‹‹ የከተማዋ የትራፊክ እንቅስቃሴ በችግሮች የተሞላ ቢሆንም ተስፋ አስቆራጭ አይደለም››- አቶ ጂሬኛ ሂርጳ የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር

10 Oct 2017

የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱ የማይታበል ሃቅ ነው፡፡ በተለይም የከተማዋን ዕድገት ተከትሎ የተሽከርካሪዎችና የህዝብ ቁጥር መጨመር ለትራፊክ እንቅስቃሴው ተጨማሪ ራስ ምታት ሆኗል፡፡ ታዲያ ይህ የትራፊክ እንቅስቃሴ ችግር በዋናነት በሥራ መግቢያና መውጪያ ሰዓት ላይ ያይላል፡፡

ለዚህም ይመስላል በከተማዋ የትራንስፖርት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ራሱን ችሎ በአዋጅ የተቋቋመው፡፡ የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የተቋቋመበት ዋነኛው አላማውም በከተማዋ ሰላማዊ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖርና የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ነው፡፡

አሁን ያለው የከተማዋ የትራፊክ ፍሰት ምን እንደሚመስል፣ ለእንቅስቃሴው እንቅፋት ናቸው ተብለው በተለዩና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ እንዲሁም በቀጣይ በኤጀንሲው በኩል ስለታቀዱ ሥራዎች ከኤጀንሲው ምክትል ዳይሬክተር አቶ ጂሬኛ ሂርጳ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የከተማዋ የትራንስፖርት እንቅስቃሴና የትራፊክ ፍሰት እንዴት ይገለፃል?

አቶ ጂሬኛ፡- የከተማዋ የትራፊክ ፍሰት በብዙ ችግሮች የተሞላ ነው፡፡ ያን ያህል ግን ተስፋ አስቆራጭም አይደለም፡፡ በከተማዋ የትራፊክ ሥርዓት ባለመኖሩ በቀጣይ የሚከሰተውን ነገር ለመተንበይ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ችግሩንም ለመቅረፍ የመንገድ ህግ መኖር አለበት፡፡ ህብረተሰቡም በእቅዱ መንቀሳቀስ የሚያስችለው የትራፊክ ሥርዓትና ፍሰት እንዲኖር እየተሰራ ነው፡፡ የመንገዶች ሁኔታም ሥርዓት እንዲይዙ ይደረጋል፡፡ ቀደም ሲል ዋነኛ ትኩረታችን የነበረው መንገድ ግንባታ ላይ ብቻ በመሆኑ የትራፊክ ማኔጅመንት የተረሳ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በተለይም በከተማዋ መንገዶችን በብዛት መገንባትና ማስፋት ሲጀመር የትራንስፖርት እንቅስቃሴው ችግር እየጎላ መጥቷል፡፡ ለትራፊክ እንቅስቃሴው አዋኪ የሆኑ ነገሮችን ማጥፋት፣በደንብ ማስከበርና በቴክኖሎጂ የታገዘና ትክክለኛ የመንገድ ህጎች እንዲኖሩና ህጎቹም እንዲከበሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የመንገድ ተጠቃሚውም ብዙ አማራጭ እንዲኖሩትና ግራ የሚያጋባ የመንገድ ሥርዓት እንዳይኖር በማድረግ እንቅስቃሴውም ሥርዓት የያዘ እንዲሆን ማድረግ የትራፊክ ማኔጅመንት ሥራ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅትም እየተስተዋለ ያለው የትራፊክ እንቅስቃሴ ችግር ቀደም ሲል የተከማቸ ነው፡፡በመሆኑም ዘለቄታዊ መፍትሔን ለማምጣት የትራፊክ ማኔጅመነት ኤጀንሲ ተቋቁሟል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኤጀንሲው ከተቋቋመ በኋላ የተሰሩ ዋና ዋና ተግባራት ምንድን ናቸው?

አቶ ጂሬኛ፡- ኤጀንሲው ከተቋቋመ ሁለት ዓመት ቢሆነውም በከተማዋ ከትራፊክ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የሚታዩ አንገብጋቢ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት አድርጓል፡፡ ህብረተሰቡ ረጅም ሰዓታትን በጉዞ የሚቆምባቸውን ማጋጠሚያ ቦታዎችንና አደባባዮችን የማሻሻል ሥራዎች አከናውኗል፡፡ ለአብነትም ጀሞ ሚካኤል፣ ቦሌሚካኤል፣ ኮልፌ18ማዞሪያ፣ኢምፔሪያልና ጀርመን አደባባይ በቀለበት መንገድ መጋጠሚያ ላይ የሚገኙና ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት የሚያስተናግዱ በመሆናቸው የማሻሻልና ተሽከርካሪዎች በአደባባይ እንዲስተናግዱ የማድረግ ሥራ ተከናውኗል፡፡

በቄራ እና በሰዓሊተ ምህረት አካባቢ ተንቀሳቃሽ የትራፊክ መብራቶችን በመትከል የትራፊክ ፍሰቱ የተሻለ እንዲሆን ከማድረግም ባሻገር በእግረኞች ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ መገናኛ፣ሜክሲኮና ስታዲየም አካባቢዎች ላይ የፕላስቲክ አጥሮች በማጠር እግረኞች ወደ ተሽከርካሪ መንገድ እንዳይገቡ የማድረግ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ይህ ሁኔታም የመንገድ አጠቃቀሙ በሥርዓት እንዲመራ ረድቷል፡፡

የትራፊክ እንቅስቃሴው የበለጠ የተሳለጠ እንዲሆን በመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) ልማት ላይ ባለሀብቶችን በማሳተፍ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ በሌላ በኩልም ደንብ የማስከበር ሥርዓቱን በማጠናከር እግረኞችም ሆኑ አሽከርካሪዎች የመንገድ ህግ አክባሪ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ የትራፊክ ፍሰቱን የሚያጨናንቁ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎችም በአምስቱም የከተማዋ መውጫና መግቢያዎች ላይ ከጠዋት 1 ሰዓት እስከ 3 ሰዓትና ከሰዓት ከ10 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ወደ መሀል ከተማ እንዳይገቡ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የትራፊክ እንቅስቃሴውን አዋኪ ከሆኑ ነገሮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱት የትኞቹ ናቸው?

አቶ ጂሬኛ፡- ለትራፊክ እንቅስቃሴው ጤናማ አለመሆን በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከእነዚህም መካከል ህብረተሰቡ ለመንገዶች ያለው ገንዛቤ አናሳ መሆን፣ መንገዶችን ለተለያዩ አላስፈላጊ ነገሮች መጠቀም ለምሳሌ ለህንጻ ግንባታ የሚሆኑ አሸዋና ጠጠር ማፍሰሻ ማድረግ፣ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖር፣ የእግረኛ መንገዶች ግንባታ ያለመጠናቀቅ በእግረኛ መንገዶች ላይ የሚካሄዱ የስልክና የመብራት ዝርጋታዎች በተናበበ መልኩ አለመሄድ፣ የመንገድ ላይ ህገ ወጥ ንግዶችና የመንገድ ዳር የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች በደንብ ያለመሰራት በተለይም በክረምት ወቅት መንገዶች በውሃ እንዲሞሉ በማድረግ የትራፊክ ፍሰቱን ያውካሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ችግሮቹን ለመፍታት ምን እየተሰራ ነው ?

አቶ ጂሬኛ፡- የትራፊክ ፍሰትን ለማሻሻል መንገዱና የመንገድ ተጠቃሚው አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡ የትራፊክ ማኔጅመንትን ከባድ የሚያደርገው ለችግሩ አስተዋጽኦ የሚያደርጉት ምክንያቶች ብዙ መሆናቸው ነው፡፡ በመሆኑም የእግረኛ መንገድ ሲዘረጋ የኤጀንሲው ደንብ ማስከበር አካል ከመንገዶች ባለስልጣን ደንብ ማስከበር ጋር በመሆን ቦታዎችን በመለየት እንዲነሱ ያደርጋል፡፡ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችን ለመገንባት ባለሀብቶችን ተሳታፊ በማድረግ ተጨማሪ ጥናቶች እየተካሄዱ ናቸው፡፡ ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም በመቀናጀት እየተሰራ ይገኛል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የትኞቹ የከተማዋ ክፍሎች በከፍተኛ ደረጃ የትራፊክ መጨናነቅ ይስተዋልባቸ ዋል? ምንስ እየተሰራ ነው?

አቶ ጂሬኛ፡- በከተማዋ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ የነበረበት በርካታ ተሽከርካሪዎችን በሚያስተናግዱ የቀለበት መንገዶችና ማጋጠሚያዎች ላይ ነው፡፡ በቀለበት መንገዱ ላይ ያሉ አንዳንድ አደባባዮች ተሽከርካሪዎችን ለማስተናገድ ያላቸው አቅም አነስተኛ መሆን ለትራፊክ መጨናነቁ ተጨማሪ መንስኤ ነው፡፡

በአጠቃላይም በኤጀንሲው በተጠና ጥናት 27 የሚሆኑ መጋጠሚያዎች ላይ ጥናት የተደረገ ሲሆን፣ በተጨማሪም የትራፊክ ፍሰት ቆጠራና የፍጥነት ወሰን ቁጥጥር ይካሄዳል፡፡ በዚህም የትራፊክ አደጋ የሚበዛባቸው ቦታዎች ይለያሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በሥራ መግቢያና መውጪያ ሰዓት ላይ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ይከሰታል፡፡ የችግሩ መንስኤ ምንድን ነው? መቼስ ነው የሚፈታው?

አቶ ጂሬኛ፡- ይህ ጉዳይ ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃር ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ወደ ከተማዋ በየጊዜው እየፈለሰ የሚመጣው ህዝብ ቁጥር መጨመርም የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡ በመሆኑም ይህ ጉዳይ እንደአገር ትልቅ አጀንዳ ሆኖ መሰራት አለበት፡፡ ምክንያቱም ችግሩንም ጥቅሙንም ያልተማከለ ከማድረግም ባሻገር ለአሰራርም ቀላል ይሆናል፡፡ ኤጀንሲው በዋናነትም በትራፊክ እንቅስቃሴው ችግር ምክንያት የሚመጡ ተፅዕኖዎችን ከመቀነስ አኳያ ይሰራል፡፡

ሁሉም የመንግሥት መስሪያ ቤቶችና ትምህርት ቤቶች የሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት እኩል መሆን ለትራፊክ መጨናነቁ የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ በቀጣይ በግልና በመንግሥት ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በመንግሥት መስሪያ ቤቶች የመግቢያና መውጫ ሰዓት በመለያየት ችግሩን መፍታት ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- አደባባዮችን በመብራት የመቀየር ሥራዎች ለትራፊክ እንቅስቃሴው ምን አስተዋፅኦ አበረከተ?

አቶ ጂሬኛ፡- በአውስትራሊያ የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂዋ ውስጥ በርካታ አደባባዮችን በትራፊክ መብራት እንዲቀየሩ በማድረግ ውጤታማ ሆናለች፡፡ በአዲስ አበባ ከ80 በላይ የሚሆኑ አደባባዮች ይገኛሉ፡፡አደባባዮች ያልተገባ ቦታ ሲገነቡ ወይም ደግሞ ከአቅማቸው በላይ ተሽከርካሪዎችን ለማስተናገድ ሲቸገሩና በትራፊክ እንቅስቃሴው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ በመሆኑም አደባባዮቹ በትራፊክ መብራት እንዲቀየሩ ይደረጋል፡፡ በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች የተገነቡ አደባባዮች በትክክል ዲዛይን ተደርገው ባለመሰራታቸው ችግር ሲፈጥሩ ይስተዋላል፡፡ በመሆ ኑም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ተገንብተው የነበሩ አደባባዮች ፈርሰው በትራፊክ መብራት መተካታቸው ጥሩ ለውጥ አምጥቷል፡፡ የትራፊክ ማኔጅመንት ሥራ ተለዋዋጭ ከመሆኑ አንፃር በየጊዜው የትራፊክ እንቅስቃሴውን ለማሻሻል የተለያዩ ዘዴዎችን በመቀየስ ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል፡፡ አሁን የመጣውን የተሻለ የትራፊክ እንቅስቃሴ ለውጥ በቀጣይም ለማስቀጠል አደባባዮችን በማፍረስ በመብራት የመተካት እቅዶች ተይዘዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ ከኤጀንሲው ምን ይጠበቃል?

አቶ ጂሬኛ፡- የትራፊክ እንቅስቃሴው ሥርዓት እንዲኖረው በቀጣይ በከተማዋ ወደ 31 የሚሆኑ የትራፊክ መብራቶች ይተከላሉ፡፡ ይህም ተግባራዊ ሲሆን ለትራፊክ እንቅስቃሴው አስቸጋሪ የሆኑ የመንገድ መጋጠሚያዎች እየቀነሱ ይመጣሉ፡፡ በተለይም ዋና መንገዶች ትክክለኛ አገልግሎታቸውን እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡ የትራፊክ ማኔጅመንት ማዕከልም ይቋቋማል፡፡ ፕሮጀክቱም በዋናነት ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም በከተማዋ ወደ 135 የሚጠጉ የመንገድ መጋጠሚያዎ ችን በማጥናት ማሻሻያ ይደረጋል፡፡ አንድ ቦታ በመሆን የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት ለማየት የሚያስችል ቴክኖሎጂም በእቅድ ተይዟል፡፡ በአጠቃላይ የከተማዋን የትራፊክ ሥርዓት የማዘመን ሥራ ይሰራል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?

አቶ ጂሬኛ፡- የትራፊክ ማኔጅመንት ሥራ በጣም ውስብስብ ከመሆኑ አኳያ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ የየራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል፡፡ መንገድ ተጠቃሚውም ትክክለኛ የመንገድ ህጎችንና ደንቦችን በማክበር መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡ የተለያዩ ተቋማት የመገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ ትክክለኛ የመንገድ አጠቃቀም ሥርዓትን ከማስተማር አንፃር ቅንጅታዊ ሥራ መስራት ይጠበቅባቸ ዋል፡ ይህ ከሆነ በከተማዋ የትራፊክ ፍሰቱ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ኤጀንሲው የትራፊክ ችግሩን ሙሉ በሙሉ ይፈታዋል ማለት አይደለም፡፡ በመሆኑም በጋራ መስራት የግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በትራፊክ ማኔጅመንት የሚታዩ የተወሰኑ ለውጦች በመኖራቸው በቀጣይ ዓመታት የተሻሉ ለውጦች ይኖራሉ፡፡ አዲስ አበባም በአምስት ዓመታት ውስጥ ዘመናዊ የትራፊክ ፍሰት ሥርዓት እንደሚኖራት ይጠበቃል፡፡

 

አስናቀ ፀጋዬ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።