የሰሜን ጎንደር ዞን ነዋሪዎች የልማት ቱሩፋትና ጥያቄዎች

06 Dec 2017

 

በጎንደር ከተማ ዙሪያ ከሚገኘው አካባቢዎች አንዱ በሆነው ቆላድባ የወትሮው ጭር ያለ እይታው ደብዝዟል። አካባቢው በርካታ ቁጥር ባላቸው የተሽከርካሪ አይነቶች ተጨናንቋል። የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች፣ ከፌደራል እና ከክልሉ የመጡ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በስፍራው ማልደው ተገኝተዋል። እነዚህ አካላት ከስፍራው ለመገኘታቸው ደግሞ አንድ የጋራ ምክንያት ነበራቸው። ይሄውም ለዘመናት በንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ሲሰቃይ ለነበረው ነዋሪ መፍትሄ ያነገበው የጎንደር ንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የመጠናቀቁ ብስራት የሚሰማበት እለት መሆኑ ነበር።

የልማቱ ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን ተከትሎ የድል አድራጊነት ስሜት ያዘለ የደበዘዘ፣ ያልተሟላ ደስታ የሚነበብበት የፊት ገፅታ ይነበብባቸዋል። ይሄውም የነዋሪዎቹ ደስታ ምልዑ እንዳልሆነ ያሳብቃል። ምክንያቱ ምን ይሆን? የሚል ጥያቄንም ያጭራል፤ ጠየቅንም። የጎንደር ከተማ ነዋሪዎችም ለማስረዳት ወደ ኃላ አላሉም።

በሰሜን ጎንደር ዞን አዘዞ ከተማ ግራር ሰፈር በሚባለው አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ መዝገበ አረጋዊ የውሃው ጥያቄ መልስ በማግኘቱ የተሰማቸውን ደስታ ይገልጹና። አሁንም መልስ የሚሹ ሌሎች የልማት ጥያቄዎች መኖራቸውን ይገልጻሉ። አዘዞ ከተማ እና አካባቢዋ ላይ የኃይል መቆራረጥ እያደረሰ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በማንሳት ችግሩን በሰሜን ጎንደር ዞን በሚገኙ ከተሞችም ተመሳሳይ መሆኑን ይናገራሉ። "በከተማዋ ያሉ በርካታ ወፍጮ ቤቶች፣ ሆቴሎች፣ የውበት ሳሎኖች እና ሌሎች የንግድ ቤቶች ግብር ለመክፈል እጅ እስኪያጥራቸው ድረስ የችግሩ ሰለባ ሆነዋል። ብርት ጥፍት የምትለው መብራት በቀን ውስጥ ከአስር ጊዜ በላይ ትጠፋለች። የመብራት መቆራረጡ በርካታ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን የማቃጠሉ ሁኔታ የመብራቱ ሌላው መዘዝ ነው። ይህም በአካባቢው ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ ከማኮላሸት በዘለለ፤ መንግስት በሚሰበስበው ግብር ላይ ጥቁር ጥላ የጣለም ጭምር ነው” ብለዋል አቶ መዝገበ።

«የውሃ ህይወትነት ያለብርሃን ያልተቋጨ ሩጫ ነው» ሲሉ የመብራት አገልግሎት እንደሌለ በመግለፅ ንግግራቸውን የሚጀምሩት በሰሜን ጎንደር ዞን ደረስጌ ማርያም ቀበሌ ገበሬ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጥላሁን መለሰ ናቸው። አቶ ጥላሁን እንደሚሉትም፤ የአካባቢ ጥያቄ ሁለት ነው። የንፁህ መጠጥ እና የመብራት ጥያቄ። ለበርካታ ዓመታት ከቀበሌ ደረጃ እስከ ክልል በመሄድ ጥያቄውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ቢዘገይም የንፁህ መጠጥ ውሃ ጥያቄው ምላሽ አግኝቷል። የቀረው የመብራት ጥያቄ ስለሆነ በተቻለ ፍጥነት መልስ ሊያገኝ ይገባዋል።

ልጆቻችን በቅርብ ርቀት የቀለም ትምህርት እንዲያገኙ በአቅራቢያችን ትምህርት ቤት ተገንብቶልናል። ነገር ግን ዛሬም ድረስ ልጆቻችን ጥናታቸውን የሚያጠኑት በኩራዝ ነው። ሴቶች ምግብ ለማብሰል አሁንም እንጨትን ይጠቀማሉ። ይሄ ሁኔታ በእርግጥም አሁን ካለንበት ዘመን እና ከአገራችን ሁኔታ ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም" ሲሉ ይናገራሉ፤ አቶ ጥላሁን።

አስተያየት ሰጪው አያይዘውም፤ «በርካታ የገጠር አካባቢዎችን መንግስት የመብራት ተጠቃሚ ማድረጉን እየሰማን ነው። ከጎንደር ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ላይ ተቀምጠን መብራት አልተመለከትንም። መንግስት ሁኔታውን ተገንዝቦ እና አጥንቶ የመብራት ተጠቃሚ አድርጎን ከችግሩ እንድንወጣ እንጠይቃለን» ሲሉም በተማፅኖ መንግስት ለችግሩ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ።

የጎንደር ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት መላኩ ተካ ደግሞ የመብራት ችግር በአካባቢው ለመፍጠር የሚቻለውን የስራ እድል እያኮላሸው መሆኑን በሌላ ወገን ያነሳል። እንደ እርሱ ማብራሪያ፤ በአካባቢው በርካታ ስራ አጥ ወጣቶች ይገኛሉ። የወረዳው መስተዳድር ወጣቶቹን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ማለትም በጣውላ ስራ፣ በዳቦ ቤት፣ በፀጉር ስራ እና ሌሎች የስራ ዘርፎች እንዲሰማሩ ታሳቢ በማድረግ መንቀሳቀስ ተችሎ ነበር። ይሁንና በአካባቢው ያለው የመብራት አገልግሎት ችግሩ ጥረቱ ከመንገድ እንዳስቀረው በቁጭት ይናገራል።

በጎንደር ከተማ ቀበሌ 17 ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ጣይቱ ወርቅነህ ደግሞ ጎንደር ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ታሪክ ያላት ከተማ ናት፤ የንግድ ማዕከልና የቱሪዝም መዳረሻ ከተማ ብትሆንም ከተማዋ እንደ ጥንታዊነቷና ታሪካዊነቷ ትኩረት ተሰጥቷት አልለማችም ይላሉ።

«ከተማዋ በቱሪዝሙ ዘርፍ ብቻ ከፍተኛ እድገትና ተጠቃሚ የምትሆንበትን መሰረት መዘርጋት ይቻላል። ይሁንና መገኘትና መሆን በሚገባው ልክ ቱሪዝሙን የሚያነቃቁ የመሰረተ ልማት ስራዎች እና ሌሎች እንቅስቃሴዎች የሉም። እነዚህና መሰል ዕገዛ ቢደረግላት ኖሮ ታድጋለች፤ ነዋሪዎቿም ተጠቃሚ ይሆኑ ነበር። አሁንም ጊዜው አልረፈደም ብዙ መስራት ይጠይቃል እንጂ» ሲሉ ወይዘሮ ጣይቱ ሀሳባቸው ቋጭተዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ነዋሪዎች ይህንን ሲሉ መንግስት በአካባቢው እያደረገ ያለውን የልማት ተግባር አይክዱም። ለአብነት ያህልም የከተማውን የመናኸሪያ ቦታ ጥበት ለማቃለል ታስቦ በ69 ሚሊዮን ወጪ የተገነባው የአዘዞ ዘመናዊ የአውቶብስ መናኸሪያ ግንባታ ተጠናቆ መመረቁ ለከተማው ነዋሪዎች ደስታን የፈጠረ ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ 870 ሚሊዮን ብር በጀት የተመደበለት የአዘዞ አርበኞች አደባባይና የ12 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ግንባታ በእለቱ በይፋ መጀመሩም ሌላው የልማት ቱሩፋት ሆኗል።

መንግስት በጤናው፣ በመንገድ፣ በትምህርት ቤት ግንባታ ላይ ሰፊ ስራዎችን በማከናወን ማህበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የሄደበት ርቀት መኖሩን አንስተው አመስግነዋል። በኢኮኖሚው ዘርፍም ቢሆን በኢንቨስትመንት፣ በጥቃቅን እና አነስተኛ እና ሌሎች የልማት ተግባራቶችን በማከናወን ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ከመልካሙ ስራ ጋር አብረው የሚጠቅሱት ነው። በእነዚህ የማህበራዊ ፍላጎቶች እጥረት ምክንያት የሚደርሱና ሊደርሱ የሚችሉ መቃወሶችን በእነኝህ ልማቶች መቀረፉ የጎንደር ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች አልዘነጉም። በተጠቀሱት የልማት ዘውጎች መንግስት እንዳከናወነው የልማት ተግባራት ሁሉ በቀሪዎቹ የልማት ጥያቄዎች ላይ አፋጣኝ ምላሹን እንዲሰጥ አጥብቀው ይሻሉ።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባው አቶ ተቀባ ተባበል፤ በነዋሪዎቹ የቀረቡትን የልማት ጥያቄዎችን እና ቅሬታዎች ተገቢነት ይቀበላሉ። አያይዘውም እንዳሉት፤ ለዘመናት ጥያቄ የነበረውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ጥያቄን ለመመለስ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ዘግይቶም ቢሆን በቆላ ድባ የተገነበው የጎንደር ውሃ ፕሮጀክት ምላሽ ሰጥቷል። የነበረውን የንፁህ መጠጥ ውሐ ችግር በመቻልና በትግስት በመጠበቅም የተግባሩን ውጤት ለማጣጣም መቻሉን ተናግረዋል። የህብረተሰቡን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመመለስ በትጋት እንደሚሰራ በመጠቆም፤ በአሁኑም ወቅት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ የሚያስችለው ጥረት ተጀምሯል ይላሉ።

መብራት ያልተዳረሰባቸው አካባቢዎችንም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ተጨማሪ የማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ እየተካሄደ በመሆኑ ችግሩ በዘላቂነት ይፈታል ብለዋል። ከንቲባው በከተማዋ ያሉ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች እንደዘገዩ አምነው፤ ከአሁን ወዲህ ከህዝቡ ጋር በመተባበር ጥያቄዎችን ለመመለስ ሁለንተናዊ ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

«በጎንደር ከተማ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ በሚደረገው ርብርብ እና ጥረት ላይም ህብረተሰቡ ጥያቄውን በትግስት እንዳቀረበው ሁሉ፤ መንግስት ችግሩን ለመፍታት ከሚያደርገው ጥረት ጋር በአብሮነት መስራት አለበት» ሲሉም አቶ ተቀባ ለከተማው ነዋሪዎች መንግስት የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ተሳትፏቸው የማይተካ ሚና እንዳለው በጥያቄም መልክ አቅርበዋል።

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የጎንደር ህዝብ አንዱና ትልቁ ጥያቄው ምላሽ አግኝቷል። ምላሽ የሚሹ ሌሎች በርካታ ጥያቄዎቹን በተገቢው ጊዜና በተቻለው ፍጥነት ምላሽ ለመስጠት ክልሉም ሆነ ከተማ አስተዳደሩ በጥምረት ይሰራሉ ብለዋል።

 

ዳንኤል ዘነበ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።