‹‹የተፋሰስ ልማት ዘላቂነት ላይ ችግር አለ›› - ዶክተር ጌቴ ዘለቀ የኢትዮጵያ ውሃና መሬት ሃብት ማዕከል ዳሬክተር ጀኔራል Featured

31 Aug 2017

የኢትዮጵያ ውሃና መሬት ሀብት ማዕከል የሦስት አስርት ዓመታት ተሞክሮ ቢኖረውም በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ሥራ ከጀመረ ሰባት ዓመት አስቆጥሯል፡፡ ማዕከሉ በሲውዘርላንድ መንግሥት ድጋፍ እየተደረገለት በጎርፍ ልቀት፣ በአፈር ክለት፣ እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ በአጠቃላይ በተፋሰስ ሥራና በጣና ላይ በተከሰተው እምቦጭ አረም ዙሪያ ከማዕከሉ ዳሬክተር ጀኔራል ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

አዲስ ዘመን፦ የአገሪቱ አጠቃላይ የተፋሰስ ልማት ዓለምን ከሚያሳስበው የመሬት መሸርሸርና መራቆት ጋር ሲነፃፀር ሥራው ምን ያህል አጥጋቢ ነው?
ዶክተር ጌቴ፦ በ 1966 ዓ.ም ከተከሰተው ድርቅ በኋላ በአብዛኛው የሰሜን እና የምሥራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች ለድርቁ መንስኤ የመሬት መራቆት ነው ተብሎ ስለሚታሰብ በተለያየ መልኩ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ሕብረተሰቡን በማንቀሳቀስ የተፋሰስ ሥራው ከተጀመረ ቆይቷል፡፡ ስለዚህ ሥራው ከ40 ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ ነገር ግን የተሠራው ሥራና አሁን በመሬት ላይ ያለው ውጤት አይገናኝም፡፡ መሬት ላይ ያለው ውጤት በጣም ትንሽ ነው፡፡
እኛ ዝርዝሩን አጥንተነዋል፡፡ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴርና በተዋረድ ያሉ ተቋማት በየዓመቱ ዕቅድ መያዝ እንጂ ትናንት ምን ተሠራ? የተሠራው የት ደረሰ? ነገስ ምን መሥራት አለብን? የሚለውን ብዙ ጊዜ ታሳቢ አያደርጉም፡፡ መሬት ላይ ያለው ምን ያህል ነው ተብሎም የሚዳሰስ አይመስለኝም፡፡ እኛ እነዚህን ጥያቄዎች አንስተን በመላው አገሪቱ ያለውን በሳተላይት ምስል በማስደገፍ ዝርዝር ጥናት አከናውነናል፡፡ በአገሪቱ እስከአሁን በአፈርና ውሃ ጥበቃ መሸፈን ከሚገባው አንጻር ተሸፍኖ የሚገኘው ስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም በእርከን መሸፈን ከሚገባው አንጻር በትንሹ ወደ 75 በመቶ ይቀረናል ማለት ነው፡፡ ይህ አኀዝ ተከልሎ መያዝ ያለበትን 11 ሚሊዮን ሄክታር እንዲሁም በተሻሻለ ግጦሽ መሸፈን የሚገባውን 14 ሚሊዮን ሄክታርና በተሻሻለ የማሳ አያያዝ መካተት ያለበትን 4 ሚሊዮን ሄክታር ሳይጨምር ነው፡፡
ይሄ ደግሞ ካለው የአፈርና የተፈጥሮ ሀብት መራቆት አንጻር እየተሠራ ያለው ሥራ በተለይ ከአራት ዓመት ወዲህ ጥሩ ቢሆንም ገና እጅግ ብዙ እንደሚቀረው ያሳያል፡፡ በጥራትም ብዙ ይቀረዋል፡፡ አብዛኛው ትኩረት የሚሰጠው ለቁጥሩ እንጂ ለጥራትና ለዘላቂነት አይደለም፡፡ ሪፖርት የሚደረገው ቁጥር ደግሞ በሚያሳዝን ሁኔታ አብዛኛው ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ዞን ባሉ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ ቁጥር መጨመር የተለመደ ነው።
የሚያሳዝነው ደግሞ የግምገማ መስፈርቱም ቁጥር ላይ መሆኑ ነው፡፡ ብዙ ቁጥር ሠራሁ ብሎ ሪፖርት የሚያቀርብ የወረዳ ባለስልጣን ወይም ከታች ያለ ባለሙያ ዕድገት ያገኛል፡፡ ጥራት ከተባለ ቁጥሩ አነስተኛ ስለሚሆን እሱን ብቻ ሪፖርት የሚያደርግ ሰው የውሸት ሪፖርት ከሚያቀርበው ጋር ሲነፃፀር የሚሰጠው ቦታ ዝቅተኛ ነው፡፡ እናም ከግምገማ ስርዓቱ ጀምሮ ሰው እንዲዋሽና ያልተሠራውን ተሠርቷል ብሎ ሪፖርት እንዲያደርግ የሚጋብዝ አካሄድ ነው ያለው፡፡ የእቅድ አወጣጥ ስርዓቱም አሳታፊ አይደለም፡፡ አገራችን እንድትለማ ካስፈለገ ይሄ አካሄድ ባስቸኳይ መስተካከል አለበት፡፡
በመሆኑም በእኛ እይታ አንደኛ የሚሠራው ሥራ በመጠንም ቢሆን ካለው የተፈጥሮ ሀብት መራቆት አኳያ አነስተኛ ነው፡፡ ሁለተኛ ከፍተኛ የሆነ የጥራት መጓደል አለ፡፡ ሦስተኛ ብዙ ሰው ላይ የግንዛቤ ችግር መኖሩ ይስተዋላል፡፡ ምክንያቱም የአፈርና ውሃ ጥበቃ እርከን ብቻ ከተሠራ ወደታች የሚሄደው ደለል ይቀራል፣ ምርታማነት ይጨምራል ብሎ ነው የሚያስበው፡፡ ነገር ግን ይሄ ስህተት ነው፡፡ እርከን ብቻውን ይሄን አይሠራም፤ ምናልባትም በረጅም ጊዜና የእርጥበት ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ካለሆነ በቀር፡፡ እርከን በሥነእፅዋት ከተጠናከረ፣ ፍራፍሬ ከተተከለበት፣ ገበሬውን ተጠቃሚ ካደረገው፣ የአፈር ለምነት ማሻሻያና የውሃ አያያዝ ሥራዎች አብረው ከተሠሩ ነው መሻሻል የሚችለው፡፡
አዲስ ዘመን፦ የሥራው ጥራት እንዴት ነው የሚለካው?
ዶክተር ጌቴ፦ ጥራት የሚለካው በመስፈርት ነው፡፡ ለምሳሌ እርከን የሚሠራ ከሆነ እንደ አካባቢው የዝናብ መጠን ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ የሚቆለለው አፈር ከፍታ፣ አፋሳሹ ያልተንጋደደ ወይም የተንጋደደ መሆኑና መጠኑ የመሳሰሉት መለኪያዎቹ ናቸው፡፡ ይሄን ጥራት ያልጠበቀ ሥራ ዘላቂ አይሆንም፡፡ ከተሠራ በኋላም ክትትልና ጥገና ይፈለጋል፡፡ በሥነ እፅዋትም መጠናከር ይገባዋል፡፡ አሁን ብዙ ቦታዎች ላይ የምናያቸው ትላልቅ ቦረቦሮች የተፈጠሩት ጥራታቸውን ባልጠበቁ የእርከን ሥራዎች ምክንያት ነው፡፡ ምክንቱም ሥራው ጥራቱን ካልጠበቀ ውሃ ያጠራቅማል፤ የተጠራቀመው ውሃ ሰብሮ ይሄዳል፤ ከዚያም ገደል ይፈጥራል፡፡ ብዙ ጊዜ ገዳዳ እርከን ሲሠራ ማፋሰሻው ይቀራል፡፡ ከዚያ ሌላ ቦታ ሄዶ ያበላሻል፡፡ እርከን በተለይም ዝናብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ሲሠራ ተጨማሪ ድጋፍ የሚያደርግ ሥራ ይፈልጋል፡፡ ከላይ የሚመጣውን ጎርፍ ማቆም መቻል ይጠይቃል፡፡ ይሄ የመተጋገዝ ሥራ ብዙ ጊዜ ይረሳል፡፡
አዲስ ዘመን፦ የተፋሰስ ልማት ላይ መቀዛቀዝ እንዳለ በተለያዩ መድረኮች ሲነገር ይደመጣል፤ የመስክ ምልከታችሁ ይሄን ያረጋግጣል? ምክንያቱስ ምን ይሆን?
ዶክተር ጌቴ፦ በነገራችን ላይ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት አብዛኛው የተፋሰስ ሥራ ሲሠራ የነበረው ከፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ ነው፡፡ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ በኋላ የአመራር አካሉን ከክልል አንስቶ እስከ ወረዳ ድረስ በኮማንድ ፖስት በማደራጀት ሕብረተሰቡን ማንቀሳቀስ ተችሏል፡፡ በዚህም ብዙ ሥራ ተከናውኗል፡፡ ነገር ግን አምና ተፈጥሮ ከነበረው የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ የአመራሩም የትኩረት አቅጣጫ ወደ ማረጋጋቱ ሄዷል፡፡ በመሆኑም ዘንድሮ በሁሉም ክልሎች ሊባል በሚችል መልኩ የነበረው እንቅስቃሴ ዝቅተኛ ነው፡፡ በአብዛኞቹ ክልሎች ሥራው ሲጀመር እንደነበረው አይደለም የተካሄደው፡፡
ሁለተኛ የተፋሰስ ልማት ውጤታማ እንዲሆን ልቅ ግጦሽ መቆም አለበት፡፡ ልቅ ግጦሽ ካለ ሥራው ዘላቂ አይሆንም፡፡ አሁን ግን ልቅ ግጦሽ ቆሞባቸው የነበሩ አካባቢዎች እንደገና ተመልሰው የወጣውን የማሕበረሰብ ሕግ በመሻር ከብቶቻቸውን እየለቀቁ ነው፡፡ አንዳንድ አርሶአደሮች ደግሞ የተሠራውን ሥራ አብረው የሚያርሱበትና የተተከሉ ችግኞች ውስጥ ከብቶች የሚውሉበት ሁኔታም አለ፡፡ በአጠቃላይ አሁን ላይ ለተፋሰስ ልማት የተሰጠው ትኩረት በጣም ተቀዛቅዟል፡፡
በእርግጥ ሰላም ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ ነገር ግን ችግር ሲፈጠር ሥራው መቆም የለበትም፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ ሕዝቡ እንዲያምንበት አድርጎ ሥራው የእኔ ነው፣ ለራሴ ሕይወት ይጠቅመኛል፣ ለልጅ ልጆቼ ማስተላለፍ አለብኝ የሚል እምነት እንዲያድርበት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ከሚሠራው ሥራም ተጠቃሚ እንዲሆን ብናደርገው የፀጥታ ችግር ኖረም አልኖረም ሥራዬ ብሎ ዓመት ጠብቆ እንዲያለማ ማድረግ ይቻላል፡፡ ነገር ግን በዚህ ዙሪያ በቂ ሥራ የተከናወነ አይመስለኝም፡፡
አዲስ ዘመን፦ ከምልከታችሁ በመነሳት ከፍተኛ ትኩረት ይፈልጋል የምትሉት የአገሪቱ አካባቢ የትኛው ነው?
ዶክተር ጌቴ፦ ሁሉም ቦታ ትኩረት ይፈልጋል፡፡ በብዙ ቦታዎች መታረስ የማይገባቸው ተዳፋቶች እየታረሱ ነው፡፡ ወንዝ ዳር ይታረሳል፡፡ በአማራም፣ በኦሮሚያም እንዲሁም በደቡብ ብሄር ብሄረሰብና ህዝቦች ክልልም ሰፊ ሥራ ይጠይቃል፡፡ ትግራይ ክልል የተሻለ ጥረት ቢኖርም እርሱም ቢሆን ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል፡፡ በተለይ ኦሮሚያ ክልል ግን ሰፊ ሥራ ይጠይቃል፡፡ በክልሉ ተዘዋውረን እንዳየነው ከሆለታ ጀምሮ አምቦ፣ ጉደር፣ ባኮ እስከ አርጆ ድረስ ያለው ቦታ ከአሁኑ ሥራ ካልተሠራበት በኋላ ላይ ጫናው ከፍተኛ ነው የሚሆነው፡፡ የዘማ፣ የሙገርና የጉደር ተፋሰሶችም ከፍተኛ ትኩረት ይፈልጋሉ፡፡ በአማራና በደቡብ ክልሎችም ቢሆን ብዙ የሚታረሱ ቦታዎች በጣም ተዳፋት የሆነ ስፍራ ነው፣ ከፍተኛ ሕዝብ ይኖርበታል፡፡ በአፋር በሶማሌ እና በቦረና ያለው የአርብቶ አደሩ አካባቢም በከፍተኛ ደረጃ የተራቆተ ነው፡፡ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ሥራ ይፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፦ እንደሚታወቀው የመሬት መራቆት ከደን ሽፋን መቀነስና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የሀይቆችን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥለው ይሆናል፤ ከዚህ አንፃር አሁን በተለይም በጣና ሀይቅ ላይ የተጋረጠው አደጋ ከዚህ ጋር ማያያዝ ይቻላል? ችግሩስ ከዚህ ጋር ይገናኛል?
ዶክተር ጌቴ፦ ጣና ሁለት ችግር ነው ያለበት፡፡ አንደኛውና የቆየው ችግር ጣና ከፍተኛ የደለል ክምችት የሚገባበት ሀይቅ መሆኑ ነው፡፡ አራት ትላልቅ ወንዞች አሉ፡፡ አንዱ ግልገል አባይ ሲሆን፤ ከጮቄ ተራራ ተነስቶ ሰፊ ቦታ ይዞ የሚሄድ ነው፤ ይሄ ገባር ክረምት ላይ ውሃ ሳይሆን ጭቃ ይዞ ነው የሚገባው፡፡ ከደቡብ ጎንደር ደግሞ ጉማራ እና ርብ ይገባሉ፡፡ እነዚህም ከጉና ጀምሮ አፈሩን እያጠቡ ወደ ሐይቁ ይገባሉ፡፡ አራተኛው ወንዝ መገጭ ሲሆን፤ ከዳባት ጀምሮ ያለውን ሰብስቦ ጣና ነው የሚከተው፡፡ በመሆኑም ጣና ላይ ያለው ትልቅ ችግር ደለል ነው፡፡ የደለል ችግር ጣናን ብቻ ሳይሆን በስምጥ ሸለቆ የሚገኙ ሀይቆችም ችግር ነው፡፡ የሃሮማያን ሀይቅ ማስታወስ በቂ ነው፡፡ ላንጋኖ መልኩ ቀይ ነው፡፡ ይሄም የደለል ውጤት ነው፡፡
ጣና በጣም ትልቅ ሀይቅ ነው፡፡ በክረምት የሀይቁ ቀለም ተቀይሮ ቀይ ይሆናል፡፡ ይሄም ከፍተኛ የሆነ ደለል እንደሚገባበት ያሳያል፡፡ በተጨማሪም ጨረጨራ ላይ ያለው የአባይ ፍሰት መቆጣጠሪያ የጣና ገባር ወንዞች ከፍተኛ ደለል ይዘው በሚገቡበት ወቅት(በተለይም ሰኔና ሐምሌ)መዘጋቱ ከፍተኛ ደለል ሀይቁ ውስጥ እንዲቀር ያደርጋል፡፡ በዚህም ምክንያት በየዓመቱ የሀይቁ ጥልቀት እየቀነሰ ነው፡፡ ሁለተኛውና አዲሱ ችግር እምቦጭ አረም ነው፡፡ በነገራችን ላይ ለእምቦጩ መስፋፋት ደግሞ በየዓመቱ የሚገባው ደለል ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ሁለቱ ችግሮች የተያያዙ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፦ ከሣይንሳዊ መፍት ሔዎች አንፃር እንቦጭን ለማጥፋት እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ በቂ ነው?
ዶክተር ጌቴ፦ የአማራ ክልል ብዙ ጥረት እንደሚያደርግ አውቃለሁ፡፡ አሁንም እያደረገ ነው፡፡ በአካባቢው ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችም እንዲሁ የሚቻላቸውን ለማድረግ እየሞከሩ ነው፡፡ ነገር ግን ይሄ ጉዳይ የአንድ ክልል ጉዳይ አይደለም፡፡ ብሔራዊ አጀንዳ መሆን መቻል አለበት፡፡ ጊዜ የሚሰጠውም ጉዳይ አይደለም፡፡ በብሔራዊ ደረጃ በጀት ተመድቦ፤ በክልል ደረጃ ይህን ሥራ የሚመራው ፅሕፈት ቤት ተቋቁሞ የሚመለከታቸውን አካላት እያስተባበረ ባጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ሊገባ ይገባል፡፡ ለመፍትሔው የተለያዩ አማራጮች አሉ፡፡ በመሳሪያም ሆነ በሕዝብ እንቅስቃሴ ተደርጎ ቶሎ ወደ ሥራ ካልተገባ በስተቀር የሚያስከትለው አደጋ ከባድ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፦ እንደ ባለሙያ የምትሰጧቸውን ምክረ ሃሳቦች ተከትሎ እስካሁን እየተወሰዱ ያሉ ተግባራዊ ምላሾች አርኪ ናቸው?
ዶክተር ጌቴ፦ እኔ ገና ብዙ ይቀረዋል ባይ ነኝ፡፡ የተለያዩ ሙከራዎች አሉ፤ ነገር ግን ሙከራዎችን ይዘን ወደተግባር መግባት አለብን፡፡ ወደ ተግባር ለመግባት ደግሞ ራሱን የቻለ በጀት ይጠይቃል፡፡ ሥራውን የሚያንቀሳቅስ ኃይል ያስፈልገዋል፡፡ ሥራውም በብሔራዊ ደረጃ በቂ ክትትል ይፈልጋል፡፡ እስካሁን የተደረገው ጥረት የሚበረታታ ቢሆንም የሚያረካ አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፦ እንደአጠቃላይ ወጥ ባልሆነ መልኩ ያዝ ለቀቅ የሚደረገውን የተፋሰስ ልማት ዘላቂነት ያለው ሥራ ለማድረግ የሚሰጡት ምክር ምንድነው?
ዶክተር ጌቴ፦ በነገራችን ላይ እስከአሁን ተተክሏል የተባለው ቢሰላ የአገሪቱን ሁለትና ሦስት እጥፍ አጠቃላይ ቆዳ ይሸፍን ነበር፡፡ በየዓመቱ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ችግኝ እያፈላን እንተክላለን፤ ነገር ግን ትልቁ ችግር የሚመስለኝ ለተከልነው ችግኝ እንክብካቤ አይደረግም፡፡ ባለቤት የለውም፡፡ በዘመቻ ከተተከለ በኋላ ዞሮ የሚያየው የለም፡፡ አንዱ ችግር ይሄ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የሚቀጥ ለውን ዓመት ዕቅድ ስናቅድ የመጀመሪያው ሥራ መሆን ያለበት አምና የተከልነው ችግኝ የት ደረሰ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ የተተከለበትን ዓላማ እየሠራ ነው ወይ? ከጠፋስ ለምን ጠፋ? ለምን ደረቀ? ምን ማድረግ አለብን? ከሚለው መጀመር አለበት፡፡ እኛ አገር ይሄ አይደረግም፡፡
በየዓመቱ የሚሠራው እርከንም ዕጣ ፈንታ ከዚሁ የተለየ አይደለም፡፡ የዚህን ዓመት ዕቅድ ማቀድ እንጂ ወደ ኋላ መገምገም የለም፡፡ ይሄን በተመለከተ ብዙ ጊዜ ጮኸናል ግን ለውጥ የለም፡፡ በመሆኑም ከዘላቂ ክትትል ባሻገር ሥራዎች ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲከናወኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የእቅድ ክንውን ግምገማው ቁጥርን ብቻ ሳይሆን ጥራትንና ዘላቂነትን ማካተት ይኖርበታል፡፡ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ይገባል፡፡ ምርታማነትን በመሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማረጋገጥም ይጠበቃል፡፡
ከዚህ አንጻር ያለውን ክፍተት ግምት ውስጥ በማስገባት የቢሮና የመስክ ባለሙያዎች የሚጠቀሙበት የዘላቂነት መመሪያ ማዕከላችን በቅርቡ አሳትሟል፡፡ ይኽን መመሪያ ባግባቡ መጠቀም ከተቻለ ከዘላቂነትና ከጥራት ጋር ተያይዞ አሁን እየታየ ያለውን ክፍተት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሻሽለው ከፍተኛ እምነት አለኝ፡፡ ነገር ግን በመመሪያው አጠቃቅም ዙሪያ በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴርና በክልል ከላይ እስከታች ያሉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ስልጠና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ይህንንም ጉዳይ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴርና ትኩረት ሊሰጠውና ስልጠናው ባስቸኳይ እንዲሰጥ ማድረግ ይገባዋል እላለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፦ ለሰጡኝ ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ!
ዶክተር ጌቴ፦ አመሰግናለሁ !

ብሩክ በርሄ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።