የባህል ማዕከሉን የገቢ ምንጭ ለማድረግ

12 Oct 2017

ባህል የማንነት መለያ ብቻ ሳይሆን የገቢ ምንጭም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ብዙ አገራት ከቱሪዝሙ ዘርፍ ዳጎስ ያለ ገቢ ያገኛል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የበርካታ ብሔር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባለቤት የሆኑ አገራት ደግሞ ባህል ከዚህም በላይ ከፍተኛ የገቢ ማግኛ ዘዴ መሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ በአገሪቱ ውስጥ ተደጋግሞ የሚነሳ ክፍተት አለ፤ ይኸውም ባህልን በሚጠበቀው ደረጃ የገቢ ምንጭ ማድረግ ያለመቻሉ፡፡ የድንቃድንቅ ቦታዎችና ተፈጥሮዎች፣ የውብ ባህሎች ባለቤት በማለት ደጋግሞ አገሪቱ ያላትን ሀብት በአንደበት ከመግለጽ ውጪ የቱሪዝም ምንጭ በማድረግ ከዘርፉ ስለሚገኘው ገቢ እምብዛም አልተሰራበትም፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል አዲስ ሕንጻ አስገንብቶ በርካታ የሥልጠናና የምርምር ክፍሎችን፣ የዕደ ጥበብ ማምረቻ ክፍሎችን እንዲሁም የገበያና ሽያጭ ማዕከላትን በማካተት በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ባህሎችን የገቢ ምንጭ ለማድረግ አስቧል፡፡ ሕንጻው ከመገንባቱ በፊት ግን በማዕከሉ ውስጥ የሚካተቱ ነገሮች ሁሉ የገቢ ምንጭ መሆን እንዲችሉና በአገሪቱ ውስጥም ያሉ ባህሎች በዓለም ይታወቁ ዘንድ ምን ይደረግ በሚል ከባለድርሻ አካላትና ከግንባታ ባለሙያዎች ጋር በዚህ ሳምንት የምክክር መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ አርክቴክት ብሩክ በቀለ ለመነሻ ሀሳብ የሚሆን ዲዛይን አሳይተዋል፡፡ አርክቴክቱ እንደሚሉትም፤ ዲዛይኑ ለውይይት መነሻነት የቀረበ በመሆኑ በሚነሱ ሀሳቦች ብዙ ማሻሻያ ስለሚደረግበት ሊለዋወጥ ይችላል። መሰራት ያለበት ሕንጻ በመድረኩ ላይ የቀረበውን አይነትም ላይሆን ይችላል፡፡ ለመነሻ በቀረበው ዲዛይን መሰረት የሚሰራው ሕንጻ በ34 ሺ ስኩዌር ካሬ ሜትር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን፣ ስድስት ፎቆች ይኖሩታል፡፡ የማዕከሉ አዳራሽ ሦስት ሺ 500 ሰዎችን እንዲይዝ ታስቧል፡፡ በውስጡም የምርምር፣ የቤተ መጻሕፍት፣ የሰነድ እና ሌሎች ክፍሎች ይኖሩታል፡፡

የመነሻውን ዲዛይን ካዩ በኋላም ብዙ ሰዎች የየራሳቸውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የጉራጌ ዞን ልማትና ባህል ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ጎይተ እንደሚናገሩት፤ የባህል ማዕከሉ የውጭ አገራትን አሰራር መያዝ የለበትም፡፡ የባህል ማዕከል የተባለው የአገሪቱን ማንነት ለማሳየት ነው፡፡ በዘመናዊው አሰራር የሚሰራ ከሆነ ግን ባህሉን የሚያሳጣ ነው የሚሆነው፡፡ ይህ እንዳይሆን ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል፡፡

አቶ ተስፋዬ «በከተማዋ ውስጥ እንደሚታዩት ፎቆች አይነት ከሆነ የባህል ማዕከል መሆኑ በምን ያስታውቃልሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ እንኳን የሕንጻው ቅርጽ ቀርቶ በግቢው ውስጥ የሚገኙ ተክሎችም የአገር ውስጥ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ በግቢው ውስጥ ያሉ መንገዶች ከአስፓልት ይልቅ የድንጋይ ንጣፍ ቢሆኑ ይመረጣል፡፡ በእንዲህ አይነት ሁኔታ የሚሰራ ከሆነ በዓለምአቀፍ ደረጃ የራሱን አሻራ ማሳረፍ እንደሚችል ይናገራሉ። ስለዚህም በውስጥ የሚታዩ ነገሮች በሙሉ ኢትዮጵያዊነትን የሚሰብኩ ሆነው በዓለም እንዲታወቁ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ከኦሮሞ ባህል ማዕከል የመጡት ዶክተር ዳኛቸው ገረመው በበኩላቸው፤ ከስያሜው ጀምሮ አይስማሙም፡፡ ስያሜው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል ከመባል ይልቅ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ የባህል ማዕከል መባል እንዳለበት ነው የሚናገሩት፡፡ ለዚህ ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡ ብሔራዊ የሚባለው ለክልል መንግሥታት በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡

ዶክተሩ እንደሚሉት፤ በማዕከሉ ውስጥ የሚካተቱ ነገሮችን በተመለከተ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቂ ምክክር መደረግ አለበት፡፡ የሚገነባው የባህል ማዕከል የፌዴራል ስለሆነ በክልሎች ከሚኖረው የተለየ መሆን አለበት፡፡ ክልሎች የየራሳቸው የባህል ማዕከላት አሏቸው፡፡ በዚህኛው ማዕከል እነዚያን መድገም ከሆነ አዲስ ነገር አይኖረውም፡፡ የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህልና ወግ ወደ ፌዴራል ማዕከልነት ሲመጣ እንዴት መሆን አለበት የሚለው መጠናት ይኖርበታል፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ ያለው ባህል ሲመጣ በክልሉ ያለውን ማዕከል መድገም ሳይሆን ወደ ፌዴራል ሲመጣ እንዴት መሆን እንዳለበት ተጠንቶ ነው መሆን የሚገባው፡፡

በሌላ በኩል ሕንጻው አገራዊ መልክ መያዝ እንዳለበት ነው አቶ ዳኛቸው የሚናገሩት፡፡ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የምትታወቅበት የራሷ የሕንጻ አሰራር ጥበብ ያላት አገር ናት፡፡ ይህ ደግሞ የባህል ማዕከል ነው፡፡ አንድ ከውጭ የመጣ ጎብኚ አገሩ ላይ የሚያየውን አሰራር ከሆነ እዚህም የሚያገኘው ምንም የተለየ ነገር አይመለከተምና ጎበኘሁ፤ ተረዳሁ ሊል አይችልም። ይህም ከንቱ ድካም ይሆንበታል፡፡ ወደሌላ አገር የሚሄደው የተለየ ነገር ለማየት እንጂ አገሩ ያለውን ለመድገም አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ ሌሎች ጎብኚዎች ደግመው እንዳይመጡ እንቅፋት ይሆናል። የባህል ምግብ ሥልጠናም መሰጠት እንዳለበት የሚጠቁሙት ዶክተሩ፤ አንድ የውጭ አገር ዜጋ ሲመጣ አገሩ የሰለቸው ምግብ የሚቀርብለት ከሆነ ራሱን እንደ ጎብኚ ሊያይ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያን ለማየት ከመጣ ማሳየት የሚገባው የኢትዮጵያን ምግብ ነው ይላሉ፡፡

ከአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በመድረኩ የተገኙት አቶ ደርበው መኮንን «ባህል ማዕከሉ ከክልሎች የተለየ መሆን አለበት» በሚለው በዶክተር ዳኛቸው ሀሳብ አይስማሙም፡፡ ክልሎች የየራሳቸው ባህል ማዕከል ቢኖራቸውም በዋናነት ደግሞ በፌዴራል ደረጃ አንድ ቦታ መገኘት አለበት፡፡ አማራ ክልል ውስጥ ያለውን ባህል ማዕከል የሚያየው በዚያው አካባቢ ያለ ብቻ ነው፡፡ በማዕከል ከሆነ ግን ከአንድ ቦታ የሁሉንም ለማየት ያስችላል፡፡

የሙዚቃ ባለሙያው ዳዊት ይፍሩ ባነሳው አስተያየት፤ አሁን ዲዛይኑን በአኒሜሽን ማሳየት ቀላል ነው፡፡ መድረክ ላይ የተወሩ ነገሮችን ወደተግባር መቀየር ግን ከባድ ነውና ትልቅ ትኩረት ይፈልጋል፡፡ የታሰበው ሁሉ ወደተግባር የሚገባ ከሆነ የባህል የሙዚቃ መሳሪያዎች፣ ባህላዊ የእንጨት ሥራዎችና ብዙ የዕደ ጥበብ ሥራዎች የገቢ ምንጭ መሆን ይችላሉ፡፡ የዕደ ጥበብ ሙያ ያላቸው ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል፡፡ በተለይም በማዕከሉ ውስጥ የገበያና የሽያጭ ክፍል መኖራቸው ማዕከሉ የአገሪቱን ባህሎች ማስተዋወቅ ብቻ ሳይሆን የገቢ ምንጭ ለማድረግ ያስችላል፡፡

አርክቴክት ንዋይ ሰሙንጉሥ በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ አንድ ሕንጻ ሲሰራ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ብሔር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን የአሰራር ባህል ሁሉ ሊይዝ አይችልም፡፡ ሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የየራሳቸው የአሰራር ጥበብ አላቸው፡፡ ያንን ሁሉ በአንድ ሕንጻ ላይ ማሳየት አይቻልም፡፡ የአገሪቱ ብሔር፣ ብሄረሰቦች የአሰራር ጥበብና ባህል የሚታየው በውስጡ በሚኖሩ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ ነው። በውስጡ ብዙ የንግድ ማዕከላት፣ ሱቆች በተጨማሪም የአውደ ርዕይ ማቅረቢያዎች ስለሚኖሩ በእነዚህ ውስጥ የብሄር ብሄረሰቦችን የአሰራር ጥበብ ማሳየት ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እልፍነሽ ኃይሌ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ይህን አዲሱን የባህል ማዕከል ለመገንባት ያስፈለገበት ምክንያት አገሪቱ የብዝሀ ባህል ባለቤት እንደመሆኗ እነዚህን ባህሎች አንድ ቦታ የሚገኙበት ማዕከል በማዘጋጀት የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ነው፡፡ አገሪቱ እስካሁን ከባህል በሚገኘው ገቢ ተጠቃሚ ባለመሆኗ ይህን እውን ለማድረግም ያግዛል፡፡ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያትም የባህል ሀብቱ የአገሪቱ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ ሐሳባቸውን እንዲያካፍሉና የየራሳቸውን ጠቃሚ ሐሳብ እንዲሰነዝረ ታስቦ ነው፡፡ ከውይይቱ የሚገኙ ገንቢ አስተያየቶችን ለማካተት ይሞከራል፡፡

ሕንጻው የሚሰራው አሁን ባለበት ግቢ ውስጥ ሲሆን፣ በውስጡ ያሉ ተክሎች እንደማይነኩ ነው ዋና ዳይሬክተሯ የተናገሩት፡፡ ሌሎች አዳዲስ አገር በቀል ዛፎችና አበቦችም ይተከላሉ፡፡ በውስጡ ብዙ ክፍሎች ስለሚኖሩ ሥራው ትልቅ ትኩረት የሚፈልግ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

ለግንባታው የሚያስፈልገውን የበጀት መጠን አሁን እርግጠኛ መሆን ባይቻልም ሰባት ሚሊዮን ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡ በጀቱ በመንግስት እየተጠና ያለ መሆኑንም ነው የሚያስረዱት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በድጋፍ የሚገኝ ገንዘብም ሊኖር ይችላል የሚል እምነት አላቸው፤ በተለይም የዕደ ጥበብ ማሰልጠኛ ማዕከል ከስፔን በተገኘ ድጋፍ የሚሰራ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ማዕከሉ ተጠናቆ አገልግሎት ሲጀምር ብዙ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ገልጸዋል፡፡

 

ዋለልኝ አየለ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።