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት የሚያስችል አቅም እንዳላት ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ዘርፉ ለሀገሪቱ በሚጠበቀው ደረጃ ውጤት ማምጣት አልቻለም። በዚህም በአበባ፣ በአትክልትና በፍራፍሬ ከሦስት መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት አልተቻለም። ለዚህም ተጠቃሽ ከሆኑ ማነቆዎች መካከል አንዱና ዋነኛው የትራንስፖርት አቅርቦት ነው። በዚህም አብዛኛው ምርት በአውሮፕላን ይሄዳል። ይህ ከዋጋ አንፃር ውድና አዋጪ አይደለም። መንግሥትም ችግሩን ለመቅረፍ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል። በዚህም የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር ሥራ መጠናቀቁ ቀደም ባሉት ጊዜያት የነበሩትን ችግሮች በተለይ ከዋጋ ጋር ተያይዞ የነበረውን ችግር ያቃልላል ተብሎ ይጠበቃል።

ከባቡሩ ሥራ መጠናቀቅ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ባለሀብቶች በሀገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ እየገቡ መሆናቸው ሌላው መልካም ገፅታ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል። በሀገር ውስጥም ሆነ  በውጭ ያሉ ባለሀብቶች በዘርፉ ለመሰማራት ጥናቶች እያካሄዱ ሲሆን ቀደም ብለው ሥራውን እየሰሩ ያሉትም ለማስፋፋትና ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረዋል።

በአውሮፓ የሚገኙ በርካታ ባለሀብቶችም የመሬት አቅርቦት ከተስተካከለ ወደ ሀገር በመግባት ሥራው ላይ ለመሰማራት ያላቸውን ፍላጎት በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደሚገልፁ ዋና ዳይሬክተሩ ይናገራሉ። ይህ ተጠናክሮ ከቀጠለ ሀገሪቱ በአትክልትና ፍራፍሬ ያጣችውን ገቢ ያስገኝላታል። ነገር ግን በሀገር ውስጥ ያሉት አካላት ዘርፉን ለማስፋፋት ፍላጎት ቢያሳዩም  ትልቅ ተግዳሮት የሆነው የመሬት፣ የማዳበሪያ፣ የኬሚካል እንዲሁም መሰል ግብዓት አቅርቦትና ከፖሊሲ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉት ክፍተቶች ናቸው። ለችግሮቹም መፍትሄ ለማምጣት ከመንግሥት ጋር በመሆን መሥራት ይጠበቃል። በተያያዘም በዋናነት የቀዝቃዛ ፍሪጅ አገልግሎት ከሚሰጡ ድርጅቶች ጋር ዋጋውን ለማሻሻል ማህበሩ ውይይቶችን  በማካሄድ ላይ ነው።

አምራቾች ምን ይላሉ?

በመቂ ባቱ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ህብረት ሥራ ማህበር የሚሰሩት አቶ መርጊያ ቶላ እንደሚናገሩት፤  ዘርፉ የገበያ ትስስርን ከመፍጠር ጀምሮ የሥራ ዕድል በመፍጠር ያለው ፋይዳ የጎላ ነው። ከዚህ ጎን ለጎንም በውጭ ተወዳዳሪ ሆኖ በመውጣት የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው። ይሁን እንጂ በዘርፉ አሁንም ያልተፈቱ ጎታች ማነቆዎች እንዳሉ ያለበትን የዕድገት ደረጃ በማየት መገመት አያዳግትም።

 አርሶአደሩ በዘርፉ ከአምራቾች ጋር ባለው ትስስር እንዲሁም በራሱ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ የሚችልበት ዘርፍ ነው። ይሁን እንጂ ባለው የገበያ ውስንነት ምክንያት ችግር ሲያጋጥመው ይስተዋላል። በተለይም አትክልትና ፍራፍሬ የዕለት ተዕለት ገበያ የሚፈልግ ነው። ይህ ካልሆነ ደግሞ የሚበላሽ በመሆኑ ዘለቄታዊ ገበያ መፈጠር ላይ ያሉ ችግሮችን ለማቃለል ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ይጠቁማሉ። የገበያ ትስስር ጠንካራ አለመሆን በዘርፉ የሚስተዋል ክፍተት ሲሆን የገበያው ሥርዓት ወጥ ሆኖ ቀድሞ የነበሩ ህገ-ወጥ አሠራሮች ከመከላከል አኳያም መንግሥት ከአምራቹ ጋር በመሆን መስራት እንደሚኖርበት ይናገራሉ።

እንደ አቶ መርጊያ ማብራሪያ፤ ምርት ሲመረት ለማን እንደሚመረት ማወቅ ይጠይቃል። የአምራቹ የምርት ሂደት ገበያውን ያማከለና የተሻለ የግብርና አሠራርን የጠበቀ መሆን እንዲችል ለአርሶአደሩ ግንዛቤ መስጠት ይገባል። ይህ መሆን ሲችል በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችን ይዞ መቅረብ ይቻላል። በመሆኑም ይህ ማህበር ምርቶቹን ለአውሮፓ ገበያ ለማቅረብ የዕውቅና ማረጋገጫ ካገኙ ህብረት ሥራ ማህበራት መካከል በሀገሪቱ ቀዳሚ ለመሆን ችሏል። በዚህም በጥቅል ጎመን፣ በፎሶሊያ እንዲሁም ቀይ ሽንኩርት ላይ የተሻለ የግብርና አሠራር ማረጋገጫ ሰርተፊኬት አግኝቷል። በቀጣይ የነበሩ ችግሮች በማቃለል በኩል ሊኖረው የሚችለው ሚናም የጎላ ነው የሚሆነው። ይህንንም በማስፋት ቁጥራቸው በዛ ያሉ አርሶአደሮች ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ እየሰራ ይገኛል። በሚቀጥለው በጀት ዓመትም ፎሶሊያን በስፋት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ዝግጅቱን አጠናቋል።

አቶ ከበደ ጋሻው ከኢታምኮ ኃላፊነቱ የተወሰነ አምራች ድርጅት ሥራ አስኪያጅ እንደሚሉት፤ በዓለም ገበያ ለመግባት አንዱ ወሳኝ ነገር የተሻለ የግብርና አሠራር ዕውቅና ማረጋገጫ ነው። በመሆኑም ይህን ባሟላ ሁኔታ ለመስራት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ይገልፃሉ። ነገር ግን ይላሉ አቶ ከበደ አምራቹ ኃይል የአውሮፓው ገበያ የሚፈልገው የዕውቅና ማረጋገጫ ቢያገኝም እንኳን የማጓጓዣ አገልግሎቱ ላይ የሚታዩትን ችግሮች ማቃለል ካልተቻለ ከዘርፉ የሚጠበቀውን ውጤት ማግኘት ያስቸግራል። በመሆኑም ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባው የመጓጓዣ ሁኔታው ምቹነትና ተደራሽነት ሊሆን ይገባል። ይህ መሆን ካልቻለ የአውሮፕላን ዋጋ እጅግ ከፍተኛ ነው። የመርከቡም ከጊዜ አንፃር ቆይታ ስለሚኖረው ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ይናገራሉ።

የዕውቅና ማረጋገጫ

በዕውቅና ማረጋገጫ ተቋም ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ ቃልኪዳን ውቤ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ባላት ሀብት የተሻለች ብትሆንም በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ መውጣት አልቻለ ችም። በመሆኑም ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ መቆየቷን ያስታውሳሉ። ባለሙያዋ እንደሚሉት በሀገሪቱ በተሻለ የግብርና አሠራር የዕውቅና ማረጋገጫ የተሰጣቸው 61 የግብርና አካላት ናቸው። ይህም ከኬንያ እጅጉን በመጠን ያነሰ ነው። ይህ የሆነበት ዋነኛው ምክንያት በሀገሪቱ ዘመናዊ አሠራር ጋር በተያያዘ በተፈጠረ የግንዛቤ ክፍተት ነው። መንግሥትም ሆነ አምራቾች ዘርፉ ለሀገሪቱ ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

እንደ ወይዘሮ ቃልኪዳን ገለፃ፤ ጎረቤት ሀገራት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ካስቻላቸው ምክንያቶች አንዱ የገበያውን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ምርት በዓይነት፣ በብዛትና በጥራት ማቅረብ በመቻላቸው ነው። በመሆኑም መንግሥት እና በዘርፉ የተሰማራው አምራች በጋራ በመሆን ችግሮችን በመለየትና መፍትሄ በማስቀመጥ ላይ መመካከር ይጠበቅባቸዋል። በተለይም የአውሮፓው ገበያ ምን ምርቶችን እንደሚፈልግ መለየትና ምርቱን በሚፈለገው ደረጃ ማቅረብ ይገባል።

ፍዮሪ ተወልደ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።