የወርቅ ግብይት ማበረታቻ

05 Dec 2017

 

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከረጅም ዓመታት ጀምሮ የወርቅ ግዥ በማከናወን ወደ ውጭ አጓጉዞና አስነጥሮ በአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ሂሳብ ገቢ ሲያደርግ ቆይቷል። ባንኩ በአገር ደረጃ ሥራውን በማሻሻል የወርቅ ግብይት ህጋዊ በሆነ አሰራር እንዲከናወን የተለያዩ ፖሊሲዎችን በመንደፍ ተግባራዊ ሲያደርግ መቆየቱን ባንኩ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

1. በባህላዊ መንገድ በወርቅ አምራቾች ተመርቶ በማእከል ደረጃ ለባንኩ ሲቀርብ የነበረው ወርቅ የአቅራቢዎች ቁጥር በመጨመሩ እንዲሁም የወርቅ ግብይቱን ሥራ በአንድ የግዥ ማእከል ብቻ በማከናወን የአቅራቢዎችን ፍላጎት ማርካት ባለመቻሉ በክልሎች የግዥ ማእከላት ተከፍተው ግብይቱ እንዲከናወን ያደረገበት አሰራር አንዱ ነው፡፡ በዚህም አቅራቢዎች ረጅም መንገድ ሳይጓዙ የያዙትን ወርቅ ባሉበት አካባቢ እንዲሸጡ የአሰራር ለውጥ በመደረጉ ወርቅ አቅራቢዎች የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

የወርቅ ግብይትን የወርቅ ማዕድን በብዛት ወደሚገኝባቸው አካባቢዎች ማስፋፋቱ ነጋዴዎች ወርቁን ወደ ማዕከል ለማጓጓዝ ይከፍሉ የነበረውን የትራንስፖርትና ተያያዥ ወጪዎች በመቀነስ እና ሥራውን በማሻሻል የበለጠ ተበረታተው ያመረቱትን ወርቅ ለባንኩ እንዲያቀርቡ ታስቦ የተደረገ ነው፡፡

2. ባንኩ የወርቅ ግዥ የሚፈጽመው በዓለም አቀፍ የወርቅ ዋጋ ላይ ተጨማሪ ከፍያ በማድረግ ነው፡፡በዚህም አቅራቢዎችን በማበረታታት ወርቅ በብዛት ለባንኩ እንዲቀርብ የሚያስችል የፖሊሲ እርምጃ ወስዷል፡፡በዚሁ ግንዛቤ ቀደም ሲል ሲሰጥ ከነበረው የዋጋ ጭማሪ 1 በመቶ እና 3 በመቶ ወደ 5 በመቶ ከፍ በማድረግ ተጨማሪ ክፍያ በእያንዳንዱ ግዥ ላይ ለነጋዴዎች እየተከፈለ እንዲሰራ መደረጉን ባንኩ ይገልጻል፡፡

3. ቀደም ሲባል በፖሊሲ በተቀመጠው መሰረት ነጋዴዎች ለባንኩ ወርቅ ሲያቀርቡ በወሩ ውስጥ በተመዘገበው ከፍተኛ የወርቅ ዋጋ ተሰልቶ ክፍያ እንዲያገኙ ሰፊ የዋጋ መምረጫ ጊዜ ይሰጥ ነበር፡፡በወቅቱ የወርቅ ክፍያ እየተፈጸመ የነበረው ወርቁ ለባንኩ ገቢ ከተደረገ በኋላ ሊኖር በሚችለው የወሩ ከፍተኛ ዋጋ ታስቦ ስለነበር የወርቁን እውነተኛ ዋጋ አያመለክትም ነበር፡፡ ይህም በመሆኑ ለወርቅ አቅራቢዎች ሲከፈል የነበረው ገንዘብ በአጠቃላይ ድምር ውጤት ሲታይ በጣም ከፍተኛ ስለነበር ባንኩን ለኪሳራ በመዳረጉ እንዲቀር ተደርጎ እንደነበር ባንኩ አስታውሷል፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች የወርቅ አቅርቦት እየቀነሰ በመምጣቱ መንግሥት አቅራቢዎችን በማበረታታት ከዘርፉ መገኘት የሚገባውን አገራዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ መወሰኑን አስታውሶ፣ ቀደም ሲል ተግባራዊ ተደርጎ ነገር ግን የወርቅ ዋጋ መውረዱን ተከትሎ በተከሰተው ኪሳራ ምክንያት የተነሳውን የ30 ቀናት የዋጋ መምረጫ ማበረታቻ እንደገና ተግባራዊ እንዲሆን መደረጉን አስታውቋል፡፡

4. እላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ዝቅተኛ የቅበላ መጠን ከ150 ግራም ወደ 50 ግራም ፣ዝቅ በማድረግ ዝቅተኛ የፋይናንስ አቅም ያላቸው አምራቾች /አዘዋዋሪዎች ያመረቱትን ወይም የያዙትን ወርቅ በአቅማቸው ለባንኩ የሚያቀርቡበት አሰራር ተመቻችቷል፡፡ በተወሰነው መሰረት እላይ የተጠቀሱት ማበረታቻዎች ከጥቅምት 4 ቀን 2010 አም ጀምሮ በእያንዳንዱ ወርቅ ግዥ ማእከል ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሚገኙ ያመለክታል፡፡ በመሆኑም ወርቅ አምራቾች እና አቅራቢዎች በየክልሉ በሚገኙ የወርቅ ግዥ ማእከላት በመቅረብ ያመረቱትን ወይም አዘዋዋሪዎች ከሆኑም ከአምራቾች የገዙትን ወርቅ ለባንኩ በመሸጥ ከማበረታቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ባንኩ ያስታውቃል፡፡

 

በጋዜጣው ሪፖርተር

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።